በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ተፈፅሟል ከተባለው የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩት መካከል አራቱ ፍርድ ዛሬ ቤት ቀረቡ

ከጥረት ኮርፖሬት፣ ላፓልማ እና ባህርዳር ሞተርስ አክሲዮን ማህበር ውስጥ ተፈፅሟል ከተባለው የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩት አምስት ግለሰቦች መካከል አራቱ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ወይዘሮ እየሩሳሌም ብርሃኑ፣ ወይዘሮ ቤተልሄም ብርሃኑ፣ ወይዘሮ አይናለም ሀይለልዑል እና አቶ ግርማቸው ዘውዱ በባህር ዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ቀርበዋል።

ወይዘሮ እየሩሳሌም ብርሃኑ፣ ወይዘሮ ቤተልሄም ብርሃኑ እና ወይዘሮ አይናለም ሀይለልዑል ላፓልማ አክሲዮን ማህበር መስራች ሲሆኑ፥ ከጥረት ኮርፖሬት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመመሳጠር አክሲዮን ማህበሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነበረው 30 ሚሊየን ብር መካከል 16 ሚሊየን ብሩን በማውጣት ያለአግባብ ተጠቅማወል ሲል የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ከላፓልማ አክሲዮን ማህበር ሲወጡ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው በመጠቀም የህዝብና የመንግስት ሀብትን በማባከን እንደጠረጠራቸውም የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡

ሌላኛው ተጠርጣሪ አቶ ግርማቸው ዘውዱ በበኩላቸው ከጥረት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመመሳጠር ከባህር ዳር ሞተርስ በ24 ነጥብ 7 ሚሊየን የአክሲዮን ግዥ ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል መርማሪ ጉዳዩን የተያያዙ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በተለይ ወይዘሮ እየሩሳሌም ብርሃኑ፣ ወይዘሮ ቤተልሄም ብርሃኑ እና ወይዘሮ አይናለም ሀይለልዑል፥ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና ጠበቆቻቸውን እንዳላማከሩ በመጥቀስ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ተቃውመዋል።

የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም በጉዳዩ ላይ ብያን ለመስጠት ለሰኞ ጥር 27 ቀን 2011 አመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የአምባሰል ንግድ ስራዎች ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምትኩ በየነ ጉዳይ በጊዜ እጥረት ለሰኞ ተላልፏል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ/ ኤፍ.ቢ.ሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.