ስልጣን  እና ኢትዮጵያ  ሃገራችን፤ (ከኃይሉ በላይ)

1ኛ) መግቢያ፤

ቀደም ብሎ በዘውዱ ዘመን በሃገሪቱ ከነበረው ስልጣን፣ ከዚህ የሚመነጨውና የሚንጠፈጠፈው ጥቅም አብዛኛው በአንድ ቋንቋ ተናጋሪወች ብቻ ተይዟል ተብሎ የቅሬታ ምክንያት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ መሪወች ጥቅምና ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ከህግና ስርዓት በተጨማሪ ሃይልና ጉልበትን፣ የቋንቋቸውን ተመሳሳይነት፣ ብዛታቸውን ወይም ቁጥራቸውን፣ ዝምድናቸውን፣ አማችና ጋብቻን እንደ ስልጣንና ጥቅም ማስቀጠያ መሳርያወች ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ በብሄርና ጥቅም ጉዳይ ወታደራዊውን መንግስት ብንተወው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሁኔታው የከፋ እንደነበር ለመረዳት ቀላል ነው፡፡

አንዱን ቀን ሲጥለው ሌሎች እየቀናቸው መሪወቻችን ቢፈራረቁም ዋና ተዋናይ የነበሩ ጥቂት መሪወችን፣ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ለዘለቄታው የተጠቀመ፣ ጎሳ ወይም ቡድን የለም፡፡  የንጉሱ አፄ ኃይለ ስላሴና ቤተ-ሰቦቻቸው፣ የመኳንንቱና የመሳፍነቱ መጨረሻ፣ በገዥ መደብነት የተፈረጀው አማርኛ ተናጋሪው ሁሉ አላተረፉም፡፡ ዘር አልባወች ደርግና ኢሰፓወችም አልተጠቀሙም፡፡ በቅርቡም ቢሆን ከትግራይ በረሃ እጅ ለእጅ ተያይዘው መሸመቃቸው እንጅ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው በተለያዩ ዘዴወች ስልጣንና ጥቅምን ለብቻቸው መቀራመታቸው፣ ተቀራምተው መባጀታቸው ለማንም በተለይ ለራሳቸውም አልጠቀመም፡፡ የሰሞኑ ውርደት፣ መሸማቀቅ፣ በህዝብ፣ በሃገር፣ በማህበረሰብ በተለይ በቤተሰብ፣ በወለድናቸውና ከአቻወቻቸው ጋር ትምህርት ቤት በሚማሩ ጨቅላ ልጆች ፊት አንገት መድፋትን የሚልቅ ኪሳራ ያለ አይመስለኝም፡፡ በህይወት መስዋትነት፣ በደምና ባጥንት የተገኘን አጋጣሚ በመጨረሻ በዚህ መልኩ ማባከን ትልቅ ከኪሳራም በላይ የሆነ ኪሳራ ነው፡፡

ሀቁ ይህ ቢሆንም አሁንም የስልጣን ሽሚያው እንደቀጠለ ነው፡፡ የሽሚያ ዘዴው ግልብና ቀላል በሆነው በማንነትና በቡድን ስሜት እንደታጀበ ነው፡፡ አሁንም ገና ሲጀመር፣ ካቢኒ ሲቋቋም በካቢኒው ውስጥ ያሉ የቋንቋቸውን ተወካዮች የሚቆጥሩ ሞልተዋል፣ የእከሌ ብሄር ወሳኝ ከሆኑ የስልጣን ድርሻወች ተገሏል ይባላል፡፡ በየትኛውም መንገድ የበላይነትንና ስልጣንን ለራሳቸው ለብሄራቸው ብቻ የሚፈልጉና የሚያልሙ ዛሬም ብዙ ናቸው፡፡ እንመልከታቸው፡፡

2ኛ) የአማራ ብሄርተኛ ሃይሎች፤

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ የኢህአዴግን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ፖሊሲ በመተቸት ለአማራ ህዝብ አማራጫቸውን ሲያቀርቡ፣ ከብአዴን የሚለዩበትን አመለካከት በመግለፅ ተከታዮቻቸውን ለማሳመን ሲሰሩ አልታዘብንም፡፡  ብዙ አወንታዊ ለውጦችን ባየንበት የዶ/ር አብይ የምኒስትሮች ሹመት ቀላሏን የቋንቋ ማንነት ካርድ መዘው ሹመቱን ተችተዋል፣ አውግዘዋል፡፡

እንደሳቸው አማርኛ ተናጋሪወች ቢሆኑም፣ በድርጅታቸው በአዴፓ-ኢህአዴግ ፕሮግራም፣ አሰራር፣ አምነው አባል ከሆኑ በኋላ፣ በብዙ ውጣ ውረዶች አልፈው፣ የተመዘገበው አወንታዊ ለውጥ ባለድርሻ ነን ብለው ለሚያምኑት አዴፓወች ጥሪ አድርገዋል፤ ጥሪው በዶ/ር አብይ ካቢኒ የተሾሙ አማርኛ ተናጋሪ ምኒስትሮች በተቃውሞ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሚጠይቅ ነበር፡፡  በአዴፓ የለውጡ ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት የዶ/ር አምባቸው ቀጣይ የስልጣን ዕጣ ፈንታ ያሳሰበው፣ የተነበየው፣ ከውስጥ አዋቂ አገኘሁት ብሎ ቀድሞ የፃፈው ብዙ ነበር፡፡ ነገሩ ስር የሰደደ በሽታ በመሆኑ  በዲሞክራሲ ምሳሌ በሆኑ አሜሪካውያን መካከል በሚኖሩ የሃገር ልጆችም ሰሞኑን ለውይይት ላቀኑት ለአዴፓ አመራሮች ከተነሱት ጥያቄወች የኦዴፓና የአዴፓ የስልጣን ክፍፍልና ስምምነትን የተመለከቱ ጥያቄወች በእየስቴቱ ተነስተዋል፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በግሌ እንደ ኢህአዴግ የምጠላው፣ ተስፋ የቆረጥኩበት ድርጅት አልነበረም፡፡ ግን ገልቱ ተቃዋሚ አይደለሁም፡፡ በዋናነት ኦዴፓና አዴፓወች ከተሳተፉበት ለውጥም በላይ ጎበዝ ያዝልቅላቸውና ኢህአዲጎች ከነበሩበት ችግር በሚገባ የተማሩ ይመስላል፡፡ እንደውም የነበረው ባህል፣ የድሮው ኢህአዴግ ዋና ችግር አሁን አሁን የተንፀባረቀው ኢህአዴግን ሲያብጠለጥሉ በነበሩት ይመስላል፡፡ ኢህአዴጎች እነዚህና መሰል ፈተናወችን በትክክለኛ ሃሰብ በመመከት እያለፉ፣ በስራቸው ላይ ብቻ ቀጥለዋል፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ቀዳዳ አላስተዋልንም፡፡ ሌሎች የስልጣን ክፍፍሉን፣ የሚንስትሮችን ሹመት በቁጥርና በሃላፊነቱ ዓይነት እየተነተኑ ሲደክሙ፣ ብአዴኖች ግን እንደ ጥንቱ ተወክለናል፣ ድርሻችንን ይዘናል፣ በቂ ነው፣ የምንፈልጋቸውን ሃላፊቶች ይዘናል አላሉም፡፡ ከላይ በሃገረ አሜሪካ  ለቀረበው ጥያቄ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልስ ትክክለኛው መርህ ነበር፡፡ ጉዳዩ የስልጣን ክፍፍልና ቅርምት እንዳልነበረና እንዳልሆነ በማያሻማ መንገድ ገልፀዋል፡፡ በእውነት ከቻለ ማንም ሊሞክረው የሚገባ የሸክምና የሃላፊነት ክፍፍል ነው፡፡

የጠቅላይ ምኒስትሩ ካቢኒም ሆነ ሌሎች አዳዲስ ሹመቶች ማብጠልጠልና መቃወም ግዴታ ካልሆነ ከድርጅቱ ከኢህአዴግ ውጭም እጅግ አይነ ሰፊነት የተሞላባቸው ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ አቅምና ችሎታ፣ የህዝብና የሃገር አመኔታ ያላቸውን ግለሰቦች ወደ ስልጣን ያወጣ፣ በሃገራቸው ውስጥ በኢህአዴግ ተጠርንፈው የተገለሉና፣ በድርጅት ጡንቻቸው አቅመ ቢስ የሆኑትን የአጋር ድርጅቶችን አባሎች ያቀፈና ያሳተፈ ነው፡፡ ከቡድንና የቋንቋ አረንቋ ወጥቶ ብሄራዊና ሰብአዊ በሆነው የፆታ ተዋፅኦ የተዋጀ ነው፡፡ የለውጡ አስተሳሰብ ከጅምሩ በቀላሉ ወደ ደቡብ ህዝቦች፣ ሱማሌና አፋር ተዛምቷል፡፡ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም በኢህአዲጎች በኩል ተጨባጭ ለውጥ፣ ለወደፊቱም ተስፍ ይታያል የምለው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

አረንቋውን በትክክል የሚያውቁት፣ በአረንቋው ተውጠው የነበሩት ኢህአዴጎች፤ አዴፓም፣ ኦዴፓም ቢሆኑ ተገቢ ነው፡፡ ዳር የነበሩት ይህንን ለመረዳት አለመቻላቸው፣ የተጀመሩ በጎ እርምጃወችን ለመደገፍ፣ የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት አለመቻላቸው፣ በዚህም በዚያም የሚሰነዘሩ ትችቶች፣ የሚፈጠሩ እክሎችና የሚጠመዱ ወጥመዶች ግን የሚያሳዝኑ ናቸው፡፡ በጭራሽ በአይናችን ስር እያየናቸው ላሉ ለውጦች የሚመጥኑ አይደለም፡፡ አንዳንዶች ከላይ እንዳነሳናቸው በግልፅ የሚደረጉ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትና አክቲቪስትነት የተሞሸሩትንም ለመታዘብ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡

3ኛ) አክቲቪስት ጀዋርና የኦሮሞ ብሄርተኞች፤

አክቲቪስት ጀዋር ሞሃመድን ጨምሮ ታወቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የተከሰተውን ለውጥ ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲቃኙ፣ ለለውጡ የበለጠውን መስዋትነት የከፈለው የኦሮሞ ህዝብ፣ በተለይ ቄሮ አብይ ሚና መጫወቱን በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ ለሃያ ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነትን ድል ባለ ስነ-ስርዓት እያከበሩ፣ ሃገርን ነፃ አውጥተናል ሲሉ ከጀመሩት፣ ከቀደሙት ነፃ አውጭወቻችን ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም ሁለቱም ፖለቲከኞች ትክክል ናቸው፡፡

የነበረውን የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ ለመቀየር ግንባር ቀደም ተሳታፊ፣ ለችግሩ ፍቱን መድሃኒት የነበሩት የኦሮሞ ህዝብ፣ በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች፣- ቄሮወች ነበሩ፡፡ ለአንድ ለውጥ ዕውን መሆን፣ ለውጥ ፈላጊው፣ አሸናፊው ብቻ ሳይሆን ጥቂትም ብትሆን ተሸናፊውም ድርሻ እንዳለው ከተረዳን በግንባር ቀደሙ ላይም መስማማት ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር የኦሮሞ ዋጣቶች በዋናነት፣ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም እንዳቅሙ በተሳተፈበት ሁኔታ የተገኘው ለውጥ ወዴት ያመረናል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ፀሎቴ ቀጣይ በተለይ የኦሮሞና አጠቃላይ የሃገሪቱ ፖለቲከኞች፣ መሪወችና ልሂቃን ዕጣ ፈንታ ከነበረው ታሪካችን የተለየ እንዲሆን ነው፡፡ ፀሎቴ የሚሰምረው ሁላችንም ከነበረው ከተማርን ብቻ ይመስለኛል፡፡

በዚህ ረገድ በግልፅ ባያስቀምጧቸውም ከላይ በስም የገለፅኳቸውን ጨምሮ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዝማሚያ የሚተች ሁኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የኦሮሞ ህዝብም በተጨባጭ የሚጠቀመው የለውጡ መንገድና መዳረሻው ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ለሁሉም በሚተርፍ መልኩ በእየወቅቱ ከነበረበት ሂደት ወደ ተሻለው ሂደት ሲሸጋገር ቢሆንም ለዚህ ሁሉን አቀፍ ለሆነ የጋራ ጉዞ ሲሰሩ አልታዘብኩም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሌሎች አቋሞች ጨምሮ፣ በለውጡ መሪወችና በጅምሩ ላይ በእየወቅቱ የሚያደርጉት ጫና ልክና መጠን ያለው፣ በሃላፊነት መንፈስ የሚደረጉት አይመስልም፡፡ ሁሉም የኦሮሞ ነን የሚሉ ፓርቲወች፣ጥናት ሳያደርጉ፣ ሳይወያዩ፣ በተለይ ማህበራዊ የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ ሃሳብ ሳይጨምሩ ድንገት ተሰባስበው፣ ወቅታዊ ፋይዳ በሌለው የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያንፀባረቁት የጋራ አቋም ለእዚህ አንዱ ማሳያ ነበር፡፡  ለህዝቦች አንድ ነገር ጠብ ባይልም፣ በአማራ ህዝብ ፣ በትግራይ ህዝብ ስም ጥቂቶች የስልጣንና የጥቅም ፈረስ መጋለብ ችለው ስለነበር በተመሳሳይ መንገድ ፈረሱን የመኮልኮል አዝማሚያና ሙከራ ይመስለኛል፡፡

በመላ ሃገሪቱ ተመሳሳይ ችግሮች ቢኖሩም በኦሮምያና በቤ/ጉምዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ከተከሰተው ከፍተኛ ሰባዊ ቀውስ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡  በተደራጁ ታጣቂወች በተወሰደ እርምጃ የሁለቱም ክልል የአስተዳደርና የፀጥታ ሃይሎች ሂወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቅርቡ በታጠቁ ሃይሎች በኦሮምያ የፖሊስ አባላት ላይ ለደረሰው አሰቃቂ ግድያ በክልሉ የነበረው ግብረ መልስ በተለያዩ ከተሞች በተደረጉ ሰላማዊ  ሰልፎች የታጀበ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በተመሳሳይ የቤ/ጉምዝ ክልል የአስተዳደር አካላት ላይ ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመ ቢሆንም ተ በድርጊቱ ማግስት በኦሮምያ የተደረጉት ሰልፎች የቅርቡን ችግር ብቻ የተመለከቱ፣ የችግሮች ብቸኛ ገፈት ቀማሽ ኦሮሞ እና ለተከሰተው ችግርም ከኦሮሞ ተነጥለው ብቻቸውን ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን የሚያውጁ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

የታዘብናቸው አዝማሚያወች የብዙሃኑን ተሳትፎና ጥረት፣ የጋራ ግንዛቤወችንና መፍትሄወችን የሚፈልጉ የጋራ ችግሮችን፣  ለሌላ ክልልና ህዝብ ብቻ ከመግፋት በተጨማሪ ለችግሩ ራሱን የኦሮምያ ክልልንና የፌዴራል መንግስቱን የሚከሱ፣ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥሩ ነበሩ፡፡ “ ኦሮሞ የታገለው የኦሮሞን መብት ለማስጠበቅ እንጅ ኦሮሞወችን ስልጣን ላይ ለማውጣት አይደለም፤” የሚል መፈክር በአንዱ ሰልፍ ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ ምን ጊዜው፣ በዚህ ሁኔታ ለዚህ መድረስ ተቻለ ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ በኦሮምያ የከተሙ ፖለቲከኞች ካለባቸው የህዝቡንና የደጋፊወቻቸውን ስሜት ካሉ ለውጦች፣ ወቅታዊ ሁኔታወች ጋር እያስተዋሉ የመምራት ሃላፊነት ባሻገር፣ በኦሮምያ ወጣቶች የነበረውን ከፍተኛ ስሜት እንደነበረ ይዘው ለፖለቲካ ጨዋታው በደቦ የመጠቀም ፍላጎት ይታያል፡፡ ኦቦ ለማ ወደ ፎረም የገቡት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

“ፖለቲከኛ አይደለሁም፣ አክቲቪስት ነኝ፤” የሚለው ጀዋር ሞሃመድ የወቅቱ ለውጥ የደረሰበትን ደረጃ ለኤል.ቲቪ. ጋዜጠኛ ሲገልፅ አዳምጫለሁ፡፡ “ከእንግዲህ በአፍሪካና በኢትዮጵያ የሚፈጠር ሃይል ሳይሆን የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታትም ቢመጡ የኦሮሞን ህዝብ ካለፍቃዱ ሊያስተዳድሩት አይችሉም፣ በዚህ ወቅት የደረስነበት ደረጃ ይህ ነው፣ ” የሚል መልዕክት ነበረው፡፡ ከዲሞክራሲ ፈጣሪወች፣ በብዙ ሂደቶች ለዘመናት ካጎለበቱት የተሻለ ስርዓትና መንግስት በላይ ከየት አንደሚመጣ አናውቅም፡፡ ነገሩ የተገለጠው ተነጥሎ በኦሮምያ ብቻ ተደረሰ የተባለበትን ደረጃ ነው፤ አንባቢው መንፈሱን መረዳት ይችላል፡፡ ከለውጡ በኋላ ወደሃገሪቱ የገባው ጃዋር በመላ ኦሮምያ ተዘዋውሮ ደማቅ የሆኑ አቀባበሎች ሲደረጉለት፣ አቀባበሎች በእየአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እየሆኑ፣ የዜጎች ህይወት ቢጠፋም ስህተቶች የተተቹበት፣ የታረሙበት በችግሩ ጊዜ የነበሩ የወጣቶቹ ስሜቶች እንዲለዝቡ የተደረገባቸው አልነበሩም፡፡  ለሳቸው የሚሰለፈው ወጣት እንጅ፣ የደመቀ አቀባበል እንጅ ስነ-ምግባርና ሞራል ቦታ ስለሌላቸው በመጨረሻ ፍቼ ላይ በተደረገላቸው አቀባበል ብሄርና ፖለቲካ አፈር ገብተው በይቅርታ የተፈታው እያንቧለለ ኦሮሞ ስለሆንኩኝ ነው የታሰርኩ ብሎ መድረክ አግኝቷል፡፡  እያንቧለለን ብዙ የአካባቢው ወጣቶች በጥንቁልናና የማታለል ስራው ሃብት አፍርቶ ተከብሮ ያውቁት ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዚህ ስራው ዘብጥያ መውረዱንም አይስቱትም፤ ስለዚህ የበለጠ የሚማሩት ከሞራልና ከስነ-ምግባር በታች የሆነውን ስብዕናውን በማንነቱ ለመሸፈን ያደረገውን ሙከራና ስልቱን ይመስለኛል፡፡

አካባቢያቸውን፣ ህዝባቸውን ነጥለው ወርቅ ብለው  የጀመሩትን መጨረሻ ብናውቅም የጀግኖችን ሃገር የአምቦን ምድር ለመርገጥ አክቲቪስቱ ጫማውን ማውለቅ ነበረበት፡፡ ጀዋር በአማራ ክልል ባደረገው ጉብኝት ስለ ሃገሪቱ ፖለቲካ፣ በክልሎቻችን መካከል ስላሉ ቅራኔወች፣ ስለህገመንግስቱ አቅጣጫወችን አስቀምጧል፡፡ አክቲቪስቱና የሚዲያው ባለሙያ ወደ ትግራይ ሊያደርገው የነበረውን ጉዞ የሰረዘው ህወሃት ጌታቸው አሰፋን የድርጅቱ አመራር አድርጎ በመምረጡ የአቋም ለውጥ አድርጎ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የዶር አብይ መንግስት ጌታቸው አሰፋ ላይ እርምጃ ካልወሰደ እንደበፊቱ የአመፃ ነጋሪት እንደሚጎስም፣ ጠቅላይ ምኒስትሩንም የሚያብጠለጥል ንግግር ተናግረዋልም ይባላል፡፡

ሁላችንም አቋሞች፣ ፍላጎቶች ይኖሩናል ነገር ግን በተለይ ጀዋር ሞሃመድ ብዙ ኢ-መደበኛ የሆነ አድማጭና ተከታይ አፍርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚዲያ፣ የሰባዊ መብትና የፀረ-አገዛዝ አክቲቪስት ነኝ እያለ በዚህ መልኩ በሁሉም ነገሮች ላይ፣ በቅፅበት አቋሞቹን ፍላጎቶቹን ለማወጅ መቸኮል አልነበረበትም፡፡

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ደፋ ቀና ብለው ለውጡን ለጀመሩት ፖለቲከኞች፣ በህግና በስርዓት በቤተ መንግስት ለተሾሙት፣ በእየክልሎች ላሉት መሪወች ከተወሰነ ጊዜ ጋር የማይነኩ ሃላፊነቶችን በትዕግስት ሰተው ሳይፈትኑ፣ በነበረው የአመፃ ዘመን ላይ ተቸክሎ፣ ከዚያ በኋላ በህግና በስርዓት ውስጥ ለታዩ አወንታዊ ለውጦች ምንም እውቅና ሳይሰጡ፣ በእኛ ሃገር ባይሆን አክቲቪስት ሳይሆን ፖለቲከኛ፣ የህዝብና የሃገር ተቆርቋሪ መምሰልም ባልተቻለ ነበር፡፡ በህግና ስርዓት የተሰጠ ስልጣን፣ በተመሳሳይ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል ባለቤት የሆነውን መንግስት መከተል፤ ተገቢውን ማወደስ፣ ችግሮችን መጀመርያ በማናውቀው በሰከነ፣ በሰለጠነ መንገድ በመተቸት፣ ከቻሉ የትም ቢሆን ሂደው በሀሳባቸው በመሞገት፣ አሁንም ከቻሉ ከየትም ቢሆን አንድ የተሻለ ሰው በማፍራት፣ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት ያለባቸው አክቲቪስቱ አቶ ጃዋር እንደነበረው በአቋሞችና ሰማይ በደረሱ ህልሞቻቸው የታጀበውን አካሄድ ሊመረምሩት ይገባል፡፡

የነበረን ባህሪንና ፍላጎትን በማስተካከል እንጅ የነበረውን ባህሪና ፍላጎት በአዲስ ስልት በማስቀጠል ለማንም፣ ለኦሮሞም ቢሆን ጠብ የሚል፣ የሚገኝ ተጨባጭ ለውጥ የለም፡፡ ይህ በሃሳቦች በማይፈተሽ፣ በማይጠየቅ የማንነት ሰልፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ በደጋፊወች ቁጥር ቢጥለቀለቅም፣ በብዙ ልዩነት አንደኛ መሆን ቢቻልም ለውጥ የለውም፡፡ ያው የነበረው ነው፡፡

መቼም አማራጮች ሲጠፉ በህዝብና በወጣቶች አመፃና አድማ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ ቢሆንም በተመሳሳይ በማንነት የጅምላና የደቦ አስተሳሰብ፣ በዚህ ሁኔታ በሚያዝ ስልጣንና የበላይነት ሃገርና ስርዓት እስከመጨረሻው እንደማይቀጥሉ ግልፅ ነው፡፡ ጀዋር ሙሃመድና ሌሎች ፖለቲከኞች የቄሮን ታሪካዊ ተጋድሎ የሚዘክሩት፣ በተጀመረው የለውጥና የተስፋ ጉዞ ውስጥም፣ የቄሮ የነበረው ከፍተኛ ስሜት እንዲቀጥል የሚደክሙት፣ በፈለጉት ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  የቅማንት ማህበረሰብ ተወካዮች በኦ.ኤም.ኤን ጣቢያ በተጀመረ ስርጭት ሃገርም፣ አማራና ቅማንትም እንደማያጭዱ፣ እንደማያተረፉ ግልፅ ነው፡፡ ወደፊት ከሚዘራውና ከቡቃያው፣ ከሁለቱ ኪሳራ እንደሌሎች ለማትረፍ አንዱን በማዳከም፣ የበላይነትን ለማስጠበቅ የታቀደ ከንቱ ህልም መመልከታችን አይቀርም፡፡

በተመሳሳይ የኦሮምያ ፓርቲወችን ፎረም ለመመስረት በአዳማ በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ ፕሮፌሰር መረራ የኦሮሞ የፓርቲወች ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀው በተለይ የቄሮ አንድነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አሁንም አስምረውበታል፡፡ በሁሉም ዘንድ ቄሮ ያለፈው ታሪኩና ገድሉ ብቻ ሳይሆን አንደነበረው፣ተጠርንፎ በሰበብ አስባቡ በጥቂቶች እየተነዳ እነዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ያለ ይመስላልል፡፡  በታሪካችን እንደነበረው ማለት ነው፤ ስለዚህ ውጤቱም ታሪክን መድገም እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡

ለነበረው ችግር አንድ ላይ፣ ባልተደራጀ መልኩ በቄሮ ስም የታገለውና መስዋዕት የሆነው የኦሮሞ ወጣት ወደፊት የተለያዩ ሃሳቦችን ፈትሾና መዝኖ፣ ማዶ ተሻግሮም ቢሆን በሩቁ ካለው ኢትዮጵያዊ ጋር ሊቆም የሚችልበት፣ የራሱን ሰጥቶ የሌላውን ሃሳብ፣ ቅሬታ የሚሰማበት ዕድል ሊኖር ይገባል፡፡ ሁኔታው ዕንቅፋት መሆን ሳይሆን የሁሉንም ሃቀኛ ቅንነት፣ ስራና ጥረትን፤ አዲስ ባህልን ይፈልጋል፡፡ ለሁሉም የሃገሪቱ አካባቢወችና ወጣቶች ተመሳሳይ ሲሆን ይህ ካልሆነ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በታጋይ ሰማዕታት ስም ህዝባቸውን በአንድ ሃሳብ ጠርንፈው፣ ፍላጎቶቻቸውን በሌሎች ላይ ጭነው ካለፉት፣ ዛሬ ከመሸባቸው ቀደምት ወንድሞቻችን አልተማርንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ውጤቱ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡

4ኛ) ኃይሌ ገ/ስላሴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤-እንደመደምደሚያ

ጦሰኛ የሆነውን ስልጣን በሃገራችን የሚፈልገው ሁሉም በእየዓይነቱ ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ ይማራል፡፡ ሃይሌ ገ/ስላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፣ እነ ገብረ እግዚአብሄር ገ/ማርያም፣ ደራርቱ ቱሉ አመራሮች ሲሆኑ ይበል ተብሎ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ገና ከጅምሩ ከኦሮምያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቃውሞወች ነበሩበት፡፡ በመጨረሻ የብዙ ክለቦች ባለቤት የሆነው የኦሮምያ ክልል የአትሌቲክስ ክለቦች በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ድምፅ ይስጡ ሲል በዚህ አሰራር የመወሰን ዕድል የማይኖራቸው ጋምቤላን፣ አፋርን የመሰሉ ታዳጊ ክልሎች ተቃዋሚወች እንደነበሩ ሰምተናል፡፡ ስለዚህ አጀንዳው ተጠንቶ በሚቀጥለው ገባኤ  ለውሳኔ እንዲቀርብ ተላለፈ፡፡

ከፍትሃዊ የተሳትፎ  ዕድል ጋር በሃሳብ፣ በአመራር ጥበብና በውጤት የበላይነት፣ በዚህ መሰረት ከሚገኝ የጋራ ስምምነት ስልጣንና ሃላፊነትን መፈለግ ተገቢ ቢሆንም ከዚህ ውጭ በየትኛውም መንገድ፣ በአንዱ ዘላለማዊ የበላይነት ስልጣንን ርስት ለማድረግ የሚደረግ ሩጫ ቢሳካም ለጥቂቶች እንጅ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ዓለም በቴሌቭዥን መስኮት ለማየት የሚጓጓለትን፣ እኔ እጁን መጨበጥ ህልሜ ብቻ ሁኖ የቀረውን፣ የብዙ ስኬቶች ተምሳሌት  አትሌት፣  ከፍተኛ ልምድ ያላት ፣ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በፌዴሬሽኑ ውስጥ አብራው እየሰራች፣ በሱልልታ በተዘጋጀ ውድድር ላይ የኦሮሞ ታዳጊ አትሌቶች እጁን ለመጨበጥ አደሙ፣ ተቃውሞ አደረጉ ሲባል እንዴት ማለት፣ መጠርጠር ደግ ነው፡፡ ካልነቃንበት ከስልጣንና የጥቅም ጥም ጋር ቡድንና ጎሳ የሚተውልን ቅንጣት ስፍራ እንደማይኖረው፣ በሁሉም እንደሚያሽመደምደን ከዚህ፣ ከነበረው የውሃ ዋና ፌዴሬሽን፣ ከቤተ-ዕምነቶቻችን …ወዘተ ልንረዳ ይገባል፡፡ ለዚህኛው ብቻ ልጠቀምበት ማለት አይቻልም፡፡

ሁላችንም መጨረሻችን የሚቀዳው ከማንነታችን ሳይሆን ከጅምሮቻችን፣ ከሃሳቦቻችን፣ ከፍላጎቶቻችንና ከድርጊቶቻችን መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አዙሪቱ እንዳይቀጥል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.