በደብረማርቆስ ተማሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው አደጋ በመቃወም ሰልፍ ወጡ

“በተለያዩ አከባቢዎች በሚደርሰው አደጋ ሀዘናችንን እንገልፃለን በሚል ለጊዜው መማር ማስተማሩ ቆሟል” የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ታደሰ ጤናው

• ዛሬ ተማሪዎች ምግባቸውን በስርዓት ተመግበዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2011 ዓ.ም (አብመድ) የደብረ ማርቆስ ዮኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ዲን አቶ ታደሰ ጤናው የዩኒቨርሲቲውን ወቅታዊ ሁኔታ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት ሀዘናቸውን መግለፅ መብታቸው ቢሆንም ይህንን ለማድረግ ህጋዊ አካሄድ አልጠየቁም። ሀዘናቸውን ለመግለፅ በምግብ አዳራሹ የራሳቸውን ምግብ መድፋት ፣ እና የሌሎች አብዛኛው ተማሪ ሰላም የማደፍረስ ጅማሬ ታይቶ ነበር። ሌሎች ተማሪዎችም ፀጥታችን ደፈረሰ እና ምግብ ለምን በየጊዜው ይደፋብናል በሚል ያለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።

ቅዳሜ የጀመረውን ችግር ለመፍታት መምህራን ፣ እና የደብረ ማርቆስ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሐይማኖት አባቶች ሁለቱ ቡድኖችን በተናጠል እያወያየን ነው ። ነገ ከፌዴራል ከሚመጡ አካላት ጋር በመሆን የጋራ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።
‹‹በተለያዩ አከባቢዎች በሚደርሰው አደጋ ሀዘናችንን እንገልፃለን በሚል ለጊዜው መማር ማስተማሩ ቆሟል›› ብለዋል፡፡

በሀገር ሽማግሌዎች እና በሐይማኖት አባቶች ጥረት ዛሬ ከእራት ስዓት ጀምሮ ሁሉም ተማሪዎች ምግባቸውን በስርዓት ተመግበዋል ። የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ለዚህ ለውጥ ግንባር ፈጥረው ውጤቶች በታዮ ማግስት ተማሪዎች ልዮነትን አጥብበው ለውጡን ሊደግፉ ይገባል በማለት አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ አከባቢ የሀገር ሽማግሌ አቶ እስራኤል እምባቆም አብመድ እንደተናገሩት ተማሪዎች የተፈጠረውን ችግር በሰከነ መንገድ እንዲያዮት ተመካክረናል ነው ያሉት ።

‹‹ሀዘናችንን መግለፅ ካልቻልን እንሂዳለን›› ሲሉም ከሀገራችሁ ወጥታችሁ ወዲት ትሂዳላችሁ እዚህ ያለው ህግ እዚያም ያለው ነው ዓላማችሁን እንድታሳኩ እኛ ከእናንተ ጎን ነን ብለን ዛሬ እራት አብረን በልተናል ነው ያሉት። ነገ ከፌዴራል የሚመጡ አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታትም ቁርጠኞች ነን ብለዋል አቶ እስራኤል ።

የደብረ ማርቆስ አድማ ብተና ኃላፊ ኮማንደር አንማው ካሴ በዮኒቨርሲቲው የተፈጠረው ችግር የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የፀጥታ ኃይሉ ሰላማዊ አማራጭ እንዲያገኝ ተማሪዎችን የማረጋጋት ስራ ሲሰራ ነበር ።

በተፈጠረው ችግር 6 ተማሪዎች ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒል እየታከሙ ነው ፤ ሶስቱ ደግሞ ታክመው ተሽሏቸው ተመልሰዋል ። ንብረት ላይ የደረሰ ችግር የለም ብለዋል ። እኛም ግቢው ከስዓት ጀምሮ ወደ ፀጥታ እንደተመለሰ እና እራት ሲበሉ ተመልክተናል ።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ ከደብረ ማርቆስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.