የምሳሩ እጀታ በምን ተቆረጠ? (ድራንዝ ጳውሎስ ከባህር ዳር)

ሰርክ የምንሰማውና የምናየው ለጆሮ የሚሰቀጥጥና ለዓይን የሚያጽበረብር ነው፡፡  በሻሸመኔ ከተማ ከጫካ አስተሳሰብ ያልወጡ የሻሸመኔ ቄሮዎች ወገናቸውን ዘቅዝቀው ሲሰቅሉ ፤በቡራዮ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ቡራዮ ላይ ከስልሳ በላይ ዜጎችን ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሲጨፈጭፉ፤ በአዋሳ ከተማ ምስኪን ዜጎቻችንን በቤንዚን ሲያቃጠሉ፤ በትግራይ ከአስራ ሰባት አመት በላይ ጠዋት፣ ማታ ሲጠብቃቸው የኖረውን መከላከያ ሠራዊት አታልፍም ብለው ታንኩንና መኪናውን ሲያግቱት፤ በኦሮሚያ-ኦነግ የሚባል ጭንጋፍ ከርታታና አገር የለሽ ስደተኛ ድርጅት በአገር ውስጥ ማሠልጠኛ ከፍቶ ወታደር ማሰልጠኑንና የሜቴክን የአገር መሸጥ ወንጀል ስንሰማ ዘይገርም አቢሲኒያ እያልን በሰማነው ስንገረም ባለንበት ወቅት የገና ዕለት ደግሞ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ዉሃ ከተማ ኮኪት አካባቢ በተከሰተ የፀጥታ ችግር የመከላከያ ሠራዊት የሰዎችን ሕይወት ማጥፋቱን አደመጥን:: ውሎ አድሮም ቢሆን የክልሉ መንግስት አቋሙን በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በኩል አሳወቀን፡፡

የእናንተ እንጃ እንጂ እኔን የገረመኝ በየዓመቱ አውድ ዓመትና በዓል እየጠበቁ የወያኔ እሽኮክላ ሠራዊት በአማራ ሕዝብ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ሳስብ አምና በጥምቀት በዓል በወልዲያ ከተማ በምዕመናኑ ላይ የደረሰው ዕልቂት ማንሳቱ በቂ ነው፡፡ ያኔም የክልሉ መንግስት መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ እነሱ ሲያጠቁ የአማራ ክልል መንግስት መግለጫ ሲሠጥ መኖር አለበት? አማራ አልገብቶትም፡፡   

ያም አለ ያም አለ መከላከያ ሠራዊቱ አማራ ክልል ዉስጥ ለምን ገባ? እንዴት ገባ? የሚገባበት ምክንያትም ሆነ የአገባብ ሥርዓቱ በሕግ የተደነገገ ነወይ? ብለን ብንጠይቅ የምሳሩ እጀታ በምን እንደተቆረጠ ምላሽ እንዳጣው ጠያቂ መሆንን ግድ ይላል፡፡   ምናልባት በአካባቢዉ ካምፕ ስላለዉ ከሆነም ከካምፑ ዉጭ መደበኛ የጸጥታ ተግባር ዉስጥ መሠማራት አይችልም፡፡ ስለሆነም መከላከያ ሠራዊቱ በገንዳ ዉሃ ንጹሃንን በመግደሉ ይህን ድርጊት የፈጸሙት ለፍርድ መቅረብ አለባቸዉ፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ የግል ድርጅት (ኩባንያ) ሃብትና ንብረት ጠባቂና አጃቢ አይደለም፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን የግል (የኢፈርት) ድርጅት ነዉ፡፡ በዚህ ድርጅት ሃብትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርሰበት (የሚደርሰበት ከሆነ) የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ድርጅቱ የሚገኝበት ክልል ፖሊስ ነዉ፡፡ በገንዳ ዉሃዉ ጉዳይ የአማራ ክልል ፖሊስ ነዉ፡፡ ስለሆነም መከላከያ ሠራዊቱ በየትኛዉ የሕግ መሠረት ነዉ የሱር ኮንስትራክሽንን ንብረት አጃቢና ጠባቂ የሚሆነዉ? የዚህን ድርጅት ንብረት በመጠበቅ ሰበብ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት ያጠፉና ትእዛዝ የሰጡ ወታደሮችና መኮንኖች በፍጥነት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለፍርድም መቅረብ አለባቸዉ፡፡

መከላከያ ሱር ኮንስትራክሽንን ደግፎ ህዝብ የጨፈጨፈው የቢዝነስ ወዳጁ ስለሆነ እንደሆነ እማኝ አንጠራም፡፡ ክንፈ ዳኘው ሜቴክ 37 ቢሊዮን ብር ሲያጭበረብር ሱር ኮንስትራክሽን ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ሜጭበርበሩን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲከካ ሲቦካ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡

የሚገርመው መከላከያ ለዚህ ዘራፊ ኩባንያ ንብረት ሲል ነው 27 ንፁሃን አማራዎችን መጨፍጨፉ ነው፡፡ የመንግስት የግዥ ስርዓት ሳይከተል ሀገር የሚዘርፍን ኩባንያ፣ መሳሪያ እየሸጠ ህዝብ የሚጨፉጭፍን የሌባ ጥርቅም የሚጠብቅ መከላከያ አባል መሆን በራሱ ያሳፍራል።

ሱር ኮንስትራክሽን ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፈ፣ ህዝብን ያስጨፈጨፈ የአጥፊዎች ስብስብ ነው፡፡ ፈቃድ ወስደው እንደሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀል ድርጅቶች ሆኖ ሳለ የመከላከያ ሽፋን ሊሰጠው መቻሉ አግራሞት ቢጭርብኝም ድርጅቱ ከሚገነባው የሚያፈርሰው፣ የሚያጠፋው፣ የሚዘርፈው መብዛቱ ባለቤቶቹ ማን ቢሆኑ ነው? ይህ መልስ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ 
መንግስት እንዲህ ዓይነቱን አሰመሳይ ድርጅት ጊዜ በሰጡት ቁጥር ጥፋቱና አስጊነቱ ስለሚጨምር የብዙዎቹን ንጹሃን ዜጎች ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን አጣርቶ መፍትሔ ለመስጠት ጊዜ መውሰድ የለበትም፡፡


ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ “መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ተተኩሶበታል፤ ሁኔታዉን ለማረጋጋት ወደ ላይ ተኩሷል፤ ራሱንም መከላከል ይችላል” የሚል ይዘት ያለዉ ምላሽ ለቪኦኤ የአማራኛ ቋንቋ ሬዲዮ ጣቢያ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ምላሻቸዉ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡

በመጀመሪያ ሲጀመር ስለምን ክልል ዉስጥ ገባ ስለምንስ የግል ድርጅት ንብረት ጠባቂ ሆነ በምን አግባብ በየትኛዉ ሕግ መሠረት እነዚህን ጥያቄዎች ሊመልሱ ይገባል፡፡

በሁለተኛነት እሳቸዉ እንደሚሉት ወደ ላይ ከሆነ የተተኮሰዉ ወደ 15 ሰዉ ገደማ ማን ገደላቸዉ 30 ሰዉ ገደማስ ማን አቆሰላቸዉ ወደ ሰማይ የተተኮሰ ጥይት ወደ መሬት ሲመለስ ብለዉ መቼም እንደማይመልሱ እርግጠኛ ነዉ፡፡

ሦስተኛዉ ደግሞ እሺ መከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተኮሰ ሰዉ ነበር ብንል እንኳን ሕይወታቸዉ ካለፉት ዉስጥ ሕጻናት አሉ፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶች አሉ፡፡ አራስ እናቶች አሉ፡፡ ጀነራል ብርሃኑ እነዚህም መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ስለተኮሱ ነዉ የተገደሉት፣ ሠራዊቱ ራሱን ሲከላከል ነዉ የገዳለቸዉ ብለዉ እንደማይመልሱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እና እንዴት በሕጻናት በነፍሰ ጡርና በአራስ እናቶች ሞት ትንሽ እንኳን ሰብአዊነት ተሰምቶዎት ጥፋተኞችን መገሰጽ አልፈለጉም ?

እርስዎ የወታደራዊ ስምሪት አዛዥ ነዎት፡፡ በዚህ መጠን ዐይንዎን በጨዉ አጥበዉ በሟችና በተጎጅዎች ላይ የደረሰዉን ኢሰብአዊ ድርጊት ወደ ሟቾችና ተጎጅዎች ለማዞር ሞክረዋል፡፡ ምናልባትም እርስዎም እነዚህን ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡርና አራስ እናቶች የገደሉትን ወታደሮች በማሰማራቱ ላይ ይኖሩበት ይሆን እንዴ ብለን ብንጠረጥር ጥርጣሬያችን ኢ – ምክንያታዊ አይሆንም፡፡

ንጹሃን ዜጎችን የገደሉ፣ ያቆሰሉ ለፍትሕ ይቅረቡ! የመከላከያ ሚኒስትሯ ስለ ሁኔታዉ ማብራሪያ መሠጠት ይበቅባቸዋል፡፡ኢታማዦር ሹሙ፣ ጀኔራል ሰዓረ መኮንንም በተለይ ጎንደር ላይ በተደጋጋሚ ሕዝብን እየገደለ ስላለዉ ሠራዊታቸዉ እኩይ ተግባር በአፋጣኝ እርምጃ መዉሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድም በጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥነታቸዉ እነዚህን ሕጻናትና እናቶች የገደሉ፣ ወታደሮች በሚመለከት እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእሳቸዉ የሚታዘዘዉ ሠራዊት አማራ ክልል ላይ ሕጻናትና እና እናቶችን ገዳይ ሆኗልና፡፡

3 COMMENTS

  1. There are indications that show the TPLF forces had posed as members of the defense force and committed the killings in the Gonder areas.

  2. በየአካባቢው ጨካኝ ግድያ በተካሄደበት ጊዜ ህወሓት ነው፣አነግነው እየተባለ ዝም ብሎ መታለፉን ፣ነብሰ ገዳዮቹም ተገንዝበውታል።ፍቅርና ሰላም ነው የምንፈልገው እየተባለ የንፁሃንን ደም ማስፈሰስ አጋር ያስመስላል። ጉዳዮችንም የልብ ልብ እየሰጠ ድፍረታቸው ወደር አጥቷል።
    መንግሥት ስለ ሰላም መስበክ ብቻ ሳይሆን ፣መብት ይዞ እስተቀመጠ ድረስ፣ ሰላምን ማስከበርም ሐላፊነት አለበት። ከግዜ ብዛት ይረዳል ብሎም ግፍን ማረሳሳት ወይም የሽግግር ጊዜ ይህ ዓይነት ሁኔታ የተለመደ ነው ብሎ ማለፍ በወገን ደም መቀለድ ነው። በየትኛውም ዓለማችን አካባቢ የደም ጥማተኞች ስለሰላም መስበክ ነብሩ እንኳን ሊናከስ የሚቧጭርበት ጥፍርም እንደሌለው ነው የሚገነዘቡት።
    እንግዲህ መንግሥት ህዝቡን መጠበቅ ካቃተው ህዝብ ራሱን ለመጠበቅ መገደዱ አማራጭ የለሽ ሊሆን ነው። ጠ/ሚኒስትራችን አጥፊን በትግስት ማሳለፍ ሳይሆን ፣ለድርጊታቸው ተጠያቂ መሆናቸውን ያለ ማወላወል ስራ ላይ ማዋል አለባቸው ። አለበለዚያ ስርአት አልባነት ይነግስና ፣ህዝብ ራሱን ለመከላከል እንዲታጠቅ ይጋብዛል።

  3. ሰለሞን፣
    ህወሓት የመከላከያ ልብስ ለብሶ ህዝብ ሲጨፈጭፋ፣ መከላከያስ የት ነበር ወይስ አትድረሱላቸው ተብሎ ትእዛዝ ተላልፏል ። ይሄ ደሞ የማያዋጣ ሰበብ ፍለጋ ነው።መንግስትንም ተባባሪ ያደርጋል። በሽግግር መንግሥት ላይ ያለውንም ጥርጣሬ ያባብሳል። ሕወሓት ነው እያሉ እኩይ ተግባርን በትዝብት ማለፍ ፣የተበዳይን ወገን ፣ ሟችን በድጋሚ መግደል ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.