ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አለ ከተባለ የገዥዎች እንጅ የስርዓት አይመስልም (ከህዝባዊ ሰልፉ)

(በአንድ ወቅት “…አዲስ ንጉስ እንጅ ለውጥ መቸ መጣ…” ብሎ የዘፈነው ኢትዮጵያዊ ጀግና ማን ነበር???)

ባለፉት 27 አመታት የህወሃት ሰዎች የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን እንዲሁም የማህበራዊውን መዘውሮች (መሪዎች) ጨብጠው ሃገሪቱን ሲያሾሯት ብቻ ሳይሆን ሲያላሽቋት እንደነበር ሁላችንም እናቃለን። በነገራችን ላይ ዘለቄታው ሳያምር ቀረ እንጅ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት ሁሉም እስረኞች ተፈቱና እስር ቤቶች ኦና (ባዶ) ሆኑ። እንዲያውም በወቅቱ አንዳንዶች ሲቀልዱ እስር ቤቶች ሁሉ ወደ አምስት ኮከብ ሆቴልነት ሊቀየሩ ነው ይሉ ነበር። ትንሽ ቆየት ካለ በኋላ ግን ስልጣንን በተደላደለ መንገድ ለማስቀጠል ደንቃራ ናቸው ተብለው የተገመቱ ሰዎች እየተለዩና ስም እየተለጠፈባቸው ወደ እስር ቤት መወርወር ጀመሩ። አንዳንዶቹ የኢሰፓ አባላት ሌሎቹ ደግሞ ቅንደኛ ቢርክራቶችና የደርግ ርዝራዦች ናቸው በሚል የህግ ሂደትን ባልተከተለ መንገድ ጭምር ወደማጎሪያ ቤት ተላኩ።

ከዚህ ሌላ በወቅቱ በውጭም በውስጥም የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሽግግር መንግስቱ ምስረታ እንዲሳተፉ ተደረገ። ነፃ ውድድርም ይደረጋል በሚል ሁሉም ሰው ተስፋ ሰነቀ። ትንሽ ቆየት ካለ በኋላ ግን ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ትክክለኛ የሆኑም ያልሆኑም ሰበቦች በመደርደር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳደድ ጀመረ። በዚህ ረገድ በመጀመሪያ ረድፍ ሊጠቀስ የሚችል ፓርቲ ኦነግ ነው።

ጋዜጦችም እንደጉድ ፈልተው እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ እያመሩ ካሉ ሃገራት አንዷ ተደርጋ መቆጠር ጀምራ ነበር። በኋላ ላይ ግን ለህወሃት ሰዎች ስልጣን ሳይመቹ ሲቀሩና መጎርበጥ ሲጀምሩ ህግን በመጠቀም እንዲሳደዱና እንዲኮሰምኑ ተደረገ፤ ሄደው ሄደውም ድራሻቸው ጠፋ።

ከኤርትራ ጋ የነበረው ግንኙነትም ቢሆን ሽር ብትን ያለ ነበረ። አቶ መለስ ከአቶ ኢሳያስ ሌላ አቶ ኢሳያስም ከአቶ መለስ ውጭ ሌላ ሰው የሌለ እስኪመስላቸው ድረስ ግንኙነታቸውን አጎኑት። እንዲያውም ቡዙዎቹ እንደሚሉት አቶ ኢሳያስ ቢኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አማካሪና ወሳኝ ሰው ተደርገው እስከመወሰድ ደረሱ። በዚህም ምክንያት አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ በብዙ የአውሮፓ አገራት ምርጥ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች በመባል ተወደሱ። አለመታደል ሆኖ ግን አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያን ሃብት በመጠቀም ኤርትራን እንደሲንጋፖር አደርጋለሁ በሚል እሳቤ ፈር የለቀቁ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ርምጃወች መውሰድ ሲጀምሩና ከዚህ አለፍ ብለውም ራሳቸው አቶ ኢሳያስ በሰጡት ትዕዛዝ በተፈፀመ የድንበር ወረራ ምክንያት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት እንዳይሆኑ ሆኖ ከረመ።

በሌላም በኩል የተለያዩ ፖሊሲዎች፤ ህገመንግስትን ጨምሮ ሌሎች የሃገሪቱ ህጎች፣ ደንቦች መመሪያዎቻና አሰራሮች ያለ ህወሃት ሰዎች ችሮታ ወይም ቡራኬ ሊወጡ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልፅ እየሆነ መጣ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሚከራከሩት ህገመንግስቱም ይሁን ሌሎች ህጎች ብሎም ፖሊሲዎች የፈለቁትና የሚፈልቁት ከህወሃት ፕሮግራምና ህገደንብ ነው በሚል ማስረጃ እያስደገፉ ሲከራከሩ ይደመጣሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎን የፀጥታ ሃይሉን የተቆጣጠሩት የህወሃት ሰዎች እንደነበሩ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። መከላከያው፣ የደህንነት ተቋሙ እንዲሁም የፖሊስ ሃይሉ በዋነኛነት ይታዘዙና ይመሩ የነበሩት በህወሃት ሰዎች ነው። የነዚህ የፀጥታ ሃይሎች የዘወትር ተግባር ደግሞ የህወሃት ሰዎችን ጥቅም ማስከበር ነበር። አንዳንድ ቦታ ያሉ የፀጥታ ሃይል ተቋማት ላይም መግባቢያ የነበረው ቋንቋ ትግርኛ ከመሆኑ አንፃር መቀሌ ከተማ እንጅ አዲስ አበባ ያሉ አይመስልም ነበር።

ኢኮኖሚውን የመዘወር እድሉ ተመቻችቶላቸው የነበሩትም የህወሃት ሰዎችና በዙሪያቸው ያሉ ደጋፊዎቻቸው ነበሩ። በዚህ ረገድ ሰፋፊ እርሻ፣ ትላልቅ ህንፃዎች፣ ዘመናዊ ፋብሪካዎችና ማሽነሪዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌላቸው የንግድ ተቋማት እንዲሁም የባንክ ብድር ተጠቃሚዎች በህወሃት ዙሪያ የተኮለኮሉ ሰዎች እንደነበሩ ፀሃይ ላይ የተሰጣ ሃቅ ነው። በዚያ ላይ እነዚሁ የህወሃት ሰዎች ኤፈርት (EFFORT) በሚባል ግዙፍ የንግድ ተቋም አማካኝነት የኢትዮጵያን ብሎም የምስራቅ አፍሪካን አለፍ ካለም የአፍሪካን ኢኮኖሚ በሞኖፖል በመቆጣጠር እንደፈለጉ ሊፈነጩ ይችሉ ዘንድ ያልፈነቀሉት ደንጋይ አልነበረም። ኢኮኖሚውን በተመለከተ ግን አንድ ሊካድ የማይችል ሃቅ አለ። ይህም ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በልማት ዙሪያ ያስመዘገባቸው ለውጦች አለምን ያስደመሙ መሆኑ ነው።

በማህበራዊ ሁኔታም ቢሆን የህወሃት ሰዎች ከፍ ብለው ለመታየት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። በዚህ ረገድ የአሸንዳ ባህልን በተመለከተ ምን ሲያደርጉ እንደነበረ ይታወቃል። ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ይህ ባህል የሚታወቀው ትግራይ ውስጥ ብቻ አይደለም። አማራ ክልልም በስፋት የሚዘወተር ባህል ነው። ይሁን እንጅ የህወሃት ሰዎች ጊዜው የኛ ነው በሚል እሳቤ በተለያዩ ክልሎች አሸንድያ፣ ሻደይ ወይም አሸንዳ ተብሎ የሚታወቀውን ባህል የትግራይ ብቻ እንደሆነ አድርገው በፌዴራል ደረጃ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ እንዲከበር በማድረግ ሊጠልፉ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። በውጭ ሃገርም ቢሆን ትግራይን ብቻ የሚወክል ባህል ተደርጎ እንዲቆጠር ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ እንደነበር አንዳንድ ጉዳዩን በትኩረት የሚከታተሉ  ያገባናል የሚሉ ሰዎች ይገልፃሉ።

በዚሁ የ27 አመታት ጉዞ ወቅት የህግ የበላይነት፣ በህግ ፊት እኩል የመታየትና እኩል ጥበቃ የማግኘት መብቶች ለህወሃት ሰዎችና ለደጋፊዎቻቸው ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያ ህዝብ ባይተዋር ነበሩ። የስብአዊ መብት ጥሰትም ጫፍ ደርሶ እንደነበር ሁሉም የሚያቀው ጉዳይ ነው። የተቋማት ግንባታ፣ ገለልተኝነትና ሚዛናዊነትም በዲስኩር እንጅ በተግባር ኢትዮያን ሲያልፉም አይነኳት ነበር። ከተቋማት ይልቅ የግለሰብ መሪ ተክለሰውነት ግንባታ ላይ ያተኮረ ሂደት ትልቁን ቦታ ይዞ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት አቶ መለስ አድርጋጊ ፈጣሪ ሆነው በህይወት ዘመናቸው ብቻ ሳይሆን ካለፉ በኋላም አገርን በፈለጋቸው መንገድ ሲያሽከረክሩ የነበሩ መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም።

እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከዚህ በላይ የተገለፁት አይን ያፈጠጡና ጥርስ ያገጠጡ ችግሮች ሲፈጠሩ ኧረ ይህ ነገር አያዋጣም፤ የፌዴራል መንግስቱ በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው ከሚለው ህገመንግስታዊ መርህ ጋር ይጣረሳል የሚል ሃሳብና ጥያቄ ሲነሳ ይህ አይነት ሃሳብና ጥያቄ የትምክህተኛ፣ የጠባብ፣ የነፍጠኛና የደርግ ኢሰፓ ነው የሚል አንገት ማስደፊያ ጥቅም ላይ ውሎ ቆይቷል። የሚገርመው እንደዚህ አይነት መልስ ይሰጥ የነበረው በህወሃት ሰዎች ብቻ ሳይሆን የነሱ ጋሻ ጃግሬ በነበሩት በሌሎቹ ድርጅቶች አመራሮችም ጭምር መሆኑ ነው። አሁን “የለውጥ ሃይል” ነን የሚሉት እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና እነ አቶ ደመቀ መኮነንም ቢሆኑ ከአንገት አስደፊዎቹ ውስጥ ፊታውራሪዎቹ ነበሩ። በሌላ በኩል ዶ/ር አብይም ሆነ አቶ ለማ ብሎም ዶ/ር አምባቸውም አንገት አስደፊ የነበሩ መሆናቸውን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም የህወሃት ሰዎች ዋነኛ ተባባሪዎች ካልሆኑም ጋሻ ጃግሬዎች የነበሩ መሆናችው አጠያያቂ አይደለም።

ይሁን እንጅ የችግሮቹ ስፋት፣ ክብደትና ጥልቀት አንገት በመድፋት ብቻ ሊታለፉ የማይችሉ ስለነበር ህዝቡ ባደረገው መራራና ፈታኝ ትግል የህወሃት ሰዎች ወደ ድንኳናቸው እንዲገቡ አደረገ ። በምትኩም ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ኮርቻው ላይ መቆናጠጥ ጀመረ። በዋነኛነት ደግሞ የኦህዴድ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለታቸው አልቀረም። ህዝቡም የስርዓት ለውጥ ተስፋ ሰነቀ። እሱን ተከትሎም ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከደርግ መንጋጋ ፈልቅቆ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር እንዳደረገው አገር ውስጥ የነበሩ እስረኞች ሁሉም ባይሆኑ እንዲለቀቁ ተደረገ። ከዚህ አልፎም ከሃገር ውጭ ታስረው የነበሩ እስረኞች እንዲፈቱ በተደረገ ጥረት በተለያየ አገር የነበሩ የተወሰኑ እስረኞች ተፈተው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ሆነ። ማዕከላዊ ተዘግቶም ሙዚየም እንዲሆን ተወሰነ። ልዩነቱ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በደርግ ታስረው የነበሩ እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ ያደረገ ሲሆን በኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ወቅት የተደረገው ግን በከፊል መሆኑ ነው።

ዋል አደር እያሉ ሲሄዱ ግን ልክ የህወሃት ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ የኦህዴድ ሰዎችም ስልጣናችን እንዳይደላደል ደንቃራ ይሆናሉ ብለው የሚጠራጠሯቸውን ሰዎች “የቀን ጅቦች፣ ፀጉረ ልውጦች፣ የኦሮሞ ጥላቻ ያላቸው፣ ኦሮሞ መምራት አይችልም የሚሉ” በሚል ቅስቀሳ በመጀቦን የተለያዩ ወንጀሎች እየለጠፉ ሰዎችን ማሸማቀቅና ብሎም እስር ቤት መወርወር ጀመሩ። የኦህዴድ ሰዎች በኛ ዘመን ሰው የሚታሰረው በቂ ማስረጃ ከተሰባሰበ በኋላ ነው እንዳላሉ ሁሉ የተገላቢጦሽ በሆነ መንገድ አስረው በተደጋጋሚ የ14 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ እስኪሰለቸን ድረስ መስማት ጀመርን። በሌላም በኩል ያለፍርድቤት ትእዛዝ ዜጎችን በጅምላ ወታደራዊ ካምፕ አጉሮ የተሃድሶ ስልጠና ሰጠሁ ያለንም በዋነናነት በኦህዴድ ሰዎች የሚመራው የፌዴራል መንግስት አካል ነው።

ፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተም የህወሃት ሰዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ እንዳደረጉት ሁሉ የኦህዴድ ሰዎች ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ሃገር ውስጥም ሆነ ሃገር ውጭ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ነው። በርግጥ አሁንም እውቅና እየተሰጥችው ያሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላለው ስርዓት ታማኝ መሆናቸውን ያረጋገጡ ብቻ እንደሆኑ የሚያሳዩ ምልክቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ይህን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅሬታ እያቀረቡ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እየሰማን ነው። ተገዳዳሪ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ እንደ ኦነግ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እየቀረቡ የመገፋት ሙከራ እየተደረገባቸው እንደሆነ እያየን ነው። ይህ ሲባል ግን ኦነግ ድሮም ሆነ አሁን ከችግር የፀዳ ፖለቲካ ፓርቲ ነው ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል።

ወደ መገናኛ ብዙሃን ስንመጣም ልክ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ የስልጣን አመታት እንደተደረገው ሁሉ ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግም ብዙ የመገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠሩ አስችሏል። በርግጥ የኦህዴድ ሰዎች እንደ ህወሃት ሰዎች ሁሉ የመገናኛ ብዙሃን እንዲኖሩና እንዲጠናከሩ የሚፈልጉት  እነሱን እስካልነኳቸው ድረስ እንደሆነ የሚመስሉ ነገሮችን እየታዘብን ነው። ለዚህም ኢ ኤን ኤን የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም እንዲከስም የተደረገበት መንገድና አሁንም የማህበራዊ ሚዲያን ለማቀጨጭ የሚያስችሉ የህግ ስርዓቶችን ለመዘርጋት እየተደርጉ ያሉ ጥረቶችን መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው። በመንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ልክ እንደወትሮው ሁሉ ባሉበት ዘመን ያለን መንግስትና የመንግስት ሰዎች በማወደስና በማንቆለጳጰስ ስራ ውስጥ ተጠምደው እንዳለ ግልፅ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

የህግ የበላይነት እና በህግ ፊት እኩል የመታየት መብቶችን ጉዳይ ስናይ በህወሃት ሰዎች ዘመን እንደነበረው ሁሉ አሁን ባሉት የኦህዴድ ሰዎች ዘመንም ለኢትዮጵያውያን እንግዳ እንደሆኑ ናቸው። ባሁኑ የኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ዘመን ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያውም በጅምላ በጅምላ ሲታሰሩ አይተናል። በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈፀመን ህገወጥ ድርጊት ማስታወስ በቂ ነው። አንዳንድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችም በዋስ እንዲለቀቁ ሲወሰን አሁንም በመንግስተ የበላይ ሃላፊዎች ትዕዛዝ ከእስር እንዳይለቀቁ የሚደርገበት አሰራር እየተከሰተ እንዳለ በተለያየ መንገድ ሲዘገቡ እየሰማን ነው። ተጠያቂነትን በተመለከተም ባለፉት 27 አመታት የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ  ሁሉ እኩል በሆነ መንገድ ነፃ/ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ ነፃ የመሆን ወይም የተጠያቂነት መስፈርት  የተደመረ/ያልተደመረ ወይም ለውጥ የተቀበለ/ለውጥ ያልተቀበለ የሚል ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በዘመንኞቹ የኦህዴድ ሰዎችና በጀሌዎቻቸው “የለውጥ ሃይል” የሚል ስም የተሰጠው ሁሉ ባለፉት 27 አመታት የቱንም ያህል በወንጀል ድርጊት የተጨማለቀ ቢሆን በነፃ እየተንቀሳቀሰ ያለበት፤ ባንፃሩ ደግሞ  በነዚሁ ዘመንኛ የኦህዴድ ሰዎችና ጀሌዎቻቸው “የለውጥ አደናቃፊ” ነው ተብሎ የታሰበ ሰው መሰረታዊ የሆነ ችግር ሳይኖርበት ሰበብ እየተፈለገ እንዲሸማቀቅና እየተለቀመ እንዲታሰር የሚደረግበት  አግባብ እያየን ነው።

የተቋማት ግንባታን በተመለከተ የኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ልክ እንደህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ሁሉ የረባ ስራ እየሰራ እንዳልሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ልክ አቶ መለስ አድራጊ ፈጣሪ ተደርገው ይቆጠሩ እንደነበሩት ሁሉ አሁን ላይም ዶ/ር አብይ ያፈተታቸውን ማድረግ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው መሆኑን የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው።  በዚህም ምክንያት ዶ/ር አብይ ባንድ ወቅት የተናገሩትን ሌላ ጊዜ ሲቀይሩት፤ ይደረጋል ወይም አይደረግም ብለው ቃል ከገቡት ተቃራኒ የሆነ ነገር ሲሰሩ ጥያቄ እንኳን ለመጠየቅ የሚዳድው ሰው እየጠፋ ነው። አንዳንዴም ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ የሚለው የፈላጭ ቆራጭ መንግስት መርህ የነገሰበት ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው ወይ ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ሁኔታ እየታዘብን ነው። በሌላ አነጋገር አቶ መለስ ከህግና ከተቋማት በላይም በላይ እንደነበሩት ሁሉ ዶ/ር አብይም ቢሆኑ በዚያው ቦይ እየፈሰሱ እንደሆነ ገሃድ እየወጣ መጥቷል።

ወደ ስልጣን ክፍፍል ስንመጣም ልክ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ወቅት የህወሃት ሰዎች የብዙ ፌዴራል መንግስት ተቋማት መሪዎች እንዲሆኑ ተደርገው እንደነበረው ሁሉ አሁን ባለው ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ወቅትም የኦህዴድ ሰዎች ቁልፍ ቁልፍ የፌዴራል መንግስት ሃላፊነቶችን እንዲይዙ እየተደረገ ነው። በዚህ ረገድ መከላከያ ውስጥ ከጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥነት ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ የአመራር ቦታዎች ለምሳሌ ዶ/ር አብይ በተደጋጋሚ በሚመኩበት አየር ሃይል ውስጥ የኦህዴድ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።  በካቢኔ ደረጃ ያለውን የስልጣን ክፍፍል በምናይበት ጊዜም ሃገርን ለመምራት በተለምዶ ቁልፍ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ እንደ ገቢዎችና የውጭ ጉዳይ የመሳሰሉ ተቋማትን በሚንስትርነት ወይም በምክትል ሚንስትርነት እንዲመሩ የተሾሙት አብዛኛዎቹ የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። በደህንነት ተቋሙና በፖሊስ ሰራዊቱ ውስጥም እነዚሁ የኦህዴድ ሰዎች ስር እንዲሰዱ ለማስቻል የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ለማሳየት የሚያስችሉ ምልክቶችን እያየን ነው። በሌላም በኩል የመንግስት ባለስልጣናትንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠብቅ በቅርቡ የተቋቋመው የኮማንዶ ሃይል የሚመራውም በኦህዴድ ሰው እንደሆነ እይየተነገረ ነው። አይደለም መሪው ብዙዎቹ የጥበቃው አባላትም የኦህዴድ ሰዎች ናቸው የሚል ሃሜት እየተናፈሰ ነው።

ወደኢኮኖሚው ስንመጣም የህወሃትና የኦህዴድ መራሾቹ ኢህአዴጎች ተመሳሳይነት እንዳላቸው የሚገልፁ ሰዎች በርካታ ናቸው። በዚህ ረገድ እንደማሳያ የሚጠቀሰው ለኢኮኖሚው ቁልፍ የሆነውን የንግድ ባንክ በፕሬዚደንትነት እንዲመራ የተሾመው የኦህዴድ ሰው መሆኑ ነው። በተጨማሪም ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ ከውጭ እየገቡ ያሉ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ዋነኛ መዳረሻቸው ኦሮሚያ ክልል እንዲሆን እያደረገ እንደሆነ የሚያመላክቱ ማሳያዎች አሉ። በዚህ ረገድ ከዴንማርክ መንግስት በተገኘ እርዳታ የተቋቋመ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ተጠቃሽ ነው።

ከማህበራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይም የኦህዴድ ሰዎች ባህላቸው ከሌላው በተለየ መንገድ ከፍ ብሎ እንዲታይ እያደረጉ ነው የሚል ትችት እየቀረበ ነው። በዚህ ረገድ እየተነሳ ያለው ትልቁ ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለስልጥናት በተለያየ ጉዳይ ላይ ንግግር ሲያደርጉ በሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ባህላዊ ተቋማት ውስጥ ባብዛኛው እንደምሳሌ የሚጠቅሱት የገዳ ስርዓትን ነው የሚል ነው። ከዚህ አልፎም የኦሮሞ አለባበስ ከሌላው ተለይቶ ከፍ ከፍ እየተደረገ ነው በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እንዲያውም ባንድ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኡጋንዳን በጎበኝበት ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል ለኡጋንዳው መሪ ያቀረቡት ስጦታ የኦሮሞ የባህል ልብስ በመሆኑ አስነስቶት የነበረውን አቧራ ማስታወስ ይቻላል።

ሌላው የኦህዴድ ሰዎች የተዛነፈ ስራ እየሰሩ ነው ተብለው የሚታሙበት ደግሞ አዲስ አበባን በተመለከተ ነው። በዚህ ረገድ ያለው የመጀመሪያው ቅሬታ ከንቲባው ኦሮሞ እንዲሆኑ ስለተፈለገ ብቻ ሀግ ተቀይሮ ከሌላ ቦታ መጥተው እንዲሾሙ ተደርገዋል የሚል ነው። ይህን ተከትሎም ከንቲባው የኦህዴድ ሰው ስለሆኑ መዋቅሩንም በኦህዴድ ሰዎች እየሞሉት ነው የሚል ቅሬታ በስፋት ይሰማል። ከዚህ በተጨማሪም ከንቲባው የኦሮሚያን እንጅ የአዲስ አበባን ጥቅም እያስከበሩ አይደለም በሚል የሚወቅሷቸው ነዋሪዎች ቀላል አይደሉም። ከዚህ አንፃር እየተነሳ ያለው ትልቁ ቅሬታ ከኦሮሚያ እየመጡ ላሉ በርካታ ሰዎች ከህግ አግባብ ውጭ መታወቂያ እየታደላቸው ነው የሚለው ነው። ባጠቃላይም የኦህዴድ ሰዎች አዲስ አበባንም ሆነ ኢትዮጵያን ኦሮሞዋዊ (Oromize) ለማድረግ ስትራቴጅ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው በሚል ጃዋር እያሰራጨ ያለውን ዲስኩር በማስረጃነት እያጣቀሱ የሁኔታውን አሳሳቢነትና አደግኝነት በመግልፅ ላይ ይገኛሉ። በዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ-አ.ሁ.ን (Addis Ababa International Movement-A.I.M) በሚል ስም የሚታወቅ ድርጅት ያቀረበውን ዘርዘር ያለ ሃስባ ለማንበብ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

http://www.ahun-et.org/2019/02/09/123/?fbclid=IwAR0N4YtoRW6oY4JlEWeCCSiCZ6VqhtGI-0O8JZBVO6ZVYRU02EbeqEW77JA

ለማጠቃለል ያህል ከዚህ በላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮች በማየት መረዳት የሚቻለው ህዝቡ ባደረገው ፈታኛና መራራ ትግል የህወሃት መራሹን ኢህአዴግ አንኮታኩቶ ቢጥልም የተተካው ግን በኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ እንደሆነ ነው። በዚህም ምክንያት ነው አሁን አለ የሚባለው ለውጥ የገዥዎች መፈራቀቅ እንጅ የስርዓት ለውጥ አይደለም በሚል ብዙ ሰዎች የሚከራከሩት።

ቸር ይግጠመን!!!

3 COMMENTS

  1. እግዚአብሄር ህሊና የሚባል ነገር ለፈጠረልን ሰዎች በዐቢይና መለስ በኦህዴድና ህውሀት መካከል የሰማይና ምድር ያህል ልዩነት አለ:: በቀኝም ነፈሰ ግራ ዐቢይ አሕመድ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ሲሆን መለስ ዜናዊ ኢትዯጵያዊነትን ያልፈለገ መሪ ነበር::
    ለአንተ ” ቡዙ” አልተለወጠም ለእኛ ግን ብዙ ተስፋ እያየን ነው::

  2. ይህ በዉቨት የተሞላ ትርክት እና በማር የተለወሰ መርዝ የያዘ ፅሁፍ ነዉ. ለዉጡ ያለተመቻቸዉ ሰዎች ምንም ብሉ ምን የተጀመረዉን ለዉጥ ማቆም ብሎ መቀልበስ አይችሉም.

  3. ይህ በዉቨት የተሞላ ትርክት እና በማር የተለወሰ መርዝ የያዘ ፅሁፍ ነዉ. ለዉጡ ያለተመቻቸዉ ሰዎች ምንም ብሉ ምን የተጀመረዉን ለዉጥ ማቆም ብሎ መቀልበስ አይችሉም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.