ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ከአፋር ዱኮሂና ወጣቶች የተሰጠ መግለጫ

የተደራጀ የሽብር ተግባርን ወደ ተራ የግጦሽ ግጭት ለመቀልበስ የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በፅኑ እናወግዛለን።

ሰሞኑን በኡንዳፎዖና በገዳማይቱ አከባቢ የተደራጁ የኢሳ ጎሳ ታጣቂዎች በውጭ ኃይሎች በመታገዝ የከፈቱት የሽብር ጥቃት የፀጥታ አስከባሪዎችን ጭምር ኢላማ በማድረግ የቀጠናውን ሰላም በማድፍረስ ላይ ይገኛል።ይህ በሺኒሌ ዞን ልዩ ስሟ አስቡሊ በምትባል ስፍራ በነ ጄነራል ማዓሾ ጠንሳሽነት ተደራጅቶ በተቀነጀ መልኩ ስውር የፖለቲካ ተልዕኮውን አንግቦ ወደ ምስራቅ ኦሮሚያና አፋር የዘመታው የጥፋት ቡድን፡ በገዳማይቱና በኡንዳፎዖ የመሸጉ የኮንተሮባንድ ነጋዴዎችንና የነጋዴዎቹ ጉዳይ አስፈፃሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን በቦታው የሚገኙ የመከላከያና የፌደራል ሃይልን ታግዞ ከቀን ወደ ቀን የአከባቢውን ስጋት እየጨመረው ይገኛል።

ከሻንኪሌ ወደ ምስራቅ ኦሮሚያ የገሰገሰው የቡድኑ አራትቃም ከሆላ ቦራ እስከ ቢኪ ከየረር እስከ ቢላ፣ እና፣ጎታ በሚባሉ አካባቢዎች በመሬት ይገባኛል ስም በከፈተው ጥቃት በኦሮሞና በኢሳ ጎሳዎች መሃል ከፍተኛ ጦርነትን ፈጥሮ አከባቢውን የጦርነት ቀጠና አድርጎት እንደሚገኝ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህን የጥፋት ተልዕኮ አንግቦ ወደ አፋር የመጣው የሽብር ቡድኑ ከሳምንት በፊት የመከላከያና የፌደራል ሃይል በሚገኝባቸው በሁለቱም ከተሞች የአንድ ሉዓላዊ ክልል ባንድራን አውርደው በአደባባይ ሲያቃጥሉ ተመልከትናል።

ይህን ኢ–ህገመንግስታዊ ህገወጥ ተግባር ለማውገዝም ሆነ ለመከልከል በቦታው የሚገኘው የመከላከያ ሃይል ፈቃደኝነቱን ባለማሳየቱ ታጣቂ ቡድኑ በዚህም ሳይቆም በአከባቢው በሚገኙ የአፋር የፀጥታ ሃይሎችና አርብቶ አደር ማህበረሰቡ ላይ ጥቃት በመክፈት ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
በገዳማይቱና በኡንዳፎዖ ባለው የኮንትሮባንድ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ከነጋዴዎቹ ጋር የጥቅም ቁርኝት እንዳላቸው የሚነገርላቸው በቦታው የሚገኙ የፌደራልና የመከላከያ ሃይል፡ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴና ለጉዳዩ ማስፈፀሚያ የጀርባ አጥንት በመሆን፣ በቀጠናው ያለውን ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እን በፌደራል መንግስት ትኩረት ውስጥ እንዳይገባ ተራ የግጦሽና የአርብቶ አደሮች ግጭት ቅርፅ ለማስያዝ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ከኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ጋር በፈጠሩት ግንባር የጥቅም ኔትወርካቸው በቦታው በሚሰፍሩ የአፋር ፀጥታ አስከባሪዎች እንዳይበጠስ ባላቸው ስጋት በአከባቢው የአፋር ፀጥታ ሃይሎች እንዳይሰፍሩና ታጣቂዎቹ እርምጃ እንዳይወሰድባቸው በማድረግ የአከባቢውን ውጥረት እያባባሱት ይገኛል።

የክልሉና የፌደራል መንግሰት ስለጉዳዩ በቂ መረጃ እንደሌለው ባናምንም፣ በቂ ትኩረት ተሰጥቷል የሚል እምነት የለንም። ባንድራን በአደባባይ በማቃጠልና በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት በመክፈት በመንግስትና በህዝብ ላይ ጦርነት ያወጀ የታጠቃ የሽብር ሃይል ላይ አስፈላጊ እርምጃ መወሰድ ሲገባ ጉዳዩን ወደ ተራ የሳር ግጦሽ ግጭት ለመጎተት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ሊያረጋግጥ ቀርቶ ለአፍሪካ ቀንድ የሚበቃ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም።

ስለሆነም መንግስት በቦታው የሚገኙ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የጥቅም ቁርኝት ያላቸውን የፌደራልና የመከላከያ ሃይልን በሌላ ተለዋጭ ሐይል በመተካትና በአከባቢው ለረጅም ጊዜ ፖለቲካዊ አላማን በማንገብ እንደ ልብ የሚፈነጩ ኮንትሮባንዲስቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አከርካሪያቸውን በመስበር በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በአስቸኳይ የቀጠናውን ሰላም እንዲያረጋግጥ ለመጨረሻ ጊዜ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

#ዱኮሂና

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.