በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት ሲሉ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ንቅናቄው “ኢትዮጽያዊነትን እናወድስ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

በኮንሰርቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ በኢትዮጵያ አሁን ያለውን አንድነት ለማጠናከር የቀደመውን አንድነት ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

“የሙዚቃ ኮንሰርቱም አንድነታችንና ኢትዮጵያዊነታችንን እያሞገስን በሀገሪቷ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የበኩላችን ለመወጣት ቃላችንን ዳግም የምናድስበት ነው” ብለዋል።

ኮንሰርቱ ኢትዮጵያዊነትን ከማወደስ ባሻገርም ንቅናቄውን በመላው ሀገሪቱ ለማደራጀት የሚያስችል ገቢን ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተዋካዮች የተገኙ ሲሆን፥ታዋቂ የሙዚቃ ባንዶች፣ ወጣትና አንጋፋ ድምጻውያን ተሳትፈዋል።

በለይኩን አለም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.