ኧረ ለመሆኑ የጤፍ ፓተንት ቁማር መቼ ነው የሚያበቃው? (ሰርፀ ደስታ)

ይሄ ጉዳይ በየ ዓመቱ ብቅ እያለ ቁማሩ ቀጥሏል፡፡ አብይ ሆይ የወያኔ ዘመን ቁማርን ዛሬም ባትጫወቱት ጥሩ ነው! በዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ ከዛም የዘለለ ብዙ የዘለቀ ተሳትፎ አለኝ፡፡ የጤፍን ፓተንት ከመጽደቁ በፊት ለማስቀረት በላቦራቶሪ የተደገፈ መረጃ ለሚመለከተው ሁሉ ሰጥቻለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ የባዮ ፓይሬት የሕግ ባለሙያም አግኝቼ ጉዳዩን በሕግ ሊከራከር አንደሚፈልግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ሲጀምር የሕግ ባለሙያና ፕሮፌሰር የሆነው ሰው ጉዳዩ ራሱም የሚፈልገውና ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ እንዳለው አስረድቶኝ መረጃውን እንዳዘጋጅ ያበረታታኝ እሱው ነው፡፡ ከሰውዬው ጋር ብዙ ሞክረን በኋላ ላይ ግን ከኢትዮጵያ ወገን እንደ ባለቤት ከሳሽ ሆኖ የሚቀርብ አገርን የሚውክል መንግስታዊ አካል በማጣታቸን ሰውዬውም ተስፋ ቆርጦ ተወው፡፡

ልብ በሉ እኔ ፓተንት ተብሎ የተጠየቀበትን “ግኝት” እውን ትክክለኛ የፓተንት ጠያቂው ኩባኒያ ግኝት ነው ወይስ የጤፍ የተፈጥሮ ባሕሪ በሚል በሰራሁት የላቦራቶሪ ቴስት በእርግጠም የጤፍ ተፈጥሮአዊ ባሕሪ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ውጤቱንም ለሚመለከታቸው ተቋማት አስገብቻለሁ፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ጥበቃና ምርምር እና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲቱት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋማት ቀደም ብለው በጤፍ ጉዳይ ከፓተንት ጠያቂው ጋር የተፈራረሙ ሲሆን ብዝሐ ሕይወት በሰጭነት ግብርና ምርምሩ ደግሞ የዝርያዎቹን ባለቤት፣ ዶ/ር ተወልደብርሀን ገ/እግዚአብሔር፣ የኒዘርላንድ ኤምባሲና ሌላ አንድ ሰው(ኃይሌ ገብረስላሴ ይመስለኛል) በምስክርነት ፓተንት የጠየቀው ካምፓኒ በተቀባይነት ተፈራርመው ነው ጤፍን የሰጡት፡፡ የውሉን ይዘት ፈልጋችሁ አንብቡት፡፡ እኔ በየቧሕነት ነበር መረጃውን መስጠት የሞከርኩት፡፡ ጉዳዩ ግን ብዙ ቁማር እንዳለበት ነው በኋላ የገባኝ፡፡ ይሄን ጉዳይ የማያውቅ ባለሙያ ሆነ የሚመለከተው ተቋም የለም፡፡ ዶ/ር ተወልደን በስልክ አውርተናል፡፡ ሌሎቹን ተቋማት በአካል ተገኝቼ የላቦራቶሪ ውጤቱን መረጃ ከመስጠቴም በላይ ስለሁኔታው በወቅቱ ኃላፊ ከሆኑት ሁሉ ጋር አስረድቻቸዋለሁ፡፡ ጉዳዩን ሁሉም እኔ ፊት ያደንቃል ግን ውስጥ ውስጡን ቁማር ነበር፡፡ ለብዝሐ ሕይወት የላቦራቶሪውን ውጤት ስሰጣቸው ሊያምኑኝ አልቻሉም ነበር፡፡ በኋላ አንድ ቡድን ከእኔ ጋር ወደሰራሁበት ላቦራቶሪ ወስጄ አይናቸው እዛው ውጤቱን በቀጥታ ከመሳሪያው አንበበዋል፡፡ በወቅቱ ሁሉም የድንፋታ አይሉት ምን ይሄማ በሰፊው መሠራት አለበት ብለው ተመልስው አንዳች ነገር አላደረጉም፡፡ ይሄን አልተደረገም የሚል ካለ እኔንና የየተቋማቱን ተወካዮች በሕዝብ ሚዲያ ያገናኘንና ውሸት ነው ይበሉ፡፡ ነገሩን ማስተባበል በማይቻበት መለኩ ነው አሁንም መረጃው ያለኝ፡፡ ከዛ በኋላ ብዙ የኢሜል ልውውጦችም አድርገን ነበር ግን ማንም ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ጭራሽ የእኔን ውጤት ለማናናቅ ብዙ የሞከሩ አሉ፡፡ ሊሰራው አይችልም ዝም ብሎ ነው ብለው አስበው ማለት ነው፡፡

ከፓተንት ጠያቂው ካምፓኒ ባለቤትም ጋር ብዙ ተዳርሰናል፡፡ እኔ ውጤቱን ለብዙ ሰዎች አሰራጭቼ ስለነበር የእኔን ኢ-ሜይል ማን እንደሰጠው ባላውቀም ወይም ሼር ከተደረገ መልዕክትም አግኝቶት ሊሆን ይችላል፡፡ በቀጥታ ጽፎልኝ ከዛ በኋላ ብዙ ጦርነት የመሰለ መልዕክት ነው የተለዋወጥነው፡፡ ሰውዬው የንቀቱ ንቀት ኢትዮጵያ ውስጥ እሱ ፓተንት የጠየቀበትን ጉዳይ ሊያሳውቅ የሚችል መሳሪያ የለም ብሎ ያምናል፡፡ ከዛም በላይ የእኛን የእውቀት ደረጃ ታች ያወርደዋል፡፡ እኔ ባለሙያ ነኝ ከዛም በላይ ተመራማሪ ነኝ፡፡ መሳሪያ የተባለው እርግጥ ብዙ ለፍቼ ነው ያገኘሁት፡፡ የተባበሩኝን አመሰግናቸዋለሁ፡፡ መሳሪያው ግን ጥቂት  የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች (ትልልቆቹን ማለቴ ነው) ወሳኝ ስለሆነ ነበራቸው፡፡  እኔም ከእነዚህ በአንዱ ነው ያገኘሁት፡፡ ውድ ሆኖ አይመስለኝም ግን እዛ ላይ የሚሰራ ስለሌለ እንጂ፡፡ ለዛም ይመስላል የሰውዬው ንቀታዊ ግምት፡፡

ይሄ ሁሉ የሆነው ፈበረንጆች 2008 ፓተንቱ ከመጽደቁ በፊት ነው፡፡ ግን ፓተንቱ ቀርቦ ከሳሽ ሊኖር ከቻለ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ነው፡፡ በዛው ዓመት ወይ በአመቱ  ኖቬምበር ላይ መሰለኝ ፓተንቱ  የጸደቀው፡፡  እንግዲህ አስተውሉ ዛሬ 2019 ላይ ነን፡፡ ጉዳዩ እንደውም ከ2004 ጀምሮ ነበር፡፡ እሱንም ሳሰብ የበለጠ ያበሳጫል፡፡ የሚያናድደው ጉዳዩን አንዲህ በማራዘም ብዙ ገንዘብ እየባከነም ነው፡፡ ከዛ በኃላ  በጨበጣ ፓተንት እናስቀራለን ብለው ሲዳክሩ የነበሩበት ወቅት ብዙ ነው፡፡ ምን አለፋችሁ በየአመቱ የጤፍን ፓተንት ወሬ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ሰዎች ውጭ ድረስ እየሄዱ የመጣሉ ብዙ ብዙ፡፡ ጉዳዩ ግን በጣም ቀጥተኛና አጭር ነው፡፡ ፓተንት የሚከሰሰው በመረጃ ነው፡፡ በጨበጣና በፖለቲካ አደለም፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን የፈረሙትንም ውል ማስጠበቅ አልቻሉም፡፡

ለማንኛውም ዛሬ አብይን ይሄን ጉዳይ እንዲያስበበት እናገራለሁ፡፡ እንግዲህ 10 ዓመት በላይ ሲቆመርበት የኖረውን ጉዳይ ሊያስቆመው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እርግጥ ነው ፓተንቱ በጣም አናዳጅ ነው፡፡ ለእንደኔ ያለ ባለሙያ፡፡ ምክነያቱም የቴፍ ተፈጥሮአዊ ባለቤት ለዘመናት ተንከባክበው እዚህ ያደረሱት የኢትዮጵያ ገበሬዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የገበሬዎች ባለቤትነት በብልጣብልጦች እንዳይነጠቅ ዓለማአቀፋዊ ሕጉ አንድም የብዝሀ ሕይወት ሀብት ፓተንት እንዳይደረግ ይከለክላል፡፡ ካምፓኒው ይሄን ያውቃል፡፡ ስለዚህ የጤፍን ዱቄት በልዩ ሁኔታ ለዳቦና ለመሳሰሉት ምግቦች እንዲሆን አደረኩ ነው ያለው፡፡ እንደ ፓተንቱ ጤፍ በተፈጥሮ የዛን አይነት ባሕሪ የለውም፡፡ ይሄንንም በቁጥር በተገለጸ መረጃ አቅርቧል፡፡ የእኔ ድርሻ የነበረው ይሄ ሰውዬው የሚለው ቁጥር (እንዲገባችሁ ነው ጉዳዩ አሚሌስ አክቲቪቲ ይባላል፣ አሚሌስ ምራቃችን ውስጥ ያለ ኢንዛይም ነው አንዴት አንደሚገናኝ እዚህ አላብራራም)እውን ጤፍ በተፈጥሮ የሌለው ሆኖ ሰውዬው ዱቄቱን በማሻሻል የሚፈለገውን ጥራት እንዲኖረው አድርጓል አላደረገም የሚለውን ማጣራት ነበር፡፡ ከ20 በላይ ዝርያዎችን ሰርቼ አብዛኞቹ ሰውዬው ከሚለው ቁጥር በላይ በተፈጥሮ ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱም እንኳን ቢኖረው ፓተንቱ በጤፍ ሥም ተቀባይነት አያገኝም፡፡ የተፈጥሮ ባሕሪን ፓተንት ማረግ አይቻልም፡፡ ግን ጉዳዮን ማን ባለቤት ይሁነው፡፡ ሚስኪኑ ገበሬ አንግዲህ አውሮፓ ሄዶ አይከራከር፡፡ ካምፓኒው ግን ጤፍን አስመልክቶ ብዙ ጥሩ ሥራዎችን ሠርቷል የቱንም ያህል የፓተንቱ ነገር ማጭበርበር ቢሆንም፡፡ እሱም የሆነው በኢትዮጵያ ቁማርተኞች ምክነያት ነው፡፡

አብይ ሆይ ይሄን ቁማር ማስቆም ትችላለህ ወይስ በሚቀጥለውም አንዲሁ እየተቆመረ አንደገና ይሄን ከዳር ለማድረስ በሚል የሆነው ሳያንስ ሌላ ዝርፊያ ጉዳዩን እንከታተለላልን በሚል ይቀጥል? በዚህ ጉዳይ ሊያናግረኝ የሚችል ማንኛውም የሕዝብ መገናኛ ብዙሐን በሳተናው በኩል ኢ-ሜይሌን ማግኘት ይችላል፡፡

አመሰግናለሁ!

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.