ኑ አብረን እንፈር! እያፈርንም እንጩህላቸው! (ጌታቸው ሽፈራው)

ጊዜው የድግስና የቅበላ ሆኗል። ለአንድ ወር ያህል የቅበላ ስነስርዓት እየተሰናዳ ነው። አይከፋም። በዛውም የማደራጀት ያህል ነው። በዛውም የሕዝብ ግንኙነት ስራ ነው። ብልጥ ያገኘውን አጋጣሚም ይጠቀማል። አርበኞች ግንቦት 7 የቅበላ ስነስርዓት እያለ አንድ ወር ያህል ዝግጅት ማድረጉ የፖለቲካ ብልጠት ነው። ይጠቀምበታል። ችግሩ አባላቶቹን መርሳቱ ነው! በስሙ የተከሰሱትን መዘንጋቱ ነው!

በዚህ የቅበላ ስነ ስርዓት ውለታ ሰርተዋል የተባሉ ሰዎች ፎቶ ተለጥፏል። ስማቸው ተወስቷል። ነገር ግን በእስር ቤት የሚማቅቁ ወጣቶችን ስም ሲያወሳ የተሰማ የለም። ይፈቱ ብሎ የጠየቀ የለም። እንዲያውም አልፎ አልፎ ስማቸውን ስናነሳ ድርጅት ለማሳጣት የሚመስላቸው ርህራሄ ያልፈጠረባቸው የሚመስሉ የሀሰት ገፆች በኩል ስድብና ውርጅብኝ ይደርስብናል።

ይህ ግን ታጋዮቼ ናቸው የሚለው የአርበኞች ግንቦት 7 ብቻ ችግር አይደለም። አብንን ጨምሮ ብሔርተኛው ለእነዚህ እስረኞች ትኩረት የሚሰጥ ጠፍቷል። በስም ደረጃ የሚገኙት “ሀገራዊ ፓርቲዎችም” እንግዳ ተቀባይ፣ የህትመት ክፍል ሰራተኛ፣ መድረክ አሟሟቂነት ያለፈ ለመከረኞቹ፣ ለታፈኑት፣ ለእስረኞቹ መጮህ አልቻሉም።

የመጀመርያው ኃላፊነት ያለበት አርበኞች ግንቦት 7 አንድ ወር የሚዘልቅ የድግስ ስርዓት ውስጥ የእነዚህን ወጣቶች ስም ረስቷል። ስቃያቸውን ረስቷል። የት እንዳሉም ተስቷል። አርበኞች ግንቦት 7 የረሳቸውን እነዚህን መከረኛ ወጣቶች ብሔርተኛውም ሕዝብ ዘንግቷቸዋል። ሕዝብ ለአቀባበል ሲሮጥ በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ወገኖቹን ተስቷል።

በርካቶች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የሚያንስባቸው አሉ። ነገር ግን በእነዚህ ፕሮግራሞች ተጠምደን ለዚህ ወቅት ካደረሱን መካከል የሆኑትን እስረኞች እረስተናል! ማፈር አለብን!

አሁንም ዘገየ እንጅ አልመሸም! የሆነ ሰው ሲመጣ ግር ብለን እንደምንቀበለው ሁሉ ለእነዚህ ወጣቶችም ድምፅ ማሰማት አለብን። ገንዘብ እየተከፈለ የእንትናን ፎቶ ይዘህ ውጣ፣ ቲሸርት አሳትም እንደሚባል እናውቃለን። የድርጅት ስም ሲገንን እንደሚውል የታወቀ ነው። የእነዚህ መከረኞችን ስም ግን ረስተነዋል።

አሁንም እያፈርን ማስታወስ አለብን! ፎቷቸው ጠፍቶ አይደለም፣ ስማቸው ስለማይታወቅ አይደለም። ወረተኛ ሆነን ነው! ጥቅምና ፖለቲካ አስቀድመን ነው እንጅ ስማቸውም ፎቷቸውም አለ። አባላቶቻችን ናቸው የምንላቸው ናቸው።

አሁንም እያፈርን፣ ለድርጅት እንጅ ቆመንበታል ለምንለው የግለሰብ ፖለቲካ፣ ሰውን የማክበር ፖለቲካ ታማኝ እንዳልሆንን፣ አባላቶችን መርሳታችን አስታውሰን ልንጮህላቸው ይገበል። ለአባላት፣ በስማችን ለተከሰሱ፣ በእስር ላይ ለሚገኙት ካልቆምን ለሀገር እንቆማለን ማለታችን በተግባር የማይለካ መሆኑ አሳፍሮን ከአሁኑ ለእነዚህ መከረኞች እየጮህን ተግባር መጀመር ይገባናል።

በአቀባበል ስነ ስርዓት ብቻ ሳይሆን ሰልፍ ያስፈልጋል! እነዚህ እስረኞች እንዲፈቱ በሰልፍ መጠየቅ ያስፈጋል። ብዙ ጊዜ አቀባባል ለማድረግ እየተንጋጋን ለእነዚህ የመከራ እስረኞች ሰልፍ ወጥተን እንዲፈቱ መጠየቅ ምን ይከብዳል? ለወራት የአቀባባል ስነ ስርዓት በየቀኑ መግለጫ ስንሰጥ እየዋልን ለእነዚህ መከረኞች መግለጫ ማውጣት ምኑ ይከብዳል? በየቀኑ ተሰብስበን ስለ አቀባበል ስናወራ እየዋልን ለአንድ ሰዓት የእነዚህን ወገኖች ድምፅ ማሰማት ምኑ ከብዶ ነው?

በዛ የመከራ ጊዜ አድፍጦ የቆየው ዛሬ ሜዳ አይበቃኝም ሲል፣ በዛ የጨለማ ወቅት የታገሉት፣ በአፈና ወቅት የሚገኙት መረሳታቸውን እያሰብን እንፈር! በዛ የአገዛዝ ወቅት የገዥዎቹ መሳርያ የነበረው ጋር፣ ከራሳቸው ከገዥዎቹ ጋር ስንጨባበጥ፣ ፋሲካና ደስታውን አብረን ስናደርግ ለሕዝብ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን መርሳታችን እያሰብን እንፈር፣ አፍረን ግን ልንጮህላቸው ይገባል! በዛ ክፉ ዘመን የፖለቲካ እንቅስቃሴን እንደ ነውር፣ እንደቅብጠት ከማየት አልፎ ለገዥዎች አሾክሿኪ ከነበረው ጋር በየ መድረኩ፣ በየ አዳራሹ፣ በአውርፕላን ጣቢያው ስንደልቅ እነዚህ አብሪ ኮከቦች መርሳታችን አስበን ኩምሽሽ ልንል ይገባል! እያፈርንም ልንጮህላቸው ይገባል!

ካልሆነ ግን ከአላማችን፣ አላማችን ነው ስንለው ከነበረው ጋር ተለያይተናል! ለአላማው፣ ለሕዝባቸው ዋጋ ከሚከፍሉት ጋር ተለያይተናል! እንዲህ ከሆነ ማፈር አይገባንም። ማፈር አንችልም። ማፈሪያዎች ሆነናል ማለት ነው!

አላማ ካለን፣ የታገሉበት፣ ግድ የሚለን ከሆነ ግን ኑ አብረን እንፈር! እያፈርንም እንጩህላቸው! ኩምሽብ ብለንም እንጠይቅላቸው!

በአርበኞች ግንቦት 7 ተከስሰው አሁንም በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል:_

ቂሊንጦ:_

1. ሻንቆ ብርሃኑ
2. ጌታነህ አቡሃይ
3. እንግዳው አዲሱ
4. ክንዱ ዱቤ
5. አስቻለው ደሴ
6. ደሳለኝ ማንደፍሮ
7. ፊሊሞን ሀይሉ

በቃሊቲ:_

1. ዶክተር አስናቀ አባይነህ
2. ጸጋየ ዘለቀ(አማኑኤል)
3. ተስፋየ አያሌው
4. ሰይፉ አለሙ

5) ኮ/ል ጌትየ አለሜ

በጎንደር አንገረብ:_
1. አያናው ደረሰልኝ
2. ተስፋዬ አማረ
3. ጥጋቡ ገዳሙ
4. ዘውዱ ደመቀ
5. ጌትነት በየነ
6. ነጋ ባየ ናቸው።

በእስር ላይ የሚገኘው ፀጋዬ ዘለቀ (አማኑኤል)

ዳንኤል ተስፋዬ እንደፃፈው!

ፀጋዬ ዘለቀ( አማኑኤል) ተዎልዶ ያደገው ፍኖተ- ሰላም ነው። ከሀሮማያ ዩንቨርስቲም የመጀመሬያ ድግሬውን በኬሚስትሬ ትምህርት ክፍል( ዲፓርትመንት) ተመርቋል። በጋንቤላ ክልል በሚገኝም አቦል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በርህሰ -መምህረነት ሲያገለግል ቦንጋ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ደግሞ በመምህርነት አገልግሏል።

መምህር ፀጋዬ በ2006 ዓ.ም ወደ ኤርትራ በማቅናት አርበኞች ግንቦት 7ን በመቀላቀል በአስመራ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ የህትመት ክፍል ኃላፌ በመሆን እንዲሁም በኤርትራ አንቶሬ የፖለቲካ ግንባር ኃላፌ በመሆን
ሲያገለግል ቆይቷል።

በ2008 ዓ.ም ከ12 የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደሮች ጋር ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ሳሉ በፀጥታ አይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ከጓደኞቹ ጋ በመከላከያ ሰራዊት ተይዞ ታስሯል። ማህከላዊ ተወስዶ ከፍተኛ እንግልት ደርሶበት በፀረ- ሽብረተኝነት አዋጁ 652/2001 ዓ.ም አንቀፅ 3/1ን በመተላለፍ ተከሶ 14 አመት የተፈረደበት ሲሆን አብረውት ተከሰው የተፈረደባቸው 6 ተከሳሾች ማለትም ጋሻው ሙልዬ፣ ዮኃንስ መንግስቴ ፣ጉርባ ወርቁ ፣ ማናስብ ብርሃኑ ፣ አስማረ ግለጥ (ቻይና) በምህረት ሲፈቱ እሱ ግን እስካሁን ከ9 ተከሳሾች ተለይቶ ሳይፈታ በቃሊቲ እስር ቤት ይገኛል።

በአሁኑ ሰአት መምህር ፀጋዬ ዘለቀን ጨምሮ በቃሊቲ 9 ተከሳሾች የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል

።—————

ፍትህ! ፍትህ!
በአርበኞች ግንቦት 7 ተከስሰው ጎንደር ማረሚያ ቤት ለሚገኙት:_

1ኛ)ዘውዱ ደመቀ
2ኛ) ጌትነት በየነ
3ኛ)ነጋ ባየ
4ኛ) አያናው ድረስልኝ
5ኛ)ተስፋ አስማረ
6ኛ)ጥጋቡ ገዳሙ

 

———————————————-

የአቪየሽን ባለስልጣን ከድጡ ወደ ማጡ

(ብሩህ አለምነህ)

የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች (ከዚህ በኋላ “ተቆጣጣሪዎች”) ከደምወዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ከነሐሴ 21፣ 2010 ዓም ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ላይ ይገኛሉ። የሀገሪቱን የአየር ክልል እንዲያስተዳድር ሙሉ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን (ከዚህ በኋላ “ባለ ስልጣኑ”) ግን ችግሩን ለመፍታት የሄደባቸው አካሄዶች በችግር ላይ ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር፣ መፍትሔ ብሎ የወሰደው እርምጃ ራሱ ህገ ወጥ ነው።
“”””””

ህገ ወጡ መፍትሔ – 1
“”””””””””””””””””””””””””””””
ተቆጣጣሪዎቹ ከአድማው በፊት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ስለታሰበው አድማ አስታውቀው ነበር። ባለስልጣን መ/ቤቱ ግን ከተቆጣጣሪዎች ጋር ከመደራደር ይልቅ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ (ከዚህ በኋላ ET) ጋር በመነጋገር ሌሎች ተቆጣጣሪዎችን ከዚምባቡዌ በማስመጣት ችግሩን እንዲፈታ ለማድረግ ሞክሯል።
“”””””
የመጀመሪያው ህገ ወጥነት የሚጀምረውም ከዚህ ነው። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ያለው የሲቪል አየር ትራንስፖርት ኢንደስትሪ አራት ተዋናዮችን ያቀፈ ነው – ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንን፣ የኤርፖርቶች ድርጅትን፣ አየር መንገዶችንና የግራውንድ አገልግሎት ሰጪዎችን። በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን 3ቱን ዘርፎች ET ነው የጠቀለላቸው – የኤርፖርትን፣ የግራውንድንና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን። ET ባለስልጣን መ/ቤቱን እንዳይጠቀልል የከለከለው ዓለማቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት (ICAO) ህግ እንጂ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለ ስልጣንን ቢጠቀልል ደስ ይለዋል። አሁንም ግን ET በእጅ አዙር ይሄንን እያደረገ ነው – ተቆጣጣሪዎችን ከአፍሪካ ሀገር እያመጣለት ነው። ይሄ ነገር ህገ ወጥ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ሀገር የአየር ክልል ደህንነት አንፃርም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው።

“”””””””
በሁሉም ሀገር ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ማህበሮች አንድ የጋራ ዓለማቀፍ ፌዴሬሽን አላቸው – IFATCA የሚባል። በIFATCA ህግ መሰረት በየሀገሩ ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ማህበሮች እርስበርስ መደጋገፍ አለባቸው፣ በተለይም የጎረቤት ሀገር ማህበሮች። በዚህም መሰረት ከIFATCA ብቻ ሳይሆን ከሱዳንና ከኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበሮች በኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ላይ እየተፈጠረ ያለውን ችግር አሳሳቢነት የሚገልፅ መግለጫዎችን አውጥተዋል። ET ከዚምባቡዌ ያስመጣቸው ተቆጣጣሪዎችም ጉዳዩ “የስራ እድል ሳይሆን የአድማ ጉዳይ መሆኑን ሲያውቁ” ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። በዚህም ባለ ስልጣኑ ወደ ሁለተኛው መፍትሄ ያልሆነ መፍትሔ ሄዷል።

መፍትሄ ያልሆነው መፍትሔ – 2
“”””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ፅፈህ የምትወዝፈው ወይም ደግሞ በቢሮህ አሳድረህና ሌሎችን አማክረህ ውሳኔ የምትሰጥበት የወረቀት ሥራ አይደለም። ሥራው በባህሪው የቀጥታ ስርጭት (Live) ሥራ ነው – የሬዲዮ ግንኙነት በተፈጠረበት ቅፅበት አስቸኳይ ውሳኔ የሚሰጥበት። በዚህ ባህሪው የተነሳም ሥራው ወጣትነትንና ንቁነትን ይፈልጋል።

“”””””

ባለ ስልጣኑ ከአድማው ዕለት ጀምሮ ያደረገው ነገር ግን ሥራውን ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥራ ጡረታ በወጡ ሰራተኞች ማሰራት ነበር – ያውም በ24 ሰዓት ውስጥ እስከ 18 ሰዓት ድረስ እንዲሰሩ በማድረግ። እንደዚህ ዓይነት መፍትሄ ከ4 እና ከ5 ቀናት በላይ እንደማያስኬድ ይታወቃል። የባለ ስልጣኑ ሐሳብ ግን “ተቆጣጣሪዎቹ ህብረትና ፅናት ስለሌላቸው ተፈረካክሰውና ተንጠባጥበው ወደ ስራቸው መመለሳቸው አይቀርም፣ ያንጊዜ “የይቅርታና የፀፀት” ፎርም አስመልሼ አስገባቸዋለሁ፣ እንቢ የሚሉትን ቀንደኞችን ደግሞ አሰናብታቸዋለሁ” የሚል ነበር።
“””””
ተቆጣጣሪዎቹ ግን ለጥያቄያችን መልስ ካልተሰጠን ወደ ስራ አንመለስም በሚለው ሐሳባቸው እንደፀኑ ሆኑ። በዚህ ጊዜ ነበር ባለ ስልጣኑ ወደ 3ኛው ህገ ወጥ እርምጃ የገበው – ወደ እስራት።

ህገ ወጡ መፍትሔ – 3
“”””””””””””””””””””””””””””””
መፍትሔዎቹ ሁሉ ውጤት አላመጣ ሲሉ ባለ ስልጣኑ ከፖሊስ ጋር በመተባበር የአድማው አስተባባሪ ናቸው የሚላቸውን 10 ተቆጣጣሪዎች (2ቱ ሴቶች ናቸው) ትናንት ነሐሴ 28፣ 2010 ዓም ማታ ላይ እንዲታሰሩ አድርጓል (ፎቶው)። የቀረበባቸውም ክስ “የውጭ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ በመከልከል” የሚል ነው (በበፊቱ ዘመን ቢሆን “በአሸባሪነት” ነበር የሚከሰሱት)

“””””””
ከባለ ስልጣኑ ብልሃት የጎደለው ውሳኔ ጀርባ የኮ/ል ወሰንየለህ ሁነኛው (የባለ ስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር) እልህ አለበት። ኮ/ል ወሰንየለህ ቀድሞ የአየር ኃይል ባልደረባ ስለነበሩ ባለ ስልጣን መ/ቤቱን የሚመሩት በወታደራዊ ትዕዛዝ ባህሪ ነው። ከደሞዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በየትኛውም ሀገርና መ/ቤት የስራ ማቆም አድማ ይደረጋል – የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ጨምሮ። ሆኖም ግን ችግሩ የሚፈታው በመነጋገርና በመደራደር እንጂ ሰራተኞችን በማሰርና በማባረር አይደለም። ከዚህ አንፃር ዋና ዳይሬክተሩ የወሰዱት እርምጃ ለኢንዱስትሪው መፍትሄን ከማምጣት ይልቅ እሳቸው ራሳቸውን የሚያስጠይቃቸው ነው የሚሆነው።

“”””””
ለማንኛውም ይሄ ክስተት ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ የአየር ክልል (ትራፊክ) ደህንነት ውስጥ ያላትን ደረጃ ሊያወርደው ይችላል።

2 COMMENTS

  1. ከአባላቱ ግማሹ እስር ቤት ሁነው ግንባሩ የድግሥ ጋጋታ ምን ሊበጀው? በመግለጫ ፍቅር እ ብ ድ ያለው አብን ምነው ይሄ አልታየው? እግዜር ይስጥህ ወንድማችን የመግለጫ አርበኛው አብን በዚህ ጉዳይ መግለጫ መስጠቱ አይቀሬ ነውና እንጠብቃለን!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.