‘የተሸፈነው ክረምት’ እና ‘የተጋረደችው ኢትዮጵያ’!

(የአልበርት ካሙና (Albert Camus) የእኔ የርሱ ተማሪ ምናባዊ ጭውውት!

አልበርት ካሙ – “ውዴ ሆይ! በጥላቻ መሃል የተዳፈነ ፍቅር በውስጤ እንደነበረ ተረዳሁ:: (My dear, In the midst of hate, I found there was, within me, an invincible love).

እኔ የሱ ተማሪ – በጎሣ ፓለቲካ ጥላቻ መሃል የተዳፈነ የኢትዮጵያ ፍቅር እንደነበረኝ ተገነዘብኩ።

አልበርት ካሙ – በእንባዬ ዘለላዎች ውስጥ የተደበቀ ፈገግታ በውስጤ መታጨቁን አወቅኩኝ:: (In the midst of tears, I found there was, within me, an invincible smile).

እኔ የሱ ተማሪ – በእንባዬ ዘለላዎች ውስጥ የማይመክንና የተደበቀ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያውያን እምቅ ፈገግታ መኖሩን ተረዳሁ።

አልበርት ካሙ – በተደበላለቀ ሁከት ውስጥ የታመቀ መረጋጋት በውስጤ እንደነበረ ተገነዘብኩ:: (In the midst of chaos, I found there was, within me, an invincible calm).

እኔ የሱ ተማሪ – በተተራመሠ የጎሣ ፓለቲካና የጎጥ ፓለቲከኞች ከሚፈጥሩት ሁከትና ከሚረጩት መርዝ ባሻገር መድሐኒቱ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ ትዕግስት መኖሩን በመረጋጋት ውስጥ ተከልዬ አወኩኝ።

አልበርት ካሙ – በዚህ ሁሉ መሃል መረዳት የቻልኩት በተሸፈነ ድቅድቅ ክረምት ውስጥም የተሸሸገ በጋ በውስጤ ተዳፍኖ መኖሩንና ማግኘቴን ነው:: (I realized, through it all, that…In the midst of winter, I found there was, within me, an invincible summer(.

እኔ የሱ ተማሪ – ከዚህ ሁሉ እንቆቅልሽ ውስጥ መገንዘብ የቻልኩት በጎጥ ፓለቲከኞችና መንጋዎቻቸው ከተሸፈነና ከተጋረደ ምስቅልቅል ባሻገር እንደ አበባ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ኢትዮጵያዊነት የማግኘቴን ጉዳይ ሳስብ ኢትዮጵያስንት በውስጤ እንደ አመድ ተዳፍኖ ያለ መሆኑን ነው።

አልበርት ካሙ – ይህቺ ዓለም ምኑንም ያህል በኔ ውስጥና በኔ ላይ ክፉ አደጋን ብትጋርጥ አንድ ጠንካራና የተሻለ ነገር ከፊቴ የመኖሩ ጉዳይ ልቤን ዳግም በተስፋ ሞልቶት ደስተኛም አደረገኝና ወደ መረጋጋትም መለሠኝ:: ( And that makes me happy. For it says that no matter how hard the world pushes against me, within me, there’s something stronger – something better, pushing right back).

እኔ የሱ ተማሪ – በዚህች የኔ ሐገረ-ኢትዮጵያ ምኑንም ያህል በታኙ የጎጥ ፓለቲካ ክፉ አደጋን ቢጋርጥም አንድ ጠንካራ፣ የሕግ የበላይነት የሠፈነባትና የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከፊቴ የመኖሯ ጉዳይ ልቤን ዳግም በተስፋ ሞልቶት ደስተኛም አደረገኝና ወደ መረጋጋትም መለሠኝ።

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት ትላንትም ይሁን ዛሬ ነበሩ። አሉ። ወደፊትም ይኖራሉ። ምኑንም ያህል የጎጥ ፓለቲካ ሐገሬ ኢትዮጵያን ቢያጎሣቅላትና ቢገፋት በእኩልነትና በመተሣሰብ የምታኖረን የተሻለች ሐገረ-ኢትዮጵያ ከፊቴ እንደምትጠብቀኝ አሰብኩ። ይህ እኔን ክፉኛ አስደሰተኝ።

ኢትዮጵያ ትተክዝ ይሆናል እንጂ አታነባም። ትሸሸግ ይሆናል እንጂ አትጠፋም!

ኢትዮጵያዊነት የክብር ማንነት ነው!

Hailu AT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.