ውሻው ይጮኻል ግመሉ ይሄዳል የህወሓት አወዳደቅ ከደርገ ኢሰፓ አወዳደቅ የባሰ ነው (ባርናባስ ገብረማሪያም ከትግራይ)

የጅብ ገበሬ ያህያ በሬ
ጦጣ ዘር አቀባይ የንዝጀሮ ጎልጓይ
ልማት እያሉ ከላዕላይ እስከ ታህታይ
አንድም የሌላቸው ሁሉም እንብላ እንብላ ባይ
ዘመናቸው አከተመ ዳግም ላይመለሱ ኦሮማይ ኦሮማይ!!

አዎ!!
ጊዜ ዳኛው ነው ታሪክ ምስክር
የታጋዮች ደም ሲጮኽ ከመቃብር
ዋይታና ልቅሶ ሲያስተጋባ ከቃሊቲ እስር
ልጄ ልጄ ልጄ ስትል እናት ዓለም ለብሳ ጥቁር
ህዝቡ በአደባባይ የወገን ያለህ እያለ ምሬቱን ሲናገር
በገዛ ሀገሩ ባይተዋር ሆኖ ሲናቅ ሲዋረድ ሲገፈተር
ታሪኩ ሲንቋሽሽ ባህሉ ማንነቱ ሲራከስ ሲደፈር
ሀገሩን ጥሎ ሲሰደድ ሲንከራተት ባህር ማዶ ሲሻገር
ኢትዮ}ያ ነበረች ለቀን ጅቦች ገነት ለብዙሃኑ የሲኦል ምድር!!

ሕግን የማያውቅ ሰውኣዊ መብትን የጣሰ
ጨካኝ ስርዓት የአውሬ መንግስት ነገሰ
በአፈ ሙዝ የሚገዛ እርስ በርስ እያናከሰ
በዘር ጥላቻ ቂም በቀል እሳት እየለኰሰ
የህዝብ ባላንጣ ግጭትን እየቀሰቀሰ እያባባሰ
ፍትሕ ለጠየቀ እስር ፣ ዳቦ ለጠየቀ ጥይት እያጎረሰ
የንፁሃን ደም በማፍሰስ የስንቱን ቤት አፈረሰ
ሰብኣዊ ፍጡርን በቁም ሰቅሎ በእሳት እየተጠበሰ
የሰው ልጅ የዶሮን ያህል የናቀ ያረከሰ
በዚህች ዓለም ማን አለ ከህወሓት ስርዓት የባሰ !!

በሌብነት በዝርፊያ በውሸት የተካነ
ሀብታችንን ግጦ ኢትዮ}ያን ያመነመነ
ክብሯን የሸጠ ድንበሯን እየሸነሸነ
ደም መጣጭ ጅግር ለባዕዳን የወገነ
አንጡራ ሀብታችንን ያሸሸ ያባከነ
የፋሽሽት ቡድን ግራዚያኒ ወያነ

ጨካኝ ቡድን በሀገር ላይ ሲሸፍት
ሕግ የማይገዛው የዱር አራዊት
ለእኩይ አላማ ፀረ ኢትዮያዊነት
የመከራ ዘመን የአርባ ዓመት ባርነት

በላያችን ላይ ቀለደብን አሸን በታተነን
ውስጣችን እንደ ምስጥ በላን ባዶ አስቀረን
በረሃብ አለንጋ ገረፈን አሰቃየን አሸበረን
ከልኩ አለፈ ሰለቸን መሸከሙ አቃተን
በቃን ብለን መነሳት ግድ ሆነብን ::

የዚህ ሁሉ ድምር የትውልድ ፍዳ
ቀንበር ተሸክሞ የኖረ የጭቆና ዕዳ
ዕድሜ ለታጋይ ህዝብ ፋኖ ቀይሮ ጋዳ
ዕድሜ ለታጋይ ድርጅቶች እናት ደራሽ ወልዳ
የትግል ሽቦ ተቀጣጠለ የለውጥ ማዕበል ፈነዳ ::

እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ የነጠረ
ከጭቆና ማህፀን ዓቢይ መሪ ተፈጠረ
የኢትዮ}ያ ትንሳኤ ሙታን ተበሰረ
ትግሉ ፍሬ አወጣ ጎመራ ጠነከረ
የጥላቻ አጥር ፈረሰ ከስሩ ተሸረሸረ
ሰንሰለቱ ተበጣጠሰ ካቴናው ተሰበረ
ፍቅር አሸነፈ በይቅርታ ተደመረ
አንድነት ለመለመ ሁሉም ተባበረ
ግንቡን አፍርሶ ድልድይ መሰራት ተጀመረ !!

ታሪክ ራሱን ደገመ
ጨቋኝ ስርዓት ወደመ
ዘረኛ ስርዓት አከተመ::

ዋይ ዋይ ዋይ ዋይ ወያነ
ሞተ ተፈረካከሰ ተበታተነ
እባቡን ተመታ እንደጉም በነነ
ከያለበት እንደ ውሻ እየታደነ

በጭቁኖች ክንድ ተያዘ ተዋረደ
በቆፈረው ጉድጓድ ተደበቀ ተናደ
ራሱ የዘራው መርዝ ራሱ አጨደ
እሱም በተራው ወህኒ ቤት ወረደ::

መቆየት ደጉ ብዙ አሳየን
ጠንክረን ከሰራን ከተባበርን
ብዙ አለ ገና ተኣምር እንሰራለን
የኢትዮ}ያ ገናናነት ዳግም እናነሳለን
በዓለም ላይ ከፍ ከፍ ብለን እንታያለን
መጪው ዘመን ብሩህ ነው እናሸንፋለን::
ነገር ግን!!
ዛሬ ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ
የመስዋእት ዋጋ የታጋዮች ውለታ
ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን እንዳይገታ
ለውጡ እንዳይነጠቅ ግቡን እንዲመታ
እንዲጠነክር እንዲጎለብት እንዲበረታታ
ወደፊት እንዲራመድ በፈጣን እመርታ
ሳንወላውል ሳንዘናጋ ላንድ አፍታ
ዘብ መቆም ነው የሁላችንን ግዴታ !!

ወጣት ሽማግሌ ገበሬ ወዛደሩ
አርቲስት ካህን ተማሪ መምህሩ
ሁሉም በያለበት በከተማ በገጠሩ
በውጭ ያላችሁ ሁሉም በየአገሩ
ላንዲት እናት ሀገር ጠንክረው ሲሰሩ
ሀገሬ ማለት ይኸው ነው ሚስጢሩ::

ካለፈው ስህተታችን ተምረን
ውስጣችን አጥበን ንስሃ ገብተን
በዴሞክራሲ ጠበል ተጠምቀን
ተያይዘን ተባብረን ወደፊት ተራምደን
እኛም ራሳችን የለውጥ ሰዎች እንሆናለን::

ደህና ሁን ወያነ

ትግራይ አትሆኑም የሌባ መሸሸጊያ
ጊዜ የጣለው የታሪክ ትቢያ
የቀን ጅቦች ዋሻ መደበቂያ
የሌባ ከለላ ምሾ መቆዘምያ
የካሃዲ ቡድን መርዝ መፈልፈያ::

ወያነ ሆይ!!
ሞኝህን ፈልግ ባንተ ማን ይታለላል
በትግራይ ህዝብ ደም መነገድ ለምደሃል
እንደ ድሮ አይደለም ህዝቡ ነቅቷል
ያንተ ተንኰል ላርባ ዓመት ሰልችቶታል
ቆበሮና ፍየል በውል ለይቶ ያውቃል
ወግ ነው ሌባ ልጅ እየበላ ያለቅሳል
እንደ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል
የጭቁኖች ደም ጠጥተህ ሰክራሃል አብዳሃል
ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ምን ያስገርማል
ላታመልጠን አታሩጠን ቀኑ መሽቶባሃል::
የአንድነት ካንሰር ትውልድን የበከለ
ዜጎችን ያኰላሸ አካልን ያጎደለ
ሀብትዋን የዘረፈ ህዝብዋን የበደለ
የቀን ጅብ ሌባ ሌባ ካልተባለ
የበሰበሰ ጋንግሪን ተቆርጦ ካልተጣለ
ምርቱንና እንክርዳዱን ካልተለየ ካልተንጓለለ::

በፍፁም አንመለስም ወደሗላ
እርቅ የለም ከደም ነጋዴ ደላላ
ከነብሰ ገዳይ ሽፍታ የባዕድ ዲቃላ
የዕድገት ጋሬጣ እሾህ አሜኬላ
እናቱን አስማምቶ ሀገሩን ሽጦ ከሚበላ::

ትግላችን ገና ነው ጠንክሮ ይቀጥላል
ውሻው ይጮኻል ግመሉ ይራመዳል
ሌባን ለማጥፋት ምንጩን ማድረቅ የግድ ይላል!!

የተከበራችሁ አንባቢዎች

የነቃ ፣ የተደራጀ ፣ ጠላቱንና ወዳጁን ለይቶ በግልፅ ያወቀ ህዝብ ይቅርና የወያነ እንደ ሾላ ፍሬ ውስጡ ውስጡን በስብሶ በመፈረካከስ ላይ ያለው የወደቀ ብቱቱ ስርዓት ቀርቶ ሌላም ቢመጣ ከንእንግዲህ ወዲህ ከቶውኑ የደም መሰዋእትነት ከፍለን በትግላችን ያገኘነውን የለውጥ ጭብጦን የሚነጥቀንና ወደሗላ የሚመልሰን ምድራዊ ሀይል አይኖርም ብዬ በፅኑ አምናለሁ:: ዕድሜ ለታጋዩ ህዝባችን ፣ ዕድሜ ለጀግናውና ታላቁ መሪያችን ክቡር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በሚከተለው ቆራጥነትን ብስሌትን ጥበብን ትዕግስትንና ሙያን የተላበሰ ሳይንሳዊ አመራር ትልቁን ስጋት አልፈነዋል :: ከእንግዲህ ወዲህ የወያነ ዘረኛ አገዛዝ ተመልሶ ይመጣል ብሎ ማሰብ የህወሓት ካድሬዎችና አጃቢዎቻቸው መለስ ዜናዊ ከመቃብር ተነስቶ ሀገር ያስተዳድራል ብለው ቢሰብኩ ይሻላቸዋል:: አሁን የቀረው ትልቁ ጉዳይ ሀገርን መገንባት ነው:: ከማፍረስ ይልቅ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው እንደሚባለው ሁሉ ዛሬ ሀገርን ለመገንባት ደግሞ የአንድ መሪ ስራ ብቻ አይደለም:: እያንዳንዱ 100 ሚሊዮን የኢትዮ}ያ ህዝብ ለውጡን እንደ ዓይን ብሌኑ በማየትና የህልውናውን መሰረት መሆኑን በማመን ሁሉም እንደየ ዓቅሙና ችሎታው ኰረት ሲያቀብል ብቻ ነው ዕድገት የሚመጣው:: አለበለዚያ አንድ ሰው ይጋግራል ሽህ ሰው ይበላል የሚባለው ስሌት በፍፁም አይሰራም :: ህዝቡ የሀገርና የልማት ባለቤት ማደረግ አለብን ካልን ደግሞ የትግሉና የግንባታ ባለቤትም መሆን ያለበት ህዝቡ ራሱ ነው:: ስለዚህ የህዝብና የመንግስት ሃላፊነት መሆን ያለበት መታገል ፣ በትግል የተገኘውን ድል ዘብ ሆኖ መጠበቅና ሀገርን ተባብሮ መገንባት ናቸው:: የዶክተር ዓቢይ በሳል አመራር የወያነ የረቀቀ ሴራን ሳይበግረው ተደጋጋሚ የግድያ ምኮራን ሳይቀር በረቀቀ ጥበብ አሸንፎ እዚህ አድርሶናል:: ይህ ታላቅ ውለታ ነው::

እኔም ለዚሁ ታላቅ መሪና ህዝብ ካለኝ ክብርና ፍቅር በተለይም ለለውጡ መሳካት ካለኝ ፍላጎትና እልህ በመነሳት ከላይ በግጥም መልክ እንደ ወረደ ያቀረብኩትን ፅሑፍ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ያላችሁ ሚዲያዎች ባላችሁ የራሳችሁ ጥበብ ቀኝታችሁ ለንባብ እንድምታደርሱልኝ ተሰፋ አደርጋለሁ::

ውሻው ይጮኻል ግመሉ ይሄዳል
የህዝብ ትግል ያሸንፋል

ባርናባስ ገብረማሪያም
ከትግራይ

[gview file=”https://www.satenaw.com/amharic/wp-content/uploads/2018/11/The-Camel-Marches-while-the-Dog-keeps-on-Barking.pdf”]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.