አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ! (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

መሬትን እንደ ሰፌድ ስንዴ አገላብጦ እሚያርስ ትርፍ አምራች ገበሬ ጉዛም ይባላል፡፡ ጉዛም ሲያርስ ተማረሻ ያመለጠችውን ዓረም በጅራፉ እንጨት ቆፍሮ ያወጣና ይጥላታል፡፡ በዚህ የጠራ አስተራረስ ምክንያት ጉዛም ያረሰው መረሬ አፈር ከአረም ይጸዳና የኦባንግ ሜቶን መላጣ ይመስላል፡፡ ሰነፍ አራሽ ግን እንኳን ያመለጠን አረም ሊነቅል ተማረሻ ምላስ የገባውንም እንደ ጅል ተኳሽ ይስትና አለባብሶት ይሄዳል፡፡ በዚህ አለባብሶ የማረስ ምክንያትም ሰነፍ ያረሰው በሬዎች ከዳር ደርሰው ሳይመለሱ አረሙ አፈሩን ፈንቅሎ ብቅ ይልና እርሻው ጎንደርና ጎጃምን ስትሳደብ እንደ ጭራሮ የሚንጨበረረውን የሚሚ ስብሐቱን የተሸመተ ጠጉር መስሎ ቁጭ ይላል፡፡

በዚህ ሳምንት ከ”ቤተ-መንግስት” የተሰበሰቡት የድሮ ዘመን ተቃዋሚ የዚህ ዓመት ተደናባሪ ድርጅቶች መሪዎች ሰነፍ አራሾች ሆነው ሲልፈሰፈሱ ተስተውለዋል፡፡ ፍትህን ካስቀደመ አንድ ጎበዝ በቀር ሁሉም ከፍትህ መቃብር አረም እየዘሩ ማለፍን መርጠዋል፡፡ እነዚህ ዋልጌ አራሾች ከዓለም ተጠራርተው “ቤተ-መንግስት” እንዲገቡ ያበቋቸውን ሰማእታት እንደ ሰባኪያቸው ፓስተር ረስተዋል፡፡ እነዚህ ሰነፍ ገበሬዎች አሜሪካ፣ አውሮጳ፣ አውስትራሊያና አስመራ ቦርጫቸውን እየገፉ በድርጅቶቻቸው ስም ያስረሸኗቸውን፣ ያሰለቧቸውን፣ በኮረንቲ ያስጠበሷቸውን፣ ያሰደዷቸውንና ያስጠለፏቸውን ሰማእታት ችላ ብለዋል፡፡

እነዚህ አሙለጭላጭ አራሾች ቦሌን ከረገጡባት ደቂቃ ጀምሮ ጫማቸው በሰማእታት ሥጋ እንደሚራመድና ሳንባቸውም የሰማእታትን እስተንፋስ እንደሚተነፍስ መገንዘብ ተስኗቸዋል፡፡ ለእነዚህ አሙለጭላጭ አራሾች በወልቃይትና በራያ ለአርባ ሁለት አመታት የረገፈውና የተሰቃየው ሕዝብ ምንም አልመስል ብሏቸዋል፡፡ እነዚህ ሰነፍ አራሾች በጋምቤላ፣ በአዋሳና በኦጋዴን እንደ አባይ ፀሐይ ሸንኮራ የታጨዱትን ዜጎች የተጠቀሙባቸው ለፖለቲካ ፍጆታ እንጅ ለፍትህ እንዳልሆነ ግብራቸው ይነግራል፡፡

እነዚህ ዋልጌ አራሾች ዛሬ የአራት ኪሎን አቀበት የወጡት በአለፉት ሶስት ዓመታት በአምባ ጊዮርጊስ፣ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ባህርዳር፣ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ ደብረ-ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ማጀቴ፣ አምቦ፣ ነቀምቴ፣ ጊንጪ፣ ኮፈሌ፣ ሻሸመኔ፣ ኮንሶና ሌሎችም ቦታዎች የተረሸኑትን አጥንት መሰላል አድርገው መሆኑን እንደ ሰበሰባቸው ጆሮ-ጠቢ ያመኑ  አይመስልም፡፡ እነዚህ ምልግልግ የፖለቲካ አራሾች ወደ አዲሳባ የነዳቸው የወጣቶች ደም ጎርፍ ሳይሆን የሰበሰባቸው ፓስተር ብጽእና መስሏቸዋል፡፡ እነዚህ ከሀዲዎች ፓስተሩ ከወንበር የተቀመጠው አንድም በሕዝብ ቁጣ መዓበል በሰጉት፤ ሁለትም ቻይናንና ኢራንን ወሽሞ በአመንዝራ ፉንቃ ባበደው ወያኔ በቀኑት ምዕራባውያን መሆኑን ስተዋል፡፡ ፓስተሩ የወያኔ ወታደር፣ ሰላይና ካድሬ ሆኖ ተከታዮቻቸውን እንደ ውሻ ሲያሳድድ እንዳልኖረ ሁሉ እነሱ ተሰባኪ ፓስተሩ ሰባኪ ሆነው ሲማሩ ውለዋል፡፡

በዚህ ፓስተሩ አስተማሪ እነሱ ተማሪ ሆነው በዋሉበት የስልጠና ሂደትም ስለ” ስለምርጫና ስለ አገር ግንባታ” ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ፍትህን ግን ክንዱ እንደዛለ ሰነፍ ገበሬ አፈር እያለበሱ ሊቀብሯት ሞክረዋል፡፡ ታዲያ በፍትህ አዳጎ እሚጥሉ ፖለቲከኞች እንዴት ለሕዝብ ይጠቅማሉ ብሎ ማመን ይቻላል? “ሩዋንዳ ሚሊዮን ሕዝብ አልቆ የታሰሩት ጥቂቶች ናቸው” በሚል ሰንፋጭ ሰበብ ነፍሰ-ገዳዮች በገደሏቸው መቃብሮች እንቧለሌ እየጨፈሩ እንዲኖሩ የሚፈቅድ አሳይ መሲህ እንዴት ፍትህን ያሰፍናል ብሎ መጠበቅ ይቻላል? “መጀመርያ ፍትህ!” ሲል የጠየቀን ጎበዝ “ያንተም ቅድመ አያት ጡት ቆርጧል!” በሚመስል የሾርኒ ንግግርና የቅጥፈት ክስ በማሸማቀቅ በፍትህ አረም ለመጣል የሞከረ እባብ እንዴት ለፍትህ ይቆማል ብሎ መጠበቅ ይቻላል፡፡ “ስንቱን አስረን ስንቱን ልንተው!” በሚል ማጭበርበሪያ በሃያ ሰባት ዓመታት በተሰውት ዜጎችና ዛሬም ኩታቸውን ዘቅዝቀው በሚያለቅሱ እናቶች የሚቀልድ ጨካኝ እንዴት አገር ሊገነባ ይችላል? ሰማእታት የውክላና ውል ፈርመውላቸው ያለፉ ይመስል ይቅርታ ተቀባይ፣ ይቀታ ጠያቂና አስታራቂ በመሆን ፍትህን በእርቅ አረም አፍነው ሊገሉ በተሰባሰቡ የፖለቲካ ቁማርተኞች ሕዝብ ምን ተስፋ ይጥላል?

አረምን አፈር አልብሶ እንደሚያልፍ ሰነፍ ገበሬ በፍትህ አፈር እየጫኑ ከሚያልፉ ተሹለክላኪ እንሽላሊት ፖለቲከኞች የአገር ግንባታ ገድል ይጠበቃልን? የሰይጣን ተከታይ ወንበዴ ገዥዎችን በአካል ሲታገሉ የተሰው የድርጅት አባሎቻቸውን ሬሳ ረግጠው ከገዳዮቻቸው አንሶላ መጋፈፍ ከጀመሩ በአሜሪካ፣ በአውሮጳና በአስመራ በምላሳቸው ሲታገሉ ከነበሩ ፖለቲከኞች ብሩህ ተስፋ ይጠበቃልን? እንደ ሾንኮራ ያሳጨዷቸውን ሰማእታት የከዱትን እነዚህን ዋልጌ ድርጅቶች ለመምረጥ እሚዳዳ እብድ ዜጋ ይኖር ይሆን? በድርጅቱ ሥም የተገድለንና የተሰቃዬን ከድቶ ከገዳዩና ካሰቃዩ የሚወባራን የፖለቲካ ነጋዴ ዳግም አምኖ እሚከተል ዘልዛላ ይኖር ይሆን? በአላማ ጽናት ከጎኑ የተሰውትን ክዶ ጓዶቹን ከሰዋቸው ነፍሰ-ገዳይ አንሶላ እሚጋፈፍ ከሀዲ ፖለቲከኛን የሚከተል ማገናዘብ የተሳነው ወገን ይኖር ይሆን?

የተደናባሪ ድርጅት መሪዎች ሆይ! ድርጅት እንደ ዳስ ባራት ባላ እያቆማችሁ መታገል ከጀመራችሁበት ጀምሮ በድርጅታችሁ ሥም ሚሊዮኖች እንደ ሰንበሌጥ ታጭደዋል፣ አካል ጎደሎና ኑሮ አልባ ሆነዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት እናቶች ኩታቸውን ዘቅዝቀው ያለቁትን ልጆቻቸውን፤ ባሎቻቸውና ወንድሞቻቸውን እያነሱ ሚሿቸውን መደርደር ቀጥለዋል፡፡ እናንተ ግን ይኸንን ሰቆቃ ጆሮ ዳባ በማለት እንደ ሚዜ ልብሳችሁን አሳምራችሁ እንደ ሙሽራ ከመድረክ ከተጎለቱት የነፍሰ-ገዳይ ሎሌዎች መሽኮርመሙን ቀጥላችኋል፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ስታነሷቸው የኖራችሁትን ሙታንን ረስታችሁ ከገዳዮቻቸው ጫማ ሥር ወድቃችኋል፡፡ ከሙታን መቃብር ቆማችሁና ፍትህን አረም አልብሳችሁ ቀልባችሁ ወደ ሥልጣን መሸጋገሪያው ምርጫ ሆኗል፡፡

የተደናባሪ ድርጅት መሪዎች ሆይ! እናንተ ከቤተ-መንግስት አዳራሽ በፍትህ አረም ስትጭኑ ስንቱ ኢሐዴግ በሚባል የሰይጣን ተከታዮች ስብስብ ከኑሮው የተፈናቀለ “የፍትህ ያለህ!” ሲል እጁን ወደ ሰማይ ይዘረጋል፡፡ እናንተ ስንቱን ተስካር አውጪ ላደረገው ኢሕአዴግ ስትሰግዱ የእናቶች ሐዘን “ለተረሸኑት ፍትሕ!” እያለ ይጮኻል! እናንተ ስለምርጫና ስልጣን ስትወሸክቱ ለቤት መስሪያ ግኒደር ከሚቆፍራቸው ያልታወቁ መቃብሮች የሚወጣው የሰማእት አጽም “የፍትህ ያለህ!” እያለ ወደ ሰማይ ይፈናጠራል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፍትህ ጩኸት ቢበዛም የእናንተ ልብ እንደ አርዮስ ደንድኖ በፍትህ አረምን መጫኑን ቀጥሏል፡፡

በፍትህ አረም ተካይ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሆይ! የእናንተስ እግር መቃብር እየገባ ነው፡፡ በእናንተ ምክንያት መከራው የበዛው ወጣቱና መጪው ትውልድ ግን አሳዛኝ ነው፡፡ አለባብሰው የሚያርሱ ልፍስፍስ አራሾች ለአራሚዎች አበሳን ያበዛሉ፡፡ በፍትህ አረም የሚጭኑ ልምጥምጥ የፖለቲካ ነጋዴዎችም የሕዝብን መከራ ያራዝማሉ፡፡ ፍትህን አረም ተጭኖት እርቅ አይፀድቅም፡፡ ፍትህን አረም ተጭኖት ሰላም አይሰፍንም፡፡ ፍትህን አረም ተጭኖት የስልጣን  ወንበርም አይቆምም፡፡ ፍትህን የረገጠን ወንበር ሕዝብና መለኮት እንደ ቁልቢጥ መድፋታቸው አይቀርም፡፡ የወንበር መደፋት ስንሽከረከርበት የኖርነው አዙሪት ቀለበት ነው፡፡ የአዙሪት ቀለበቱን ዳግም እንደ እንዝርት ለማሽከርከር እናንተ የፖለቲካ ደላላዎች ከነፍሰ-ገዳዮች ጋር እየተዳራችሁ ነው፡፡ ይህንን መረን የለቀቀ ድሪያ የተመለከተች እናት ኢትዮጵያም “አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱን!” እየቆዘመች ነው፡፡

 

የሞተን አትርሳ የወደቀን አንሳ!  አመሰግናለሁ፡፡

ተመሳሳይ ጽሑፎች፡-

ፍትህ የሌለው እርቅ ሥራ እንደሌለው እምነት የሞተ ነው!

http://quatero.net/amharic1/archives/30170

የንፁሓን ደም ይጮሃል!    https://www.satenaw.com/amharic/archives/52522

 

No One Has the Right to Forgive on Behalf of the Dead Souls!

https://ecadforum.com/2018/06/28/no-one-has-the-right-to-forgive-on-behalf-of-the-dead-souls/

We  Shall  never  Feed  or Trade  on  Dead  Souls!

https://www.zehabesha.com/we-shall-never-feed-or-trade-on-dead-souls-by-belayneh-abate/

We Shall  Never Forget the Dead Souls to Lick Ice Cream of Political Advantages from Blood Stained Spoons

We Shall Never Forget the Dead Souls to Lick Ice Cream of Political Advantages from Blood Stained Spoons

 

ህዳር ሃያ ሶስት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.