የኦህዴድ ሰዎች ፖለቲካዊ ሰምና ወርቅ፡ ሰሙ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ወርቁ ደግሞ ኦሮሟዊ ይመስላል     (ከህዝባዊ ሰልፉ)

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ሹመታቸውን ያፀደቀላቸው ተሿሚዎች ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ

እንደሚታወቀው የኦህዴድ ሰዎች የስልጣን መንበሩን ለመያዝ ማኮብኮብ ከጀመሩበት አንስቶ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በስብከት ደረጃ አንድ ሽህ አንድ ጊዜ ጠርተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እነዚህ የኦህዴድ ሰዎች ከጅምሩ አንስቶ ኢትዮጵያ ሱሴ ነች፣ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ መኖር አይቻልም፣ እማማ ኢትዮጵያ ብትጎብጭም አልተሰበርሽም፣ ብትመነምኝም አልተበጠስሽም በሚሉ ባማሩና በተከሸኑ ቃላቶች እንዲሁም አረፍተ  ነገሮች ለትዮጵያ ያላቸውን “ወደር የሌለው ፍቅር” ሲገልፁ ሰምተናል። ዶ/ር አብይም በየክልሉ እየዞሩ ሲሰብኩ የነበረው ይህንኑ ነው። አሁንም በስብከት ደረጃ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ካፋቸው አይጠፋም።

በዚህም ምክንያት ህዝቡ ከዳር እስከዳር በሚባል ሁኔታ ድጋፉን አሳይቷቸውል። በተለይ የመገናኛ ብዙሃኑን የተቆጣጠሩት ልሂቃን ዶ/ር አብይና ሌሎች የኦህዴድ ሰዎች የሚናገሯቸውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚኮረኩሩ ንግግሮች በማስተጋባት የነዚህ የኦህዴድ ሰዎች ዝና እንዲገንና እንዲናኝ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። በጣም በተለየ ሁኔታ ደግሞ የአማራው ልሂቃን በስብከቶቹ ምክንያት ለዶ/ር አብይና ለአቶ ለማ እንደቀጤማ ተጎዝጉዘውላቸዋል፤ ጫማ ለመሳምና በአራት እግራቸው ለመሄድም ተገልግለዋል። ይህንኑ የሚገልፀውን ደስታቸውንም ለአለም ሁሉ አሰራጭተዋል።

አሁን አሁን ግን ሁኔታው እየሄደበት ያለው አቅጣጫ የሚያምር አይነት ስላልሆነ እንዴት ነው ነገሩ የሚል ሰው እየበዛ መጥቷል። ለዚህ ጥያቄ መነሻ የሆነውም የሚሰበከውና በተግባር የሚታየው ነገር አራምባና ቆቦ እየሆነ በመምጣቱ ነው። ስብከቱ (ሰሙ ለማለት ነው) በዚህ ፅሁፍ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው በኢትዮጵያዊነት ስም የተጀቦነ ማማለያ ነው።  ተግባሩ (ወርቁ) ደግሞ ኦሮሟዊነት እየሆነ ነው። በሌላ አነጋገር ዶ/ር አብይ  ከኦሮሞ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መስማት የሚፈልገውን ዲስኩር በተከሽነ አማርኛ እያንዶለዶሉ ለኦሮሞ ህዝብ ግን የሚፈልገው እንዲደረግለት የሚያስችሉ አሰራሮች እንዲዘረጉ እያደረጉ ነው። ለዚህ ደግሞ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ በሚንስትርነት፣ በምክትል ሚንስትርነትና በተለያዩ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ደረጃ እንደ አዲስ እየተሾሙ ያሉት በብዛት የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። እዚህ ላይ መታየት ያለበት እነዚህ የኦህዴድ ሰዎች በቁጥር መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን የሚሾሙበት ቦታም የአገርን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ለመቆጠጠር ቁልፍና ወሳኝ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው እንደ ውጭ ጉዳይ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግና፣ የገቢዎችና የመሳሰሉት ተቋማት መሆናቸው ጭምር እንደሆነ በሌሎች ፅሁፎችም ተገልጿል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን በቁጥጥር ስር ለማድረግ በመታወቂያ ስምና መዋቅሩንም ኦሮሟዊ ለማድረግ እንዲቻል የኦህዴድ ሰዎችን ለመሰግሰግ እየተሰራ ያለን ሴራ በተለያየ መንገድ እየሰማን ነው። የመታወቂያውን ጉዳይ በተመለከተማ ስራዋን ባግባቡ ለመወጣት በማሰብ ለሚድያ ተቋም መረጃ የሰጠች የመረጃና የወሳኝ ኩነቶች  ሰራተኛ ከስራ እስከመታገድ ሁሉ ደርሳለች።  የፀጥታ ተቋሙንም ቢሆን በነዚሁ የኦህዴድ ሰዎች ቁጥጥር ስር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንድም በዋና አዛዥነት ለምሳሌ አየር ሃይል ካልሆነም በምክትልነት እንደ ኢታማዦር ሹም እና በደህንነት ተቋሙ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማየት መረዳት ይቻላል። እንዲያውም አሁን አሁንስ ከዋናው ኤታማዦር ሹም ይልቅ የኦህዴድ ሰው የሆኑት ምክትሉ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን የባለቤትነት ጥያቄም ሆነ ኦሮምኛን የፌዴራል መንግስት ቋንቋ አድርጎ በሌላው ህዝብ ላይ በህግ ለመጫን የተጠነሰሰን እቅድ ለማስፈፀም ጊዜ እየጠበቁ እንደሆነ እነጃዋር ሳት ብሏቸው እያወጡ ካለው ምስጢር እየተረዳን መጥተናል። ይህን ለማድገ ደግሞ የእቅዱ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚያደርጉትን ትወና እየተመለከትን ነው። ለምሳሌ  በቅርቡ በተደረገ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ አማርኛ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ ይሁን ብለው ጥያቄ አቅርበዋል ተብሏል። ይህን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ወደፊት ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ይሁን የሚል መነሻ ሃሳብ ሲያቀርቡ ጥያቄ ቢነሳባቸው አማርኛ የአፍሪካ ህብረት ቋንቋ ይሁን ብለን እየተሟገትን እንዴት ኦሮምኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዳይሆን ጥያቄ ይቀርባል የሚል ክርክር በማቅረብ ለማሳመን እንዲመቻቸው ነው በሚል የሚከራከሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከዚህ ሌላም እንዲህ አይነት ኢትዮጵያዊ የሚመስል ተግባር በመፈፀም የአንድነት ሃይል ነኝ የሚለውን በተለይም ሚዲያ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ አፍ ሸብበው ውስጥ ለውስጥ የሸረቡትን ሴራ ተግባራዊ ለማድርገ እንዲረዳቸው ነው የሚሉ ሰዎች አልጠፉም። ይህን የነዶ/ር አብይን ሰምና ወርቅ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ የተረዳው  ርዕዮት የተባለ የፖለቲካ አቀንቃኝና ጋዜጠኛ የሚከተለውን መከራከሪያ አቅርቧል።

“በዚህ ሰሞኑን በተለቀቀው Video ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስአበባን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ያራመዱት አቋም ከፓርቲያቸው የማይለይና አዲስአበባን ለአንድ ክልል ባለቤትነት አሳልፎ የሚሰጠውን ከፋፋይ ረቂቅ አዋጅ የሚደግፍ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ …አሁን [ደግሞ]ኢትዮጵያንና ታላቅነቷን ባገኙት መድረክ ሁሉ መስበክ ጀምረዋል..”

የብአዴን (አዴፓ) ሰዎች ደግሞ ልክ እንደ ልሂቃኑ ሁሉ እየተሸወዱ ያሉት በእነ ዶ/ር አብይና አቶ ለማ በሚቀነቀነው ስብከት (ሰም) እንጅ  እየተደረገ ባለው  ድርጊት (ወርቅ) አይደለም። የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ የአዴፓ ሰዎች ይህን በሴራ የተጠመጠመ ተግባር (ወርቅ) ቆፍሮ ለማግኘት እንኳን ብቃቱ ፍላጎቱም የሌላቸው መሆኑ ነው። የብቃት ነገር ሲነሳ አዴፓዎች በጣም ያሳዝኑኛል። ሌላው ይቅርና ተማርን የሚሉት እንኳ ሲማሩ በነበረበት ጊዜ ፈተና ለማለፍ ካጠኑትና ካነበቡት ውጭ ስትራቴጂክ የሆነ ሃሳብ ለማመንጨትና የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ህዝብ የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አለ ለማለት ይከብዳል። ብቃት ያላቸውን የአማራ ምሁራንም ስልጣን ይጋፉናል ብለው ስለሚያስቡ አያስቀርቧቸውም። በዚህም ምክንያት ይመስላል ሙህራን አንድ መድረክ ላይ ምን እንርዳችሁ ብለው ሲጠይቁ የአዴፓ መሪዎች በበኩላቸው ድርጅቱ ውስጥ ገብታችሁ ትግሉን አጠናክሩት በማለት ፋንታ እዛው በያላችሁበት በየሙያችሁ ካገለገላችሁ በቂ ነው የሚል እንደምታ ያለው መልስ የሰጡት። ከዚህ አንፃር አሁን ባላንበት ከፍተኛ የውድድር ዘመን የአዴፓ  ሰዎች እንዴት አድርገው የአማራን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቁ እንደሚችሉ ፈጥሪ ነው የሚያቀው።

እነዚህ የአዴፓ ሰዎች ብቃታቸውን አሳድገውና ልቀው በመገኘት የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ለመፍታት ከመጣር ይልቅ  የለውጥ “ሃይል በሚል” ባጋጣሚ በተገኘ ስም ተጀቡነው የኦህዴድ ሰዎች አጋፋሪ ሆነው ቀጥለዋል። ድሮም የብአዴን ሰዎች የህወሃት ሰዎች ቅጥ ሲያጡ ተው ብለው ወደ መስመር እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ አጋፋሪዎች ነበሩ፤ ያሁኖቹ የአዴፓ ሰዎችም የተወረወርችላቸውን ፍርፋሪ ስልጣንና ጥቅም የሙጥኝ ብለው እግራቸውን ዘርግተው ተጎልተዋል። እየሆነ ያለው አዝማሚያ ያሳሰባቸው ሰዎች ሁኔታው እንዲስተካከል ጥያቄ ሲጠይቁ እንኳ እነ አቶ ገዱና ዶ/ር አምባቸው የእኛ ትልቁ ጉዳይ ስልጣን አይደለም የሚል የፌዝ መልስ ሲሰጡ እየተደመጡ ነው። የሚገረመው ነገር ግን በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ  ጊዜ የስልጣን ጥያቄ ከሚያነሱት ሰዎች ውስጥ ቁጥር አንድ የነበሩት እነ ዶ/ር አምባቸው የነበሩ መሆናቸው ነው። ምነው ታዲያ አሁን ትልቁ አጀንዳችን የስልጣን ጥያቄ አይደለም እያሉ ሰውን ለማሳመን ሲዳክሩ የሚሰሙት፤ ምናልባት የየነሱ “ቆራጥ ተጋድሎ” አሁን የተወረወረላቸውን የአማካሪ ሚንስትርነትና የመሳሰሉ የስልጣን አይነቶችን ለማግኘት ካልነበረ በስተቀር።

የአዴፓ አመራሮች ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የብቃት፣ የራዕይ፣ በጎጥ ላይ የተመሰረተ መፈራቀቅ እንዲሁም የተልዕኮ ግልፅነት መጓደል ጠፍሮ የያዛቸው ስለሚመስል አይደለም ከኦዴፓና ከሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋ ተስማምተውና አንድነት ፈጥረው ረዘም ላለ ጊዜ ሊሰሩ ራሳቸውም እንደ እምቧይ ካብ ሊበታተኑ እንደማይችሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ለዚህም ነው የአማራ ህዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ ምን አልባት በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ካልሆነ በስተቀር በአዴፓ ሊወሰን አይችልም የሚል ድምፅ በስፋት እየተሰማ ያለው።

ዲያስፖራዎች፣ ተቃዋሚ ተብየ የፖለቲካ ስብስቦች፣ የሚዲያ ሰዎችና ሌሎችም በበኩላቸው መሰረታዊ የሆነ የአወቃቀር፣ የአደረጃጀት፣ የተቋማት፣ የአመራርና የአሰራር ለውጥ በሌለበት፤ እዚህም እዛም በሚደረጉ ለውጥ በሚመስሉ እርምጃዎች በመሸወድ ለውጡ እንዳይደናቀፍ በሚል አሁን በሃገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል የበኩላቸውን ጥረት አለማድረግ ከውርደትም ትልቅ ውርደት፣ ከሞትም የከፋ ሞት፣ ከሃጥያትም ነውረኛ ሃጥያት እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል። እንዲያውም በዚህ ረገድ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባው ትልቅ ነገር ችግርን አንስቶ እንዲስተካከል ትግል ማድረግና በመረጃ የተደገፈ የተለየ ሃሳብ ይዞ መከራከር አለ ለሚባለው ልቅምቃሚ ለውጥ ድጋፍ እንጅ አደናቃፊ ሊሆን የማይችል መሆኑ ነው። ይልቁንም አደናቃፊ የሚሆነው አገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ተግባራትን እያዩና እየሰሙ ገና ለገና ለለውጡ አይመቹም ብሎ አንገትን ደፍቶ አፍን ሸብቦ ሲያሽቃብጡ መዋልና ማደር ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ እነ ዶ/ር አብይ በሰምና ወርቅ ፈሊጥ አይነት ፖለቲካ ጨዋታ የተዋጣላቸው ይመስላል። ሌት ተቀን የሚያቀነቅኑት ስብከት ሰሙ ኢትዮጵያዊነት ሲሆን የተግባሮቻቸው ወርቅ ደግሞ ኦሮሟዊ እየሆነ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች በዝተዋል። ይህ አይነት ፖለቲካ ደግሞ የእርድና ፖለቲካ ከሞሆን አይዘልም። እኔ በተወለድኩበት አከባቢ አራዳ ሲባል ጭልፊት፣ አፈ ቂቤ፣ ጮሌ፣ አፈ ጮማ፣ ቂቤ ጠባሽ  ወይም አማላይ ማለት ነው። በዚህ መንገድ የሚጠራ ሰው ብዙውን ጊዜ ከአፉ ክፉ አይወጣም። እንዲያውም ነብሴ፣ ሆዴ፣ እናቴ፣ ምን ልሁንልህ፣ ምን ይጠበስ፣ እኔ ልሙትልህ/አፈር ልሁንልህ፣ ካንተ በፊት እኔን ያድርገኝ  ይልሃል። ይህ ማለት ደግሞ ሰም መሆኑ ነው።  የዚህ አይነት ሰው  የተደበቀ አላማ ማለትም ወርቁ ግን ካንተ ላይ ሊያገኝ የሚፈልገውን የሚገባም ይሁን የማይገባ  ጥቅም በተለሳለሰ መንገድ ማግኘት ነው። የነዶ/ር አብይ አላማም ይህ እንዳይሆን እጅግ በጣም ጥንቃቄና ብስለት በተሞላበት መንገድ መከታተል ይጠይቃል። ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ለህወሃት ካለ ጥላቻ ብቻ ተነስቶ  ለውጡ እንዳይደናቀፍ በሚል ሰበብ  አንገት ደፍቶ አፍ ሸብቦ አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ትርፉ ተያይዞ ገደል መግባት እንጅ ሌላ ጥቅም አይኖረዉም። ይልቁንም እዚህም እዛም የሚታየው ልቅምቃሚ ለውጥ ሊጎለብት የሚችለው በጠንካራ መርህ ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ ሲቻል ብቻ እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። በሌላ አነጋገር ከመሸ በኋላ ችግሩን ለመፍታት ባትሪ ፍለጋ ከመሯሯጥና ከመደናበር ይልቅ  አሁኑኑ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በሚዛናዊነት ያገባናል የሚሉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር፤  በአጠቃላይም የኢትዮጵያ አንድነት፣ሰላምና ዴሞክራሲያዊ እድገት እንዲጎለብት መስራት ይጠይቃል።

5 COMMENTS

 1. የፊንፊኔ አዲስ አባባ ታሪክና የኦሮሞ ማንነት በጽንፈኞች አይታወክም አማራዊነት ኢትዮጲዊነት ወይም ክርስትና ተብሎ በተነገረበት ሃገር በብሄረ (በዘር) ደረጃ ብዙሃን የሆነውን የኦሮሞን ቋንቋና ማንነት ማረመድ ለአንዳንዶቹ በተለየ ለጽንፈኞቹ የሚዋጥ አልሆነም:: ዶር አብይ ከማንም መሪ በሀገራችን ታሪክ ባልታየ ሁኔታ ጥበብ ፍቅር ትህትና መሞላቱን ጽንፈኞቹ ቢክዱት ያስታረቃቸው የተዋህዶና የሙስሊም አንጃ መሪዎች ታሪክ ከእስር የፈታቸው የሽምቅ ተዋጊዎች በተለይ አንዳርጋቸው ጽጌ አማራው አልካደውም:: ኦሮሞዎች በቁጥር አነስተኛ በሆኑበት ኬንያ የነበራቸው መብት ብዙሃን ከሆኑባት ኢትዮጲያ የላቀ ነበር:: ዶ/ር አብይ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በክፈተኛ ስልጣን የመደባቸው ብዙ ጊዜ የጎበኘውም አማራ አካባቢ ሲሆን ጽንፈኞቹ የራሱ ኦሮሞችም ሆነ ለአማራ ቆመናል የሚሉት ሲያብጠለጥሉት ይገኛሉ:: በአጭሩ ቃል ኦሮምና የፌደራል ቋንቋ መሆን ከስነህዝብና ከታሪክ አንጻር የግድ ነው:: ዶ/ር አብይ አማርኛን የአፍሪካ ህብረት ይፋ ቋንቋ ያስደረገውገው ለኦሮምኛ ማስፋፋት እንዲመቸው ነው የሚለው ኢሎጂክ ይስቃል:: ስለፊንፊኔ አዲስ ኣአበባ ብላቴን ጌታ ህሩይ የ1929 መጽሃፍ ላይ የንጉሱ ምኒሊክ ኣያት ሳህለስላሴ በገዙበት ዘመን ፊንፊኔን ሲወሩ የተናገሩት ትንቢትና በአብቹና በገላን የኦሮሞ ጎሳዎች መካከል የፈጠሩት ከፋፍለህ ግዛው በግልጽ ተዘግቧል:: ከዚያ ስፍራ ማዶ በየረር የነበረች በረራ ከተማ ኦሮሞ ወደዚያ ስፍራ ሳይፈልስ የነበረች ገናና ከተማን አዲስ አበባ ነች ማለትም ሚዛን የሚደፋ ኣየደለም:: በዚያ 15ኛ ክፍለዘመን ዘመን አማርኛ ቋንቋ ስለመነገሩ ታሪካዊ ማስረጃ የለም አማርኛ ይፋ የሆነው በ19ኛ ክፍለዘመን በንጉሱ ቴዎድሮስ መሆኑም ይስተዋል::
  ይህች ታዳጊ የሁሉ የሆነች ከትማ ሌሎቹ Metropolitan ሜትሮፖሊታን የአለም ከተሞች ባላቸው ህግ ትተዳደር:: ነዋሪዋ ከሶስትና አራት ትውልድ በፊት ተዳባልቆ ከህሉም ዘርና ብሄር የተከማቸው የቻርተር መብቷ ይከበር ለፖለቲካ ፍጆታና ለማጋጨት ወያኔ ያወጣቸው ህጎች በብዙሃን ተወካዮች ከወቅቱ ጋር ይስተካከል::
  ለማንኛውም የተጀረመውን በጎ ለውጥና ቅን መሪዎቹን መክሰስ ማዋከብና ያላስፈላጊ የዘር ጥላቻ ከመቀሰቀስ ሰሞኑን ምሁራኑ ከአማራም ዶ/ር ዳኛቸው ከኦሮሞ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ያቀረቡትን በጎ ምክር በመስማት ለውጡን ልንደግፍ በዘር ላይ የተመስረተ ፖለቲክ ጫና ጥላቻ ብናቆም ለራሳችንም ለመጭውም ትውልድም የበጃል::
  ዲጎኔ ሞረቴው ሴሜቲክ ኩሽቲክ ናይሎቲኩ ከደክ ሃራራ ፊትበር USA February 2019

 2. The Ethiopian peoples have been suffering from man-made political syndrome which was created by greedy politicians all the time so far. All these politicians have never cared about collective and individual rights. That is why we are still struggling against all sorts of odd ideologies and thinking.

  There is nobody without national background and heritages in this planet. All human beings have ethnic backgrounds regardless of the composition of their ethnicity. Those who try to nullify their ethnic backgrounds are claiming Amhara ethnicity by default under the mask of Ethiopianism. They speak amharic and claim the cultures from north as their culture. They try to impose their default identity (Amaharaism as Ethiopianism) on the others. But it is not acceptable! 

  The struggle of the Oromo nation is not against the Amahara and the Tigre peoples. It is only against subjugation and exploitation, discrimination and forcibly imposed assimilation.

  We believe the Oromo nation is the pillar of peace, stability, security and prosperity of the Horn of Africa. You should have to accept these facts and work with us so that we can promote together mutual understanding and respect.

  The politics of one language, one culture and a single nation cannot be accepted any more in Ethiopia. Don’t forget that such demands have no room in today’s Ethiopian politics. But now temporally you can make noise here and there. That is all what you can do right now.

 3. በእኔ እምነት ኦሮምኛ ቋንቋ የፌዴራል ሁለተኛ ቋንቋ መሆኑ ችግር የለውም። እንኳን ቁጥሩ በበዛ ህዝብ የሚነገረው ኦሮምኛ ቋንቋ ቀርቶ አቅም ካለ ሌሎችም ቢጨመሩ ህዝብ ለማቀራረብ ይረዳሉ እንጅ የሚጎዱት ነበር የለም። ትልቁ ጥያቄ ያለው ሂደቱ ላይ ነው። አሁን “ዘመኑ የኛ ነው” በሚል አንድን ቋንቋ በህግ ለመጫን የሚሞከር አካል የሚኖር ከሆነ በሌላው ህዝብ ዘንድ ቅሬታ እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም። ይሄ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት እንቅፋት ይሆናል። ከዚህ ይልቅ በተጠና መንገድ መስፈርት አውጥቶ የተወሰኑ ቋንቋዎችን በመለየት የህዝብ ውሳኔ አካሂዶ ህዝቡ የሚፈልገውን ቋንቋ ቢመርጥ አንድም በስርዓቱ ላይ እምነት ለማሳደር ያስችላል፤ ሁለተኛ ደግሞ ሀዝብ ለህዝብ መተማመን ስለሚፈጥር የተመረጠውን ቋንቋ ለመማር ፍላጎት ይጨምራል።

 4. Dear Gelaneh,

  The Oromo people have never imposed its culture and language on others. Even the Oromo individuals like Tsegaye Gebremedin, Bahilu Girma, Tilahun Gesse and others have contributed a lot to the development of the Amahara language, culture and arts.

  There are a lot of cultural groups in Oromia today which came from other regions, but have been enjoying full rights like the Oromo themselves. The Oromo people embrace any group and individual as far as they respect the values and norms of the Oromo people.

  Now it is a right time for the afaan Oromoo to become one of the federal working languages of Ethiopia.  It is long time a go overdue. No more delay is needed any more.

 5. “በሚንስትርነት፣ በምክትል ሚንስትርነትና በተለያዩ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ደረጃ እንደ አዲስ እየተሾሙ ያሉት በብዛት የኦህዴድ ሰዎች ናቸው።”
  1ኛ የኦህዴድ ሰዎችም ቢሆኑ እኮ ብዙዉ ስሙን የለወጠ ትግሬ ወይም አምሃራ ነው!
  2ኛ እንዲያው በድሮ ግዜ 90% አማራ ሁሉን ይቆጣጠር እንደነበረው እንዲሆን ምኞቱ አሁንም አልቀረም??

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.