ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ዳኡድ ኢብሳ በጋራ መግለጫ ሰጡ

«ተጠላልፎ ከመዉደቅ ተደጋግፎ መራመድ» በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ተወያዩ፡፡

 በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማእከል በተከናወነው በዚሁ ውይይት ላይ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት በተደረገው በዚህ ውይይት የኦዲፒ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የመነሻ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት በሚል ሃሳብ ላይ የተነሱት አቶ አዲሱ ትግሉ አሁን ስላለበት ደረጃ ማብራሪያ ከመስጠታቸውም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ቀጣይ የትግል ምእራፍ አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበት በመነሻ ሀሳባቸው ዘርዝረዋል። ‹‹በአንድነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር›› በሚል መሪ ቃል በተከናወነው በዚህ ውይይት ማጠቃለያ ተሳታፊዎቹ ውይይቱን ለማስቀጠል እንዲቻል  በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ለማቋቋም መወሰናቸውን የኦዲፒ፣ የኦፌኮ እና የኦነግ አመራሮች አስታውቀዋል። መድረኩ በፓርቲዎች መካከል ችግር ቢያጋጥም በውይይት ይፈታል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች  በተገኙበት የዚህ ውይይት አላማ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 14 የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር;  በተናጠል የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች በጋራ 1 ጠንካራ ፓርቲ ሊመሰርቱ የሚስችሉበትን ሁኔታ መፈተሽ ነው።

ፎረሙ እንዲመሰረት ከተስማሙ በኋላ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ; የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የኦነግ መሪ አቶ ዳኡድ ኢብሳ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል::

አቶ ለማ  በመግለጫቸው “የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም እንዲቋቋም ተወስኗል:: የፎረሙ መቋቋምም በየጊዜው ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ነው:: በፓርቲዎች መካከል ችግር ካጋጠመም ችግሩን በመደማመጥ እና በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ነው” ካሉ በኋላ “መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ ይገኛል::፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡ ለዚህ ሥራ ሊተባበር ይገባል” ብለዋል::

“ኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ የተጠኑ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆኑን የገለጹት አቶ ለማ፥ “የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁን ህዝቡ ይህንን በንቃት መመልከት አለባቸው:: እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ተያይዞ ከመውደቅ ይልቅ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ በጋራ መቆም ወሳኝ ነው” ብለዋል::

የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፥ “አሁን የተመዘገበው ድል በእልህ አስጨራሽ መሰዋእትነት የተገኘ በመሆኑ፤ የወጣቱ እና የህዝቡ እንድነት መጠናከር አለበት:: የፖለቲካ ፓርቲዎችም የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ አንድነታቸው መጠናከር ይኖርበታል:: በመሆኑም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነትም በውይይት ሊፈታ ይገባዋል” ብለዋል::

የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም፥” የህዝብን ችግር መቅረፍ የሚቻለው አንድነትን በማጠናከር ነው:: መዋሃድ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ፤ መዋሃድ የማችሉ ደግሞ እርስ በእርስ በመተባበር የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ወሳኝ ነው:: መንግስት የህግ የበላይነትን በሚያስከብርበት ጊዜ እኛም የሚጠበቅብንን ሀላፊነት እንወጣለን” ሲሉ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.