በደ/ጎንደር ዞን 3 መስጅዶች ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአፋጣኝ እንዲወጣ ተጠየቀ 

በሐይማኖት ሽፋን ህብረተሰቡን ለማጋጨትና ለማተራመስ አላማ ያደረጉ ቡድኖች በክልሉ ደቡብ ጎንደር ዞን 3 መስጅዶች ላይ የፈፀሙትን የማቃጠል ድርጊት እንደሚያወግዝ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ ሙሐመድ በሰጡት መግለጫ ድርጊቱ በክልሉ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በሰላምና በፍቅር የመኖር ባህልን ለመሸርሸር ታልሞ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ በፍጥነት እንዲያከናውን ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

በተለይ ደግሞ ባለፉት ቀናት በተቃጠሉት መስጅዶች ዙሪያ እየተካሄደ ያለው የምርመራ ጊዜ መውስዱን ተከትሎ አፋጣኝ የሆነ የምርመራ ሂደት ተደርጎ ፍትህ እዲረጋገጥም ጠይቀዋል፡፡

በሀገራችን የእስልምና እና የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ተከባብረው በፍቅርና ሰላም እየኖሩ አንድነታቸውን አሳይተዋል ያሉት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ ሙሐመድ ፣ መስጂድ በማቃጠል ሽፋን የማጋጨት አላማው የሚሳካ አይደለም ብለዋል፡፡

ልዩነት የሚፈልጉ አካላት ሀገሪቱን ወዳልሆነ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚያደርጉት ጥረት በመሆኑ፣የእነዚህን አካላት ድርጊት ህብረተሰቡ በማውገዝ በአንድነት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ችግሩ በተከሰተበት ቦታ ድረስ በመሄድ የእስልምና ሐይማኖት መሪዎች ፣የክልሉ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና የመንግስት አካላት በተገኙበት የማረጋጋት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቀጣይ የድጋፍ ስራዎችና በተለይ ደግሞ ህግ የማስከበር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጠይቋል፡፡

በራሔል ፍሬው/EBC (ከባህርዳር )

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.