በ59 ሰዎች ሞትና በ412 ሚሊዮን ብር ውድመት የተጠረጠሩ የቀድሞ ሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ኡመርን ጨምሮ 47 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

በሶማሌ ክልል “ሄጎ” የሚል ቡድን በማደራጀት ዜጎች እርስ በርሳቸው እንዲዋጉ አድርገዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ኡመርን ጨምሮ 47 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቢ ህግ ሁሉንም ተከሳሾች ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ከሰኔ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ባሉ ቀናቶች ውስጥ ነው አንዱ ወገን በሌላ ወገን ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል ያላቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሶማሌ ተወላጆችና በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች ላይ በአካባቢው አጠራር “ሐበሻ” በሚል በሚጠሯው የክልሉ ነዋሪዎች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር በማሰብ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ “ሄጎ” የሚል ቡድን በማደራጀት በገንዘብና በቁሳቁስ ደግፈዋል፣ መሳሪያም አስታጥቀዋል ብሏል የዓቃቢ ህግ ክስ፡፡

ተከሳሾቹ ግጭቱ የሚመራበትና መልዕክት የሚተላለፍበት ‹‹ሄጎ ዋሄገን›› የሚል የፌስቡክ ገጽ ከፍተው የተለያዮ መልዕክቶች በማሰራጨት ግጭቱ እንዲፈጠር አድርገዋል ሲልም ክሱ አመልክቷል፡፡

“በኦሮሞ ተወላጆች ተወረናል፤ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታችንን ለቀው መውጣት አለባቸው፤ ነዳጃችንን፣ ወርቃችንንና መሬታችንን በጉልበት ሊወስዱብን ነው ፣እንዲሁም የፌዴራል መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ሊወረን ነው ፣አዲስ መንግስትም ሊያቋቁም ነው ፣ስለዚህ ሁላችንም በጋራ መነሳት አለብን” ብለው ተጠርጣሪዎቹ ቀስቅሰዋል ብሏል ክሱ፡፡

በዚህም በክልሉ ከሶማሌ ተወላጆች ውጪ የሆኑትን ብሔረሰቦችን በአካባቢው በተለምዶ “ሐበሻ” በሚል የሚጠሩትን መግደል፤ ንብረታቸውንም መዝረፍና ማውደም፤ ባንኮችንና ኢንሹራንሶችን መዝረፍ፤ ቤተክርስቲያኖችና ማዲያዎችን ማቃጠል አለብን በማለት በአድማ ተንቀሳቅሰዋል የሚለውንም ክሱ አክሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በግጭቱ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ ሀላፊነቱን እንዳይፈጽም ከካምፕ እንይወጣ በማድረግ “ሄጎዎች” የሰሯቸውን ስራዎች እንዳይከላከል አድርገዋልም ተብሏል፡፡

ተከሳሾቹ በየቦታው ተንቀሳቅሰው ትዕዛዝ በመስጠት በክልሉ ውስጥ ግጭት እንዲነሳ በማድረጋቸው የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ በመንግስት፣ በእምነትና በግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፤ ሴቶች እንዲደፈሩና በርካታ የከተማው ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ አድርገዋልም ይላል ክሱ፡፡

አንደኛው ተከሳሽ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ሰኔ፣ 2010 ዓ.ም በፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አዳራሽ ውስጥ የሄጎ አመራርና አባላትን በመሰብሰብ የእሱን የስልጣን አገዛዝ የሚቃወሙ ሰዎችን ለመከላከል፣ ለማዋረድና ለመተቸት በሚል የሄጎ ቡድን እንደአዲስ ተጠናክሮ እንዲደራጅ አድርጓል ሲልም ክሱ አትቷል፡፡

በዚህም ሰዎችን ለማዋረድና ለመተቸት የሚረዳቸውን 41 የሳምሰንግ ስልኮችን ለሄጎ አባላት ሰጥቷል እንዲሁም ዘጠኝ የሄጎ ስራ አስፈፃሚዎች የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁ አቶ አብዲ መሐመድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፤ በየዞኑና በየወረዳው እየዞሩ የሄጎ አባላትን እንዲመለምሉ አድርጓም ብሏል ዕቃቢ ህግ፡፡

ስራ እንሰጣችዋለን በሚል ሽፋን የሄጎ አባላትን ለመመልመልና ለማደራጀት ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በጀት ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲወጣ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንቱ አድርገዋል ሲልም ክሱ ጠቁሟል፡፡

የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ሙሐመድ ለሄጎ አባላት ሐበሻ ተብለው የሚጠሩትን ተንቀሳቅሰው እንዲገድሉ ንብረታቸው እንዲዘርፉና እንዲያወድሙ፣ ባንኮችንና እንዲዘርፉ፣ ቤተክትስቲያኖችና ማዲያዎችና እንዲያቃጥሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚሉ ጉዳዮችም በክሱ ተካቷል፡፡

ተከሳሾች ክስ መቃወሚያችውን ለማቅረብ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳልተመካከሩ እና ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱም ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ከጠበቆቻቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ የክስ መቀወሚያ ለማቅረብ ይችሉ ዘንድ ለጥር 29፣2011 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

የቀጠሮ እስረኞችም እስከዚያው ደረስ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩና የዋስትና ጉዳይ ከዚያ በኋላ የሚታይ መሆኑን ችሎቱ አመልክቷል፡፡


በጥላሁን ካሳ/ EBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.