ዛሬም ዳግም የተከዳችው አዲስ አበባ (ቃል ኪዳን ኃይሉ)

 


(ቁም ነገር መጽሔት ላይ የወጣ)
.
እለቱ ሐሙስ ነው፡፡ ወደ ስራ ለመሄድ ታክሲ ውስጥ ነኝ፡፡ ከምኒሊክ አደባባይ በስተግራ በኩል አንዲት እድሜና ዘመን ያደከማቸው እናት ምርኩዛቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ መስተዳደር ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ባለው የመሻገሪያ መንገድ ላይ ምርኩዛቸውን እየተደገፉ በቀስታ ይሻገራሉ፡፡ ከእሳቸው ፊትለፊት ሁለት ወንድና ሴት ፖሊሶች ስልካቸውን እየጎረጎሩ እየተሳሳቁ ጎን ለጎን ቆመው ያወራሉ፡፡ ደካማዋ እናት ለመሻገር ሲሞክሩ መኪናው ከዚህ ከዚያ ማደነበሩ ሳያንሳቸው አንድ አእምሮውን ሳተ ያደረገ ጀብራራ ዘሎ ተጠመጠመባቸው፤ ፊታቸው ላይ ድንጋጤ ይታያል፡፡ አደባባዩን የሚዞሩ በላታክሲዎች በክላስና በጩኽት ልቀቃቸው እያሉ ተቆጡ፤ ጀብራራው ግን ሊለቃቸው አልቻለም፡፡ ከዚያም ሁለት ሰዎች መጥተው መነኩሴዋን እናት አስለቅቀው አሻገሯቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ፖሊሶቹ ከስልካቸው ቀናም አላሉም፡፡
.
ማታ ከስራ ስመለስ ደግሞ ስቴዲየም አካባቢ ኳስ ጨዋታ አልቆ ተመልካቾች እየተበተኑ ነው፡፡ ታዳሚዎቹና የአዲስ አበባ ፖሊስ ግን እንደ ቶሚና ጄሪ እየተሯሯጡ ነው፡፡ በተለየ የሚደግፉትን ቡድን ማልያ የለበሱ ወጣቶች ከፖሊሶች ፊት ለፊት ከተገኙ ፖሊሶቹ አይን ወይም ጭንቅላት ሳይሉ የያዙትን ሽመል አለስስት በየጥኛውም የልጆቹ የሰውነት አካል ላይ ያሳርፋሉ፡፡ ወጣቶች በየጉራንጉሮ እየተሯሯጡ ይደበቃሉ፡፡ የሚደግፉትን ማልያ መልበስም በየትኛው ፍትሐብሔር ሕግ እንደተከለከለና በዱላ እንዲሚያስነርት ተጽፎ ባለነብም ወይም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከየትኛው አካል የአዲስ አበባን ወጣት አባረህ በለው እንደተባለ ባለውቅም ባለጊዜው “የአዲስ አበባ ፖሊስ” ግን ልጆቹን እያሳደደ ይደበድባል፡፡ ይህኔ ነው አዲስ አበባን ማን ነው ነጻ የሚያወጣት ስል ራሴን የጠየኩት?
.
አዲስ አበባ ማን ነጻ ያውጣት?
አዲስ አበቤነት ዱሮ ዱሮ ለዘማናዊነት የቀረበ፤ ቀለለ ያለ ኑሮ የሚኖርባት፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም የሀገሪቱ ጥግ መጥቶ ሰርቶ የሚለወጥባት፤ ነግዶ የሚያተርፋባት፤ ከየት ነህ የማን ዘር ነህ ሳይባል በአስተሳሳቡ፣ በማኅበራዊ ትስስርና ግንኙነቱ ብቻ የሚዳኝባት ከተማ ነበረች፡፡ አዲስ አበባ፡፡
.
ቋንቋን መሰረት ያደረገው የብሔር አወቃቀር ያለው ሕገ መንግስት ከተቀረጸ በኋላ አዲስ አበባን በአንቀፅ 49 ላይ ከክልል አስራ አራትነት በይፋ ተፍቃ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት የሆነ ራስ ገዝ እንዲሁም የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ሆነች፡፡ “ይህ አካሄድ አዲስ አበባን የኦሮሚያ የሚያደርግበት ምንም መንገድ የለም ግን የከተማዋን ሕልውነት የተፈታተነ ውሳኔ ነው” ይላሉ በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራን ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም “ከሕገ መንግስቱ በፊት የክልል ያህል ድምጽ ያላትን የሀገሪቱን ዋና ከተማ ከክልል አሳንሶ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዳትወከል አድርጎ፤ ከዚያም ከፍ ሲል አዲስ አበባን እንደ ክርስቶስ ጨርቅ በአራቱ የኢሕአዴግ ማኅበረ ፓርቲዎች ስር የፈረቃ ንግስናን እንዳታስተናግድ ወይም የሽኩቻ ሜዳ ሆና እንድትቀጥል ያለውዴታ ግዴታ ውስጥ ያስገባ ውሳኔ” ሲሉ ተቃውሟቸውን ያነሳሉ፡፡
.
በዚህ ተቃርኖ ውስጥ የቀጠለችው አዲስ አበባ እስከ 1996 ድረስ በአራት ኪሎው መንግስት ተረስታ ምንም አይነት የልማት ፀሐይ ሳይሞቃት በሰበሰች፡፡ ይህን የተመለከቱ “ደፋር” የአፍሪካ ሐገራት መሪዎች ጭምር ከተማዋ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነት የማትመጥን እንደሆነችና መቀመጫነቷ ተነጥቆ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ የአፍሪካ ከተማ እንዲቀየር ጠየቁ፡፡
.
በዚህ ባልተጠበቀው ጥያቄ የተደናገጠው ሕውሐት/ኢሕአዴግ “ሁሉ ነገር ወደ አዲስ አበባ” በማለት አዲስ አበባን ለማደስ በይበልጥም የህብረቱ መሪዎች ርሃብና ጥማት የሆነውን ባለኮከብ ሆቴል በፍጥነት መገንባት ጀመረ፡፡
.
በዚህ “የልማት” ትንቅንቅ ውስጥ ግን ሕውሐት/ኢህአዴግ ሳያስበው በከፈተው የማርያም መንገድ ገብቶ ቅንጅት የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕብረት አዲስ አበባ ላይ ሙሉ ለሙሉ በዝረራ ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን አሸነፈ፡፡ ይህኔ ነበር ወትሮም በጠላት አይን የምትታየው አዲስ አበባ መስመር አበጅታ ሙሉ ለሙሉ የሕውሓት/ኢሐአዴግ የጠላት ቀጠናነቷን በገዛ ካርዷ ያስመሰከረችው፡፡
.
ይህች ባለቤት አልባዋ ከተማ፤ ወይ ክልል ያልሆች፤ ወይ ልብ ገዝታ ራሷን በራሷ ያላስተዳደረችው አዲስ አበባ የፖለቲካ መናኽሪያነቷ፤ ዓለም ላይ ካሉት የዲፕሎማቶች መቀመጫ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከአርባ እጅ በላይ የሚዘወርባት፤ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትልቁ የምጽዋት የገንዘብ ምንጭ፤ የፌደራልና የአፍሪካ ሕብት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ እንዳይሆን እንዳይሆን ተወጋች፡፡
.
ሕውሓት/ኢህአዴግ ወትሮ የአዲስ አበባ የሆነውን ፖሊሷንና ትራንስፖርቷን ወደ ፌደራሉ አዞረ፤ ኦሮሚያን ከናዝሬ በማስነሳት አዲስ አባባ የክልሉ መቀመጫ እንዲሆን ነገር ሸረበ፡፡ ይህን ከተማውን በእጅ አዙር የመጠቅለሉ ሴራ የተመለከቱት የቅንጅት አመራሮች ፓርላማ ላለመግባት፤ አዲስ አበባንም ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ አዲስ አበባና ነዋሪዎቿ ግን በሕውሓት/ኢሕአዴግ ቂም የልጆቿን ደም ከማፍሰስ እስከ ሕይወት መገበር ደረሰች፡፡
.
በዚያም ያልበቃው ቂም ግን አዲስ አበባ ላይ የሚገደረገው ምንም አይነት የመሰረተ ልማት ግንባታ በነዋሪዎቿ እምባና ሐዘን፤ መፈናቀልና ጎደና መተዳደር፤ ከለመዱት ካቀኑት ሰፈር፤ ወልደው ከሳሙበት፤ አግብተው ካረጁበት ቀዬ በግፍ በመባረር የሀገሪቱ ዳር ተጥለው የከተማው የግድ ዘብ እንዲሆኑ ተፈረደባቸው፡፡ የከተማውን ቀደምት ሕንጻና መለያ የሆኑ ቦታዎችን ከካርታው በማጥፋት በነዋሪቿ ለቅሶና ደም ላይ አዲስ አበባ ዳግም ተቆረቆረች፡፡ በእውቀቱ ስዩም እንዳለው “city without past” ሆነች፡፡
.
አዲስ አበቤነትና ፖለቲካ
ብዙ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአዲስ አበቤዎች የሚሰጡት አመለካከት የተለያየ ነው፡፡ ይበልጥ ግን ፖለቲካን መሰረት ያደረገው እይታ የሚያስቅና አንዳንዴም የሚያስቆጣ ነው፡፡ አዲስ አበቤው በፌደራል መንግስቱም ሆነ በራሷ በከተማዋ ውስጥ ተወክሎ ይሄ ነው የሚባለውን የስልጣን እርከን ላይ አይታይም፡፡ ይህ አለመታየቱ የአዲስ አበባ ተወላጅ ለአቅም ፖለቲካ ብቁ አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ላይ ያደረሰ ይመስላል፡፡ ሰላም (ስሟ የተቀየረ) የተባለች አንድ አስተያየት ሰጪ የአዲስ አበባ ልጅ ላለፉት ሃያ ሰባት አመት በፌደራሉም በከተማው የስልጣን ተዋረድ ላይ አለመታየቱን እንዲህ ስትል ትገልጻለች “የአዲስ አበባ ልጅ መሆን የሚችለው ብዙ ጊዜ አርቲስት ወይም ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ወጥቶ መኖር (ስደተኛ መሆን) ወይም ደግሞ ሀገር ውስጥም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ጎመና በጤና ብሎ መኖር ካልሆነ በሱስ መናወዝ ነው እንጂ ፖለቲካ ብዙም አይደፍሩም፡፡” ይህ ሐቲት ብዙዎች የሚጋሩት ይመስላል፡፡
.
እውነታው ግን ከዚያ ራቅ ይላል፡፡ ከአቶ መለስ እስከ ዶክተር አብይ ያለው መንግስት ከተሜነት ጠልና ክርር ያለ ዘውጌ ብሄርተኛ ነው፡፡ ይህ ጎሰኛ ቡድን ከእኔ ጎሳ ውጪ የተበደለ፤ መከራ የቀመሰና የተሰቃየ የለም የሚል የሮሮ ትርክት ስላለው ከእሱ ውጪ ሁሉም ጠላቶቹ ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ከተሜነት ላይ አንድም ከበታችነት ስሜት የተነሳ ሌላም የጎሳ ፖለቲካው የተገነባበትን መሰረት የሚንደው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ስለሚያቀነቅንብት ከተሜ ላይ ቂም የቋጠረ ነው፡፡
.
ስለዚህም ከተሜው ከዘር ይልቅ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነቱን ፈልጎ አንዳንዱም ከእናቱ አስበልጦ የአባቱን ዘር መምረጥ አቅጦት ወይም በተቃራኒው፤ አልያ ሳይፈልግ ቀርቶ ሁሉን የሚያስማማለት ኢትዮጵያዊነት በልጦበት ለስልጣን ሲል ከአራቱ የብሔር ድርጅት አንዱን መርጦ ለመቀላቀል ስላልፈቀደ አዲስ አበቤን በሚኒስትሩም ሆነ በከተማው የስልጣን ተዋረድ ልናየው አልቻልንም፡፡
.
በስልጣኑ ስላልተወከለ ግን መናቅና መሰደብ ብሎም የተጠና፣ የተጠናከተረና ሆን ተብሎ ለሚደረግ በደል ጫንቃውን አደንድኖ ይቀመጣል ማለት አይደለም፡፡ የኢሕአዴግን መንግስት ከ1993 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ህጋዊና ዲሞክራሲያው መብቱን እየተጠቀመ ሲሞግትና ሲታገል ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማው ወጣቶች ሕይወታቸውን ከመገበር እስከ ብዙ አመታት ወይኒ ለመታጎር በቅተዋል፡፡
.
በቲም ለማ የመጣው ለውጥም ቢሆን እንደፈጣሪያቸው ሕውሓት ሁሉ ጎሳን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ከማይመርጠው ህዝብ ውጪ ያለውን ሁሉ ከመጤፍ ያለመቁጠር አባዜ በጉልህ ታይቶበታል፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ጀምሮ የተለያዩ የቅጽል ስምና ስድቦች፤ እንዲሁም እንደሕዝብ ንቀትና መደፈር በዶክተር አብይ የስልጣን ዘመንም ከፍ ብሎ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው የዶክተር አብይ አስተዳዳደር ብዙ አድርጎ አዲስ አበባ ላይ “እንዳምናው ባለ ቀን ያምናውም ተቀጣ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ” የሚል ስንኝ ያለውን የቴዲ አፍሮ ጃ ያስተሰርያልን ዘፈን ዳግም እንዲቀነቀን በር የከፈተው፡፡
.
የምርጫ ዘመኑን የጨረሰውን የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔን በመበተን ሕጋዊ ምርጫ ማካሄድ፤ ካልሆነም ጊዜው ለምርጫ አመቺ ካልሆነም የከተማዋ ነዋሪ ለሆነ የባለአደራ መንግሥት ከማስረከብ ይልቅ የአዲስ አበባን ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/2003 አንቀጽ 13 ላይ የተደነገገውን “የተከተማዋ ምክር ቤት ከንቲባ እና ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት አባላት መካካል” ይመረጣል የሚለውን ሕግ ጥሶ አንድን ሰው በመሾም ለአንድ ሰው ወይም የሆነ ቡድንን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣ ሕግ bill of attainder የሚለውን መርህ የጣሰ ነው፡፡
.
ይህም ብቻ ሳይሆን የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 49 (2) ጥሶ፤ ሕገ ወጥ ህግ በማውጣት በምክት ከንቲባ ማዕረግ ሦስት ሰዎች በመሾም ይበልጥም ደግሞ የኦህዴድ/ኦዴፓውን ሰው ጠንክሮ እንዲወጣ በማድረግ፤ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አጠገብ ካሉት ውስጥ ለቦታው ቅርበትም፤ ከተገቢነት አንጻርም ለቦታው ትገባለች የምትባለውን ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስን ትራንስፖርት ሚኒስቴር አድርጎ ራቅ አድርጎ ሾሞ ኦህዴድ/ኦዴፓ የፈጣሪውን የሕውሓትን የአግላይ ጠቅላይነት መንገድ አጥብቆ ተከትሏል፡፡
.
“ለምን የከተማዋን ስነልቦናና አመለካከት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው አልተመረጠም” ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ምኒስትሩ የመለሱት መልስ “በዘር መነጽር ታይቶ እንጂ ቢሮ ሳይሆን ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ሦስት ምክትሎች መድበናል ከንቲባ የሚሾመው የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ነው” የሚል መልስ በመስጠት ነገሩን በቃላት ሽወዳና የጥያቄውን መሰረት ለማሳት ሞክረዋል፡፡
.
ተሿሚው “ምክትል ከንቲባም” የኦነግ መሪዎች ሲመጡ ያደረገው ስሜታዊነት የተቀላቀለበትን፤ ከቆመበት መድረክ ሊያርግ እስኪመስል ድረስ እየተመነጨቀ ለቄሮና ለአቶ ዳውድ ኢብሳን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እንዳላደረገ ሁሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች በግፍ ሲታሰሩ፤ ዓይናቸው ስር አስለቃሽ ጭስ ሲወረወር፤ ብሎም የከተማው ወጣቶች በጥይት ሲገደሉ ድምጹን ሊያሰማ አለመፈለጉ፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ሰብሰብኩ ብሎ ማን እንደወከላቸው ከማይታወቁ ሰዎች ጋር መወያየቱ “ምክትል ከንቲባውን” ብሎም ሿሚውን ጠቅላይ ምኒስተር ትዝብት ውስጥ ጥሎ አልፏል፡፡
.
“ተረብሾ የጮኽ ሁሉ ረባሽ ይባላል” እንዲል እያዩ ፈንገስ፡፡ በባንዲራ ግጭት በተነሳ አለመግባባት እንዲሁም በቡራዩና በአካባቢው በተነሳ መጠነ ሰፊ ጉዳት ላይ ሰልፍ የወጣው የከተማዋ ነዋሪ ላይ በፌስቡክ ገጻቸው ዛቻና ማስፈራሪያ የሰነዘሩት የፍትህ ሚኒስተሩ ቃላ አቀባይ አቶ ታዬ ደንደአ፤ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ደግሞ ለገደሉና ላሰሩዋቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የሰጧቸው ምክንያቶች እንደቀድሞ ጊዜ ሁሉ ዛሬም በጅምላ “ጫት የሚቅሙ፤ ሺሻ የሚያጨሱ(ሌላው የማይቅም የማያጨስ ይመስል)፣ ቦዘኔ፣ መሳሪያ የሚቀሙ…” ብሎ የከተማውን ነዋሪ ለማሸማቀቅ የተጠቀሙበት ቃለት ስንሰማ ዛሬም አዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱን ከተሞችን የሚመጥን ስርአት ለማምጣት ትግል የሚያስፈልግ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡
.
ፊንፌኔን ጎርጉሮ በረራን የወለደው የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ
አዲስ አበባ የኛ ነው ትርክት የተጀመረው ዛሬ ባይሆንም፤ ቀድሞ ውጪ ያሉ አክቲቪስቶችም ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያወሩት ለፖለቲካ ታክቲክ ነው ተብሎ ይታለፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲና አክቲቪስት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ እንዲህ ያለ አፍራሽና ብቻዬን ልብላው የፖለቲካ ትርክት ሲመጣ ግን ብዙዎችን የሚያስደነግጥ ሆነ፡፡
.
“ፊንፊኔ በታሪክም ሆነ በሕግ የእኛ ነው” የሚል ትርክት ብሎም ሌሎች እንዲኖሩ ሳያስፈቅዷቸው በግድ እንፍቀድ የሚሉ አምስት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሐቲት ላይ የተለያዩ ተቃውሞዎች ከየአቅጣጫው ተሰነዘረበት፡፡ ተቃውሞው ፊንፊኔን የአዲስ አበባ አቻ ስያሜ ሊሆን አይችልም ከሚል እስከ የከተማዋ ቀደምት ነዋሪነት የሚያጠይቅ ታሪክና ዶሴ ይገላበጥ ጀመር፡፡
.
በዚህ ጉዳይ በመረጃ ጠብሰቅ ያለ ዳሰሰ ያሰናዱት አቶ አቻምየለህ የተባሉ አክቲቪስት እንዲህ በማለት የፊንፊኔ የአዲስ አበባ አቻ ትርጉም መሆን አለመቻሉን ያስቀምጣሉ፡፡ አቶ አቻምየለህ እ.አ.አ በ1860 ክራፕፍ የተባሉ ጀርመናዊ ምሁር ኢትዮጵያ መጥተው የጻፉትን መጽሐፍን ዋቢ በማድገር እንዲህ ሲሉ ይሞግታሉ “የክራፕፍ ምስክርነት እንደሚነግረን ፊንፊኔ፣ የካ፣ ጉለሌና ገላን የተባሉ የኦሮሞ ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ መሬት እንደነበረች አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ፊንፊኔ ልክ እንደ የካ፣ ገላንና ጉለሌ ራሷን የቻለች መንደር፤ የየካ የገላንና የጉለሌ ጎሳዎች አካል ያልሆነች የራሷ ጎሳ ይኖርባት የነበረች እንጂ የየካ፣ የጉለሌና የገላን ሰዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ ቦታ አልነበረችም፡፡ ለዚህም ነበር አዲስ አበባ ማለት ፊንፊኔ ማለት አይደለም ስንል የከረምነው፡፡” በማለት ፊንፊኔ የአዲስ አበባ አቻ ቃል መሆኑ ላይ ጥያቄን የሚያነሱት፡፡
.
አቶ ሐብታሙ ተገኝ የተባሉ ጸሐፊ ኦጂኤስ ክራውፎርድ፣ ሪቻርድ ፓንክረስትን እና ሀርት ዌትግ ብሪትሪት፤ ሳሙኤልዎከር እና ማርሶ ቪጋኖ እንዲሁም የታዋቂውን የጣሊያናዊ የካርታ ባለሙያ ፍራው ማውሮ ካርታ ዋቢ በማድረግ የአዲስ አበባ የጥንት ስም በረራ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ አመክንዮዋቸውንም ሰፋ ሲያደርጉ “በረራ የነገስታቱ ቀዳማዊ ዋና መቀመጫ ከተማ መሆን ከአጼ ዳዊት ቀዳማዊ ዘመን (ከ1380-1413) ድረስ፣ እንዲሁም ከአጼ ልብን ድንግል ስርወ መንግስት ዘመን ማለትም (ከ1408-1480)፣ በረራ ከመቶ በላይ አገልግላለች” ይላሉ፡፡
.
በስቶኒ ብሪክ ዩንቨረስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሽመልስ ቦንሳ (ፒኤች ዲ) “አዲስ አበባ ከየት ወደየት?” በሚል ርዕሥ ባስነበቡት ጽሑፍ ላይ ስለ አዲስ አበባ ቀደምት ኗሪዎች እንዲህ ሲሉ ያስነብቡናል “በከተማዋም ሆነ በዙሪያዋ እንደ ወረብ ባሉት ግዛቶች ይኖሩ የነበረው ማኅበረሰብ በብዛት ከአምሃራ፣ ከጉራጌ እና ከጋፋት (ከሶስቱም ተቀራራቢ ቋንቋዎች ይናገራሉ) የተውጣጣ እና ክርስትና እምነት ተከታዮች የነበሩ ሲሆን በተጨማሪም የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ ይገኙ እንደነበር ይታሰባል፡፡” ሲሉ የአራቱ ዘውጌ ፖለቲከኞችን “አዲስ አበባ የእኛና የእኛ ብቻ ነች” የሚለውን ትርክት ታሪክ በማጣቀስ ሊሞግቱ ይሞክራሉ፡፡
.
ዘውጌ ፖለቲከኞቹ የመዘዙት የአዲስ አበባ ካርድ ፊንፊኔ የሚለውን ስም ከማጠየቅ አልፎ የቀደምት ኗሪውን ማንነት እስከ ማስጎልጎል ደርሷል፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች በሚለው ትርክት የማይስማሙት በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት ብአዴን/አዴፓም ጭምር ነው፡፡ ብአዴን/አዴፓም የሚቀበለው ትርክትም “የአዲስ አበባ ባለቤት ነዋሪዎቿ ናቸው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም…” በማለት የአስራ ሁለተኛው የብአዴን/አዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ አቀባይ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደ ገልጸዋል፡፡
.
ስለዚህ ቀጣዩ የኢህአዴግ ጉዞ አሁን ካለበት ብዙ የፖለቲካ ስንክሳር ባሻገር ወይም የአንበሳ ድርሻውን ተግዳሮት የሚገጥመው በአዲስ አበባ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በትልቁ የሚፈተኑበት ነገር የአዲስ አበባ ህልውናዋን አስጠብቆና የሚያቀና ፖሊሲ መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዶክተር አብይ መንግስትም አዲስ አበባ ላይ ባሳየው ቸልተኝነትና አድሎ የሚመስል ዝምታ እስከሞት ድረስ ዋጋ የከፈለለትን ደጋፊ ከማስቀየም አልፎ የመደመሪያ ማሽኑ ላይ ያለውን መቀነስ ተጭኖ በጊዜ እየወረደ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ አተያይ ትሻለች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.