ሰበር ዜና – የባሕር ዳር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዐረፉ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፤ የባሕር ዳር ከተማ የአዊ እና መተከል ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ከታኅሣሥ 23 ቀን 1923 – ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም.)

His Grace Abune Petros
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፤ የባሕር ዳር ከተማ የአዊ እና መተከል ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ከታኅሣሥ 23 ቀን 1923 – ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም.)

ሐራ ዘተዋሕዶ

  • የቀብር ሥነ ሥርዐቱ÷ ነገ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አበው ካህናት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲኹም የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ በርካታ ምእመናን እና የክልሉ አስተዳደር ሓላፊዎች በተገኙበት በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ከቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ አጠገብ በተዘጋጀው መካነ መቃብር ይፈጸማል::
  • ዕለተ ዕረፍታቸውን አስቀድመው ዐውቀዋል፤ የምረቃ መርሐ ግብሩ ለነገ ሚያዝያ ፲፩ ቀን ተይዞለት የነበረው የካህናት ማሠልጠኛ‹‹እኔ ሳልሞት ኮሌጁ ይመረቅልኝ›› በማለታቸው ምረቃው ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት ተከናውኗል:: የባሕር ዳር ካህናት ማሠልጠኛ ኮሌጅ 90 ሠልጣኞችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ያለው ሲኾን ሦስት የመማሪያ ክፍሎች እና 850 ሰዎችን የሚይዝ አዳራሽ ያካተተ ነው፡
  • ከአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ከገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተሰበሰበ የብር 3.8 ሚልዮን ጠቅላላ ወጪ የተገነባው የባሕር ዳር ካህናት ማሠልጠኛ ኮሌጅ ሥራ÷ ብፁዕነታቸው የነበረባቸውን የደም ግፊት እና ስኳር ሕመሞች በመቋቋም በየዕለቱ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ ሥራውን ተከታተለው ያስፈጸሙት ነበር፡፡
  • የብፁዕነታቸው የኅልፈት መንሥኤም በቂ ክትትል ያላደረጉለት ከዚኹ የጤና እክል ጋራ የተያያዘ ሕመማቸው ነበር፡፡ በትላንትናው ዕለት ከቀኑ 10፡00 የኮሌጁን ዘላቂ የበጀት ምንጮች በተመለከተ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ልኡካን ጋራ በኮሌጁ በመወያየት ላይ ሳሉ በድንገት ራሳቸውን መሳታቸው ተጠቁሟል፡፡
  • በቅድሚያ በጋምቢ ሆስፒታል አፋጣኝ ርዳታ ከተካሔደላቸው በኋላ ማምሻውን ለተሻለ ሕክምና ወደ ባሕር ዳር ፈለገ ገነት ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ሌሊቱን የሕክምና ክትትል ቢደረግላቸውም ያጋጠማቸው የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ዛሬ፣ ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከጠዋቱ 1፡00 ለኅልፈት እንዳበቃቸው ተጠቁሟል፡፡
  • ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ ሀገረ ስብከት የተመደቡት እና በተወለዱ በ84 ዓመት ዕድሜአቸው ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ÷ የመላው አፍሪቃ ኤጲስ ቆጶስ ሳሉ በተለይም በደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም፣ በናይጄሪያ – ሌጎስ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመትከል፣ በኬንያ፣ በጋና ) ከ1991 – 1994 ዓ.ም. ያበረከቱት ከፍተኛ ሐዋርያዊ ተግባር ተጠቃሽ ነው፡፡
  • ከዚኽም በኋላ በሽሬ እና ሑመራ አህጉረ ስብከት (ከ1994 – 1996 ዓ.ም.)፣ በአውስትራልያ እና ኒውዝላንድ (ከ1998 – 2001)፣ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት (2001 ዓ.ም.)፣ በምዕራብ ጎጃም፣ አዊና መተከል ዞኖች አህጉረ ስብከት (2003 ዓ.ም.) መንበረ ጵጵስና በማሠራት እና አህጉረ ስብከቱን በማጠናከር ከፍተኛ አባታዊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡
  • በምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ዐይን ዓምባ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ሰበካ ታኅሣሥ 29 ቀን 1923 ዓ.ም. የተወለዱት ብፁዕነታቸው፣ ጎልተው የሚታወቁት በቅኔ እና የቅዳሴ መምህርነታቸው እንዲኹም በበርካታ ቋንቋዎች ተናጋሪነታቸው ነው፡፡ የትምህርተ ኅቡአት፣ የቅዳሴ ማርያም፣ የውዳሴ ማርያም፣ አርባዕቱ ወንጌል ትርጓሜያት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ከመሪጌታ ወልደ ኪዳን፤ ቅዳሴ ከደብረ ዓባይ ዬኔታ የኋላ እሸት፣ (ከ1954 – 1956 ዓ.ም.) በሚገባ ተምረው አጠናቅቀዋል፡፡
  • በራስ መኰንን ት/ቤት ከ1967 – 69 ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ከ1969 – 73 ዓ.ም. ዓረቢኛ ቋንቋ እና ቴዎሎጂ አጥንተዋል፡፡ በግሪክ ሔለኒ ኮሌጅ (ከ1973 – 74 ዓ.ም.) እንዲኹም በአሜሪካ ቦስተን ሔለኒ ኮሌጅ በተጨማሪ ሥልጠናዎች የቴዎሎጂ ጥናታቸውን አጠናክረዋል፡፡ ከሀገርኛው ግእዝ፣ አማርኛ እና ትግርኛ በተጨማሪ ከውጭ በዐረብኛ፣ በግሪክኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎችም ይነጋገሩ፤ ይግባቡ ነበር፡፡
  • በፊት ስማቸው ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ በዛ የሚባሉት ብፁዕነታቸው፣ ከሌሎች 15 አባቶች ጋራ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ተብለውበመላው አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶስ የተሾሙት ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. በቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተፈጸመ አንብሮተ እድ ነበር፡፡
የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደረብን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.