የአማራ ቲቪ ጋዜጠኛ ከበረከት ስምኦን ጋር ያደረገው ምናባዊ ቃለ ምልልስ

ጋዜጠኛ:  አቶ በረከት በመታሰርህ ምን ይሰማሃል ።
በረከት:  ታላቅ እፎይታ።

ጋዜጠኛ:  እንዴት?

በረከት:  ባለፈው ቃለምልልስ ላይ እንደገለፅኩት የራሴ መኖሪያ ቤት ስለሌለኝ በየጎዳናው ስንክራተት ነው የከረምኩት። ስለዚህ አሁን ቋሚ ማረፊያ ቤት ስላገኘሁ ደስተኛ ነኝ።

ጋዜጠኛ ፣ የታሰርክበትን ምክንያት ታውቀዋለህ?

በረከት:  እነሱ የሚሉት ከጥረት ጋር የተያያዘ ነው። እኔ ግን ደጋግሜ እንዳስረዳሁት የጥረትን ካፒታል ወደ 11 ቢሊየን ብር ከማሳደግ ውጪ የሰራሁት ጥፋት የለም። ትክክለኛ የታሰርኩበት ምክንያት ሌላ ነው።

ጋዜጠኛ:  ሌላ ምክንያት ስትል ?

በረከት: ባለፈው ቃለምልልስ ላይ እንደገለፅኩት አብይ ተደመር እና በብራስልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ላድርግህ ብሎ ጠይቆኝ እምቢ ስላልኩት በቂም በቀል ነው የታሰርኩት ።

ጋዜጠኛ:  ለምን እምቢ አልክ?

በረከት: እስቲ ይታይህ ይሄ ሆነ ብሎ የተቀነባበረ ደባ ነው። ብራስልስ የመለስ ነፍስ የወጣችበት ቦታ ነው። እኔ ከመለስ ጋር የገባሁት ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አለ። ቃል ኪዳኑን ማፍረስ አልፈልግም ።

ጋዜጠኛ:  ምን የሚል ቃልኪዳን ነው ከመለስ ጋር የገባችሁት?

በረከት:  ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና ህዝቧን እርስበርስ ለማባላት።

ጋዜጠኛ:  እሱ እኮ ከስሟል። አሁን ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ጠሚ ቤተመንግስቱን ተረክቧል።

በረከት:  በጣም የዋህ ነህ ማለት ነው። አብይ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ይበል እንጂ ህዝቡ እሱን አይሰማውም። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም የዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ ብሎ በመለስ መንፈስ ነው የሚተዳደረው ።
የመለስ መንፈስ ገና ሐያ አመት ሃገሪቱን ይመራታል። በዚህ ከቀጠለች ልትፈርስም ትችላለች ።

ጋዜጠኛ:  በነገራችን ላይ መለስ በሕይወት በነበረበት ወቅት አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ስትወያዩ ፣ ሰይጣን ግድግዳው ላይ ጆሮውን ለጥፎ ከእናንተ ክፋት ለመኮረጅ ይሞክር ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ ። ይሄን ጉዳይ ታስተባብላለህ?

በረከት:  ሰይጣን እኔና መለስ ስንወያይ ሊኮርጅ ሞክሮ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይሄንን የሚሉት ሰዎች ሰይጣኖቹ እራሳቸው ካልሆኑ በስተቀር ይሄንን ሚስጥር እንዴት ሊያውቁ ቻሉ?

ጋዜጠኛ: ለመታሰርህ  ሌላ የምትጠረጥረው ምክንያት ይኖራል?

በረከት:አዎ በመሐመድ አላሙዲን ላይ የሰራሁት ግፍ ሳይሆን አይቀርም ።

ጋዜጠኛ:  ምን አይነት ግፍ ነው የሰራህው?

በረከት: እንደምታውቁት መሐመድ የሁለት ምርጫዎች ወግ የሚለውን መፅሀፌን ስፓንሰር አድርጐ አሳትሞልኛል፣ ስታመም ውጭ ሐገር ልኮ አሳክሞኛል ፣ ወርቅ ሸልሞኛል ፣ ሌላ መጥቀስ የማልፈልጋቸው ብዙ ውለታዎች ፈፅሞልኛል። እኔ ግን ሲታሰር ይፈታ ብዬ እንኳን አልጮህኩለትም ፣ ሄጄም አልጠየቅኩትም።  የሰውዬው ግፍ አለብኝ።

ጋዜጠኛ: ብዙ ጊዜ ስትዋሽ አይኑ እንኳን አይርገበገብም የሚሉህን ሰዎች ምን ትላቸዋለህ።

በረከት:  ጅሎች እላቸዋለሁ። አፌ ለሚዋሸው አይኔ ለምንድነው የሚርገበገበው?

ጋዜጠኛ: ከአፍህ እንቅስቃሴ መዋሸትህን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አፍህን ገጥመህ ነው የምታወራው ። ይሄንን ልምድ እንዴት ነው ያዳበርከው?

በረከት: አፉን ከፍቶ የሚያወራ ባለጌ ብቻ ነው። ጨዋ ሰው እንደ እኔ አፉን ገጥሞ ማውራት መቻል አለበት። በረጅም ጊዜ ልምድ ያዳበርኩት ነገር ነው።

ጋዜጠኛ: ከትግራይ ክልል ለምን ተመለስክ? እዚያ ብትሆን ምናልባት ላትታሰር ትችል ነበር።

በረከት:  እንዴት መሰለህ አንዳንድ አክራሪ የትግራይ ባለሥልጣኖች አንተ ድርብ ጠላታችን ስለሆንክ እናጠፋሃለን እያሉ ያስፈራሩኝ ጀመር። 
በዚህ ላይ እነ ደብረጽዮን ከለላ አንሰጥህም ። እዚ ሆነህ ከታሰርክ የትግራይን ክልል ታስደፍራለህ ብለው ወደ አዲስአበባ እንድሄድ ተፅእኖ አደረጉብኝ ።

ጋዜጠኛ:  ድርብ ጠላት ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?

በረከት: በአንድ ወገን ጠላታችን የሆነውን የአማራን ክልል ስታገለግል ነው የኖርከው። በሌላ በኩል ደግሞ በደምህ የሌላው ጠላታችን የኤርትራ ሰው ነህ ስለዚህ ድርብ ጠላታችን ነህ አሉኝ ።

ከዚያም የአማራ ፓርቲ አባል ብሆንም ውስጥ ለውስጥ ህወሓትን ነው ሳገለግል ነው የኖርኩት ስላቸው ።እንዲያውም ደብል ኤጀንት የመሆን ልምድ ስላለህ አሁን ደግሞ ድሮ ያጠፋሀውን ለመካስ ስትል ለእነሱ ልታገለግል ስለምትችል አናምንህም አሉኝ ።

ጋዜጠኛ:  ሰራዊት ፍቅሬ እና ሸዋፈራሁ ደሳለኝ የቀድሞው ኢቲቪ የማስታወቂያ ስራ ያሰራን የነበረው በችሎታችን እንጂ ልዩ ድጋፍ አልተደረገልንም ይላሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

በረከት:እንደምታውቀው በማስታወቂያ ስራ ኩሬውን ባህር ነው ብሎ ለማሳመን ጥሩ የማጭበርበር ችሎታ ይጠይቃል። እነ ሰራዊት ደግሞ በዚህ የተካኑ ናቸው። ስለዚህ እነ ሰራዊት በችሎታችን ነው ማስታወቂያ እንሰራ የነበረው ያሉት ትክክል ነው። ጥሩ የማጭበርበር ችሎታ አላቸው ።

ጋዜጠኛ:  የእራስህን ጠበቃ ታቆማለህ ወይስ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምልህ ትፈልጋለህ?

በረከት:  ያሉኝ ጥሪቶች መፅሀፎቼ ናቸው። አላሙዲን እንዳይረዳኝ እሱም ታስሯል ። ስለዚህ መፅሀፎቼን ተረክቦ ጥብቅና የሚቆምልኝ ባገኝ ደስ ይለኛል ።

ጋዜጠኛ: ጥሪት የለኝም ካልክ እስርቤት ውስጥ የሻማ ምን ልትሰጥ አስበሃል?

በረከት: የሚገርምህ ይሄንኑ አስቤ ድንገት ከታሰርኩ ብዬ መፅሀፎቼን በባክ ፓክ ተሸክሜ ነው የምዞረው። እሱኑ እሰጣቸዋለሁ።

ጋዜጠኛ:  አሁን እኮ እንደ ድሮው የፓለቲካ እስረኞች የሉም ። ደረቅ ወንጀለኞች ደግሞ መጽሀፍ የማንበብ ልምድ የላቸውም ።

በረከት: እንደዛ ከሆነ እኔው እያነበብኩ እተርክላቸዋለሁ።

ጋዜጠኛ: በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ይኖራል ።

በረከት:  እነ ገዱ እና ደመቀ ሳያውቁ ብቻዬን የሰራሁት ምንም ወንጀል የለም። እነሱም መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

ሌላው ሁሉም ሊያውቁት የሚገባው ጉዳይ እኔን በማሰር የመለስን ራእይ ማጨናገፍ እንደማይቻል ነው። መለሰ ከሞተ ስምንት አመት ቢያልፈውም ህዝቡ ማንም ሳይቀሰቅሰው ራእዩን በራሱ ፍላጎት መለስ ትቶት በሄደው ሚኒሞ እያስኬደው ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.