በደቡብ ክልል የዞን ምክር ቤቶች ባነሱት የክልል ጥያቄ ዙሪያ – አቤኔዜር ይሳዕቅ

ደቡብ ክልል ላይ ያለው አካሄድ በመጣው የለውጥ ጅማሮ መብታቸውን መጠቀም መጀመራቸውን የሚያሳየው? ወይስ በዶር አብይ የአመራር ችግር የተከሰተ ነው?

ደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ የዞን ምክር ቤቶች የክልልነት ጥያቄዎችን አሁን ላይ በተከታታይ ማንሳታቸው አንዳንዶች “የመበታተን ምልክት ነው” ሲሉ ዶር አብይን የሚተቹ ደግሞ ሀገር “የመምራት ብቃት ስለሌለው” የተከሰተ አድርገው እያቀረቡ ነው። በእኔ በኩል ጉዳዩን በዚያ መንገድ አላየውም። በተቃራኒው የየዞኖቹ ምክር ቤቶች ውሳኔያቸው የሚያሳየው ነገር:-

1. ባለፉት 27 ዓመታት ያለፍላጎታቸው በትህነግ-ኢህአዴግ ታፍነው መቆየታቸውን እንጂ የዶር አብይን ሀገር የማስተዳደር ችግር አይደለም። ልብ ብሉ ይሄንን ውሳኔ እየወሰኑ ያሉት ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ የደኢህዴን-ኢህአዴግ አባላት ናቸው። እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳን ወደ ክልልነት የማድግ ፍላጎት ቢኖራቸውም በትህነግ መሪዎችና የእነሱ ተወካዮች በነበሩት በእነ ሽፈራው፣ ሀይለማሪያም ወዘተ በኩል ታፍነው ዝም ብለው ነበር።

2. ሌላው ደቡብ ክልል መጀመሪያም 5 ክልሎች ማለትም ከክልል 7 – 11 ያሉት ክልሎች በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ተጨፍልቀው የፈጠሩት ክልል ነው። መነሻው ላይም በሕዝብ ፍላጎት የተመሰረተ አይደለም። ሌሎች ከአንዳንዶቹ በቁጥር ጭምር ያነሱ ሆነው ክልል ሲባሉ በደቡብ ክልል ውስጥ ግን ያ ባለመሆኑ በርካታ ቅሬታ ነበር። ይሄንን በተጨማሪ የሚያሳየን ነገር የተመሰረቱት ክልሎች በሙሉ በሕዝብ ፍቃድ ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ነው።

ለማንኛውም አሁን አፋኙ ቡድን በሕዝባዊ አመጹ ስለተወገደና ዶር አብይም ከድርጅቱ ላይ ያለውን ማዕከላዊ አሰራርና የአፈና ሰንሰለት ስላነሳላቸው የፈለጉትን በመወሰን ላይ ናቸው። ስለሆነም ውሳኔያቸው የዶር አብይን የ አመራር ብቃት ችግር የሚያሳይ ሳይሆን በተቃራኒው ዶሞክራሲያዊ አካሄድንና በነጻነት ውሳኔ ማስተላለፍ መጀመራቸውን እየተለማመዱ መሆኑን ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.