ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተፈናቀሉ አማራ ተማሪዎች በባህር ዳር ህዝብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው- አያሌው መንበር

በአጭር ቀናት ውስጥ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች መማር ካልቻሉ በአዴፓ ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ ፋኖዎች አሳውቀዋል።

===================

በኦሮሚያ ክልል ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰው ብሄር ተኮር ጥቃት ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎች በዋናነት ከአማራ ክልል የመጡ ከህዳር ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምረው ለስቃይ ሲደረጉ ሰንብተዋል።ለኦሮሚያና አማራ ክልሎች ብሎም ለትምህርት ሚኒስቴር መረጃው ቢደርሳቸውም ለችግሩ በቂ ትኩረት ባለማድረጋቸው ሊፈቱ አልቻለም።በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ለአስገድዶ መድፈር፣ለስወራ፣ለአካልና ስነልቦና ጥቃት ተጋልጠው ቆይተዋል።

ሶስት ተማሪዎች ተገድለዋል።ሶስት ተማሪዎች ተሰውረዋል (ተጠልፈዋል)።19 ተማሪዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።ህክምናም ተከልክለው ትናንት ባህር ዳር ከደረሱ በኋላ በአምቡላንስ ወደ ፈለገህይወት ሆስፒታል ተልከዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሁሉም አካል በቂ መረጃ አለው።

===============
ትናንትና ዛሬ ቁጥራቸው እስከ ሶስት ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ባህር ዳር ገብተዋል።ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ተማሪዎች ለችግር እንዳይጋለጡ በማሰብ ባህር ዳር ከመድረሳቸው በፊት የባህር ዳር አማራ ወጣቶችና የአማራ ተማሪዎች ህብረት ከመንግስት ጋር ቁጭ ብለው ለመወያየት ጥረት አድርገው ነበር።በዚህ በኩል ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገው ለመግባባት ሲሞከር የአማራ ክልል መንግስት ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ዝምታን መርጦ ነበር።የቡሌ ሆራ ችግር ከመከሰቱ በፊትም የአማራ ተማሪዎች ህብረት ደመቀና ገዱን ለማናገር ሞክረው እንደነበር ነገር ግን ቀና ምላሽ እንዳላገኙ ፅፈው ተመልክቻለው።አሁንም የተደገመው ይህ ነው።
ወጣቶቹ ግን ተስፋ ባለመቁሩጥ ጥያቄውን ገፉበት።ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ፣የታክስት መልዕክትና ሌሎችንም ለአመራሮች አድርገዋል።
አልተሳካም።

በመጨረሻም ራሳቸው ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ።በዚህ ወቅት መረጃው ወጥቶ ስለነበር በባህር ዳር ዙሪያ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እኛ ኦሮሞዎችን ተንከባክበን ነው የያዝን ለምን ነው የእኛ ተማሪዎች የሚባረሩት? ሂሳቡን የክልሉ መንግስት ላይ እናወራርዳለን የሚል አቋም ያንፀባርቃሉ።ባለትልቁ ጆሮ አዴፓ አሁንም ዝም አለ።እኛም ከመረጃው በከፊል አጋርተን ነበር።
በመጨረሻም ብልጡ አዴፓ ደህንነቱን መድቦ ተማሪዎቹ ባህር ዳር ከመግባታቸው በፊት ድባንቄ አካባቢ ላይ በፖሊስ አጅቦ የባህር ዳር ህዝብ እንዳይሰማ እና እንዳይተባበራቸው ለማድረግ ሲሞክር ወጣቶች ሰምተው ከፖሊስ ጋር ለመወያየት ሞክረው ተማሪዎች ወደ ከተማው ገቡ።

ከዚያም ለክልሉ አመራሮች የእነዚህን ተማሪዎች ችግር ካልፈታችሁ በኋላ ተጠያቂ ትሆናላችሁ የሚመ መልዕክት ይልካሉ።አዴፓም ህዝቡ እንደማይታገሰው ሲያውቅ ሶስት አመራሮችን ስድስት ሰዓት ገደማ ልኮ የተማሪ ተወካዮችንና ወጣቶችን አነጋገረ።

================≠==

በውይይቱ ወቅት አዴፓ ተማሪዎች አዴት መውጫ አካባቢ ቦታ ይሂዱ የሚል አማራጭ ቢያቀርብም ቦታው ለብዙ ነገር ስለማይመች በሚል ተማሪዎች የባህር ዳር ስታድየም ውስጥ ያለው አዳራሽ እንዲያርፉ ተስማምተዋል።ከዚህም ባለፈ አዴፓ ይህንን ጉዳይ ችላ የሚለው ከሆነ ውርድ ለራሱ ብለው ልከዋቸዋል።ከሰሞኑ አመራሮችና ተማሪዎች ፊት ለፊት ለውይይት ይገናኛሉ።መፍትሄው ምን ይሆናል? የሚለውን አብረን የምናየው ቢሆንም እኔ የሚታየኝ ግን ኦሮሚያ ክልል ባለፈው አመት ተማሪዎቹን ከጅጅጋ አስወጥቶ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መድቦ እንዳስተማረው አዴፓም እነዚህን ተማሪዎች በአማራ ክልል ውስጥ እንዲመደቡ ቢያደርግ መልካም ይመስለኛል።ለነገሩ አላደርግም ቢልም አይችልም።ምክንያቱም የሚቆረቆርልን መንግስት የለንም ብለው ተስፋ የቆረጡ ተማሪዎች ዛሬ አዴፓን የሚያዳምጡበት ጆሮ ያላቸው አይመስለኝም።በተመሳሳይ ይህንን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ፋኖዎችም ግልፅ አቋም አሳውቀዋል።ይህንን ችግር ክልሉ በአስቸኳይ ፈቶ ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ካላደረገ አፀፋ ይጠብቀዋል የሚል።ይህኛው አደገኛ ነው።የጊዜ ገደብም አስቀምጠዋል።አዴፓም ለማናገር የተገደደው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል።የሆነው ሁኖ ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ መደረግ አለበት።ማንም ብሄር ሳይፈናቀል እነርሱ ግን እዚህ ክልል እስጥ እንዲማሩ ቢደረግ፣ይህ ችግር ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እንዳይፈጠር የቅድመ መከላከል ቢሰራ፣ አጥፊዎች ካሉም ተመጣጣኝ ቅጣትና ተግሳፅ ቢሰጣቸው መልካም ነው

ሰጥቶ የማይሰለቸው የባህር ዳር ህዝብ ደግሞ እንደለመደው ምግብ እየመገባቸው ነው።እናቶች ድግስ እንዳለባቸው ሁሉ ወገባቸውን ታጥቀው ወጥ ሲሰሩ፣ እንጀራ ሲጋግሩ፣ ወጣቶች ደግሞ ዳቦና እንጀራ ሲሸከሙ ወጥ ሲያሳልፉ ተመልክተናል።እኛም እምነታችን በእናንተ ነው።በርቱ።
ተማሪዎቹ ዛሬ ምሽት ፍራሽ እየተሰጣቸው ነው።

አዴፓ በስንት ትግል ያገኛትን ከህዝብ ጋር የመታረቂያ ገመድ ባይበጥሳት መልካም ነው።ገመዷ የሲር ሳትሆን ትንሽ ከሳብናት የምትበጠስ የማግ ክር ነች።በአግባቡ መጠቀም መልካም ነው።በተለይም ካለብን ሰፊ ችግር አንፃር ቢያንስ የውስጥ ችግሮችን ከስር ከስር እየፈታን ወደ ህዝብ ብንቀርብ መልካም ይመስለኛል።

ለማንኛውም ሁሉንም በቅርበት እንከታተል።

ክብርና ምስጋና ለባህር ዳር ህዝብ!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.