የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው? በዲያቆን ዳንሄል ክብረት

በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብ ነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑን በወጉ መግለጥ ነው፡፡
ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችን ግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነት ኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮ ፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡ የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?
ዜጎቹ በሕገ ወጥ መንገድም ይሂዱ በሕጋዊ፣ ድንበር ጥሰውም ይሂዱ በአውሮፕላን ተሳፍረው፤ መጀመሪያ ሰዎች፣ ቀጥሎም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸውና ኀዘን ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚያስበው ክብር አንዱ በሞቱ ጊዜ የክብር ልቅሶና ኀዘን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአካባቢያቸው ላለመራቅ፣ ከራቁም ለመመለስ ከሚሰጧቸው ምክንያቶች አንዱ ‹በክብር ዐርፎ በክብር መቀበርን፣ የክብር የኀዘን ሥነ ሥርዓትን ማግኘትን› ነው፡፡
ካገሬ እንዳወጣህ አገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ፤
እንኳን የሚቀብረው የሚያዝንለት አጣ
ምን ወግ ማረግ ያያል ካገሩ የወጣ፤
የሚሉት ለዚህ ነበረ፡፡
የመንግሥት አካላት ለምን ይኼንን ለመዘንጋት እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ቃጠሎና ግድያ ሲመጣ የሀገራችን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ብለው ‹‹በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ነገር ከልብ እናዝናለን፣ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ተነጋግረን አስፈላጊውን እናደርጋለን፤ ተመሳሳይ ችግር ለወደፊቱ እንዳይከሰትም አንሠራለን› ዓይነት ሰውነት ያለበት መግለጫ ጠብቄ ነበር፡፡ የለም፡፡ ሲሆን በሀገራችን የልቅሶ ሥነ ሥርዓት መሠረት፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም ያወቀው አሸባሪ ‹አይ ሲስ› ኢትዮጵያውያኑን በክርስትና እምነታቸው ብቻ ሲሠዋቸው የተሰጠው መግለጫ ስሜት የሌለበት፣ ማዘን መደሰታቸውን የማይገልጥ፣ እንኳን ሰው እንስሳ የሞተብን የማያስመስል ሆነ፡፡ ከማጣራቱም ከምኑም በፊትኮ ስሜቱ ይቀድማል፡፡፡ አዝናችኋል ወይ? ስትሰሙና ስታዩ ምን ተሰማችሁ? የአሜሪካ መንግሥት እንደዚያ ዓይነት መግለጫ ሲያወጣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ያንን ነው ወይ መስማት ያለብን? ለመሆኑ መሪዎቻችን ኀዘናቸውን የሚገልጡት ምን ስንሆን ነው? ለምንድን ነው ሁሉም ነገር ፖለቲካ የሚሆነው?
ሁለተኛው የሚጎድለው ነገር ደግሞ ፍጥነት ነው፡፡ አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ ሲያሸንፉ የባለሥልጣናቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ሯጮቹ ቆርጠውት ካለፉት ሪቫን ቀጥሎ የሚመጣ ዜና ነበር፡፡ አትሌቶቹ ደክሟቸው ከመሬት ሳይነሡ የባለሥልጣናቱ መልእክት ለሚዲያ ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ የሁላችንም ኀዘን በሆነው ጉዳይ ግን ለምን መዘግየት እንደተመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ ማጣረቱ፣ መረጃ መሰብሰቡ፣ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን መሄዱ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ማዘን ግን ጊዜ አይወስድም፡፡ ቪዲዮው ተለቅቋል፡፡ ሲሞቱ እያየን ነው፡፡ መልካቸው የኛው ነው፡፡ አይሲስ የገደላቸው ‹ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች› ብሎ ነው፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ያንኑ እያስተጋቡ ነው፡፡ ይኄ ለኀዘን ያንሳል? አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ‹በሆነው ነገር እናዝናለን፤ ልባችን ተነክቷል፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፤ ዝርዝሩን በየጊዜው እንነግራችኋለን› ለማለት ስንት ሰዓት ይወስዳል? የደቡብ አፍሪካው ችግር ደረሰ እንደተባለ ሙጋቤን ለውግዘት የቀደማቸው የለም፡፡ የኛዎቹስ የት ሄዱ?
መንፈሳዊ መሪዎችስ የት ናቸው? አንዳንዶቹ ውጭ ሀገር መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ ሲሆን ይህንን ሲሰሙ አቋርጦ መምጣት፤ ካልሆነም ባሉበት ሆኖ አባታዊ ኀዘንን መግለጥና በእምነቱ የሚገባውን ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ሲኖዶሱስ ምን እየሠራ ነው? አልሰማም ይሆን? ዛሬ ጠዋት ቢያንስ በአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎት መደረግ አልነበረበትም? ባፈው ካይሮ ሄዳችሁ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው ያያችሁት? በጎቹ እረኛ የላቸውም ማለት ነው? አባቶች የሚያዝኑት ምን ሲገጥማቸው ነው? እረኛው የሚያለቅሰው ስንት በጎች ሲታረዱ ነው?
ቤተ ክርስቲያኒቱ ነገሩን በዝምታ የምታልፈው ከሆነ እኛ እንደ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ቀኖና እነዚህን በክርስትናቸው ምክንያት የተሠው ክርስቲያኖች ‹ሰማዕታተ ሊቢያ› ልንላቸው ይገባል፡፡ የሰማዕትነታቸውንም በዓል ማክበር አለብን፡፡ በስንክሳሩ ማስገባት ባንችል ታሪካቸው በኅዳጉ ማስፈር አለብን፡፡ ማንም ይሁኑ ማን፣ በሚገባ የተማሩም ይሁኑ ያልተማሩ፣ ከመካከላቸው የማያምኑም እንኳን ቢኖሩ የተገደሉበት ምክንያት ክርስትና ነውና ሰማዕታት ናቸው፡፡ ያውም ‹ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት›፡፡ በስንክሳሩ እንደምናነበው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የክርስቲያኖች መንደርና ቤተ ክርስቲያን እየተወረረ ክርስቲያኖቹ ሲሠው ገና ያልተጠመቁት፣ ነገሩ ያልገባቸው፣ ክርስትናን ለመቀበል ያልወሰኑት ሁሉ አብረው ተሠውተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የተሠውበት ምክንያት ክርስትና በመሆኑ ሁሉንም ሰማዕታት ብላቸዋለች፡፡ የእነዚህም ክብር እንዲሁ ነው፡፡
እነርሱ በሰማይ ዋጋ አላቸው፡፡ አክሊለ ሰማዕታትንም ተቀብለዋል፡፡ እኛ ግን ሰማዕታቱን ባለማክበራችን ክብር ይጎድልብናል፡፡ ‹በረከታቸው ይደርብን› እንጂ ‹ነፍስ ይማር› አንልም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.