ዓምዶም ገብረስላሴ የአሉላ የየሐንስ ጀግንነት ወራሽ ለመብት ተሟጓች የነፃነት መራሽ የቀውጥ ቀን ልጅ ለወገኑ ደራሽ የልቡን የሰራ የማይንበረከክ ጭራሽ

በአሁኑ ጊዜ በትግራይ በድቅድቅ ጨለማ ምድር እንደ ፋኑስ የሚያበራ ፣ እንደ አንበሳ የሚያገሳ ፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ተሟጓች በመሆን ወደ ፓለቲካ መድረኩ ብቅ ያለው ወጣቱ ምሁር አምዶም ገብረስላሴ ነው:: ይህ አንፀባራዊ ሁኔታ ሲታይ በአንድ በኩል አብዛኛው ምሁር ትግራዋይ በዛሬው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እየኖረ ነገር ግን የለውጥ ባለቤትና ግንባር ቀደም መሪ እንዳይሆን አእምሮ እያለው እንዳያስብ ፣ ጆሮ እያለው እንዳይሰማ ፣ ዓይን እያለው እንዳያይና አፍ እያለው እንዳይናገር ተደርጎ በህወሓት አደንዝዝ ፕሮፓጋንዳ ስለተሸበበ ከጭቁኑ ህዝብ ጎን ከመሰለፍ ይልቅ የነ ስብሓት ነጋ አሮጌ ስርዓት አጃቢ ፣ የዘራፊዎች ጠበቃና አውራ እንደሌለው ንብ በያለበት ተበታትኖ የጋን መብራት ሆኖ የቀረበት ፈታኝ ወቅት ሲሆን ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ህዝብ አማራጭ አጥቶ በህወሓት መሪዎች ሆስቴጅ (ጅሆ) ተይዞ በገዛ ሀገሩ የቁም እስረኛ ሆኖ የፍትሕ ያለህ!! የወገን ያለህ!! እያለ በመጮኽ የሚደርስለት ወገን ባጣበት ጊዜ :- ታጋይ ዓምዶም ገብረስላሴ ፍርሃትን ሰብሮ በመውጣት የዘራፊዎችንና የፅንፈኞችን ገመና በአደባባይ በማጋለጥ የፈፀመውን ጀግንነት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ያስመሰከረ ብቻ ሳይሆን ለአዲሱ ትውልድም ፈር ቀዳጅ ፣ የፅናት ተምሳሌትና ፋና ወጊ ሆኖ በኢትዮ}ያ የፓለቲካ መድረክ ብቅ ብሏል::    

ይህ አርቆ አስተዋይና ባለራዕይ ወጣት – የዓረና ትግራይ ለሉዓዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መስራችና የአመራር አባል በመሆን ላለፉት አሰርቱ ዓመታት ከያዘው አላማና ከመስመሩ ሳይዛነፍ በፅናት በመቆም እንደ ምድራዊያን መላእክት ተደርገው የሚሰገድላቸውንና ማንም ቀና ብሎ የማያያቸው የህወሓት መሪዎች ይቅርና ለመቶ ሚሊዮን የኢትዮ}ያ ህዝብ ቀርቶ ቁመንልሃል ለሚሉት የትግራይ ህዝብም ቢሆን የማይወክሉ ፣ ፀረ ሰብኣዊ ፍጡር ፣ ፀረ ዴሞክራሲ ፣ ፀረ ፍትሕ ፣ ባጠቃላይ የሕግ የበላይነት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን ጭራሽ የማያውቁ በሕገ አራዊት የሚመሩ የጥፋት ሐይል መሆናቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በአደባባይ ሲያጋልጧቸው ከቆዩት በሀገር ውስጥና በዲያስፓራ ከሚኖሩ ሐቀኛ የትግራይ ልጆች ከሆኑት የዓረና ታጋዮች አንዱ ዓምዶም ገብረስላሴ ነው::

 ሰሞኑን በትግራይ ክልል በህወሓት መሪዎች ስፓንሰርነት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀውና አሉ የተባሉትን ከፍተኛ የህወሓት ካድሬዎች፣ ባለስልጣናትና ሌሎች ተወካዮች በተገኙበት ትልቅ የውይይት መድረክ ላይ እነ አቦይ ስብሓትንና እነ በረከት ስምኦንን በህዝብ ፊት የሐፍረት ሸማን በማከናነብ የአዳራሹን አንበሳ ሆኖ የታየው ወጣቱ የፓለቲካ መሪ ዓንዶም ገብረስላሴ ነው:: 

ዓንደም አዳራሹ ብቻ አይደለም ወደ ማዕበላዊ (የትግል ሞጎድ) የቀየረው:: በይፋ ያስተላለፈውን መልእክት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም በሚገኙ ታጋዮችና ሚዲያዎች ዘንድም መነጋገሪያ ሆኖ ከመሰንበቱም በላይ ዓረና ትግራይ ፓርቲ አጥሩን አፍርሶ ለውጥ ማምጣት የሚችል ዓቅም እንዳለውና በተለይም የበሰበሰ የህወሓትን ስርዓት ለመተካት ብቻ ሳይሆን የማይበረከክ ደማሚት መሆኑን በተግባር በማሳየት ወደ አንድ የትግል ምዕራፍ ከፍ እንዲል አድርጎታል::

በመሆኑም የትግራይ ምሁራን በተለይም አዲሱ ትውልድ ትግራዋይ በምንም መልኩ ጊዜ የጣላቸውና ህዘብ የተፋቸው በመክሰም ላይ የሚገኙትን ዘራፊ መሪዎች እያስታመመ እነ ስብሓት ነጋና እነ በረከት ስምዖን በሚሰጡት የከሰረ አጀንዳ ተጠምዶ የታሪክን ጎማ ወደሗላ ለማሽከርከር የገመድ ጉተታ እየተጫወተ ፀረ ጥቅሙ ከሚሰለፍ ይልቅ የለውጥ ባለቤትና አራማጅ እሱ ራሱ መሆኑን አውቆ በጋራ መነሳት አለበት:: ያለፈውን የአርባ ዓመት ታሪካዊ ስህተት እንዳይደገም የነ ስብሓት ነጋን ሴራ ማምከን ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት::

“ጅብ ቀን የሚደበቀው በሌሊት የሰራውን ጉድ ስለሚያውቅ ነው” እንደተባለው ሁሉ ዘራፊ የህወሓት መሪዎች ማንም ሳይነካቸው በገዛ ፍቃዳቸው ፈርጥጠው በመሄድ በመቀሌ ከተማ የመሸጉበት ዋናው ምክንያት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈፀሙትን ወንጀል ጠንቅቀው ስለሚያውቁ መሆኑን ያደባባይ ሚስጢር ነው:: ነገር ግን ማን ላይ ቁመሽ ማንን ታምያለሽ ነውና ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል ከህዝባዊ ክንድ እንደማያመልጡ ገና አልገባቸውም:: የህወሓት መሪዎች እየተላተሙ ያሉት ከህዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጊዜም ጭምር ነው:: ስለዚህ የትግራይ ምድር የሌቦች መደበቂያ ሳይሆን የአብዮያታዊ ዴሞክራሲ ሰይጣናዊ ሰርዓት ማክተሚያና የህወሓት ቤተሰባዊና አረሜናዊ አገዛዝ መቀበሪያ እንደሚሆን ሩቅ አይሆንም::                              ከበላይ ገሰሰ

                                                                               ኢትዮ}ያ በልጆችዋ ትግል ትለመልማለች

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.