አቶ ያሬድ ዘሪሁንና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ያፈሩት ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ለፍርድ ቤት በዝርዝር ቀረበ

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራታቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገለፀ፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው አቶ ያሬድ በስማቸው የተመዘገቡ ቤቶችና ድርጅቶች እንዳላቸውና ለሚስታቸው አባት ውክልና ሰጥተው እያሰሩ መሆኑን ፖሊስ ተናግሯል፡፡ እንዲሁም በሚስታቸው እናት ስም የተመዘገበ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ማከራየት ንግድና በሚስታቸው ወ/ሮ አዳነች ተሰማ ስም የተመዘገቡ የተለያዩ ቤቶች መኖራቸውንም አስረድቷል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማም በአቶ ያሬድና በሚስታቸው ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ቤት መኖሩን ጥቆማ እንደደረሰው፣ የተናገረው ፖሊስ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የተለያዩ ንብረቶች በባለቤታቸውና በባለቤታቸው እናት ስም ተመዝግበው እንደሚገኙ ጥቆማ እንደደረሰውና ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም በዱከም ከተማ በሚስታቸውና በእሳቸው ስም ያለ ንብረት ማስገመት እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

አቶ ያሬድ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ላይ ግድያ በመፈፀም መጠርጠራቸውንም ጋዜጣው አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን በቀጣይ ለማየት ለታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተያያዘ ዜና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሽብር ከተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉቦ ይቀበሉ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ፖሊስ ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው አቶ ተስፋዬ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ የድርጅቱ አባላት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ቤት ውስጥ በድብቅ በማስቀመጥ በሽብርተኝነት ያስፈርጇቸው ነበር፡፡ ግለሰቦች ቤት የኦነግን ባንዲራ በማስቀመጥ እንዲታሰሩ ከማድረግም ባለፈ፣ በማስፈራራት ከ200 ሺሕ ዶላር በላይና ስድስት ሚሊዮን ብር መቀበላቸውንም ፖሊስ አስረድቷል፡፡ ግለሰቦችን ሐሰተኛ ደብዳቤ በመጻፍ እያስፈራሩ ያሰቃዩ እንደነበር፣ የገለፀው ፖሊስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ጨምሮም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በተለያዩ አካባቢዎች ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማፍራታቸውን፣ በንግድ ባንኮችም ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀመጣቸውንና በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ገልጿል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.