እራሳችን ከእራሳችን ጋር እውነቱን እንዲነጋገር ብናስችለው ምን አለበት? (ጠገናው ጎሹ)

February 17, 2019

አዎንታዊና አበረታች የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ ኩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ይኸውና አሁንም ዓመት ሊሞላው ከሁለት ወራት ያነሰ በቀረው የለውጥ ሂደታችን ካጋጠሙን እጅግ አስከፊና መሪር ፈታኝ ሁኔታዎች ትርጉም ባለው አኳኋንና ደረጃ የተማርን አንመስልም ።

በየክልሉና በየመንደሩ  የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ያሉ   እንደ ግለሰብ  ዜጋም ሆነ እንደ አንድ አገር ህዝብነት  አዋራጅ የሆኑ ድርጊቶችን አስመልክቶ የሚሰጡ ምክንያቶችና መግለጫዎች ደግሞ ከድርጊቶች ባላነሰ ህሊናን ያሳምማሉ ።

ለቀናት ወይም ለወራት ሳይሆን ለዓመታት የግጭትና የምስቅልቅል ብሎም የእርስ በርስ ውድመት  ሲያስተናግዱ የኖሩ አካባቢዎች ልዩ ትኩረትና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው  አውቆ ተገቢውን ማድረግ እንደሚገባ ለማወቅ የተለየ እውቀትና ችሎታ አይጠይቅም ። የምር ፣ የቅንነትና የተቆርቋሪነት ህሊና ባለቤት መሆን በቂ ነው ።

ችግሩ ያለው ለጉዳዮቻችን በቅደም ተከተል ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠትና በሚጠይቁት የጊዜ ማእቀፍ ፣ የመጠንና የብቃት ደረጃ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ካለመወጣት ውድቀት ነው ።አስከፊ ድርጊቶች ከተፈፀሙም በኋላ ለጥፉቱ እራስንም ተጠያቂ በሚያደርግ አኳኋን ፈጥኖ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በደፈናው ለውጥ ቀልባሾች የምንላቸውን ጨምሮ ለውድቀታችን መሸፋፈኛ ወይም ሰብብ  ይሆናሉ የምንላቸውን ሁሉ በየመግለጫውና በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እየደረደርን እራሳችን ማታለላችን ሳያንስ ህዝብንም ግራ ከማጋባት  ክፉ አባዜ መቼና እንዴት አራሳችን ነፃ እንደምናወጣ ለመረዳት ይቸግራል ።

በተጠየቀው መሠረት የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያና የፖሊስ ሃይል ወደ ማእከላዊና ምእራባዊ ጎንደር እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ በሁለት ባለሥልጣናት (ወታደራዊ እና የፖለሊስ ሃይል) የተሰጠውን መግለጫ አነበብኩት ። በመሠረቱ የእርምጃው አስፈላጊነትና ተገቢነት ከቶ  አጠያያቂ አይሆንም ።

እንዲህ አይነቱን እጅግ የዘገየ (የተልፈሰፈሰ) መንግሥታዊ ሃላፊነትንና ተግባርን መተቸት ግን ተገቢና ትክክል ነው ። የድጋፍ ጠያቂ (የክልል መስተዳድር) እና ተጠያቂ ( የፌደራል መንግሥት) ተመሳሳይ የችግሩን ገፅ እያነበቡና  እየተናበቡ ያለመሆናቸው ድንቁርና ወይም አወቆ የማደናቆር ክፉ ልማድ ህዝብን (አገርን) አላስፈላጊ መሪር ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ ከዚህ ይወጡ ዘንድ በቀጥታና በግልፅ መነጋገር ይበጃል ። ከድክመት (ከልፍስፍስነት) ወይም የመሪዎችን ደካማ የፖለቲካ ሰብእና ለመሸፈን ሲባል ከሚመነጭ ስሜት የለሽ ምክንያት የሚመጣ ቀውስንና ውድመትን መታገስ ቢያንስ የሞራል ውድቀት ነው ፥ ሲበዛ ደግሞ ወደ የማይወጡት ቁልቁለት ተያይዞ መንኮታኮት ነው ።  በተጠቀሰው አካባቢ የአስከፊ ግጭቶችና ወድመቶች ምክንያት የሚሆኑ ሁኔታዎች ለረጅም ጊዜ የመኖራቸው ብቻ ሳይሆን  ተደጋግሞ የመከሰታቸው እውነታም ከበቂ በላይ ግልፅና ግልፅ ነው ። እናም  ሊከሰት የሚችልን ቀውስ ሲሆን አስቀድሞ የመከላከል ቢያንስ ደግሞ የሚያስከትለውን ውድመት የመቀነስ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ሆኖ ሳለ የከፋ ቀውስና ውድመት ከደረሰ በኋላ ዘግይቶ “ደረስኩላችሁ!” ከማለት ክፉ አባዜ መውጣት ይኖርብናል ።

ማነኛውም ዜጋ በቀላሉ ከሚረዳቸውና እንዲተገበሩ ከሚጠብቃቸው በጣም መሠረታዊ ከሆኑ የመንግሥት ተግባራትና ግዴታዎች መካከል  አንዱ  የህዝብን ፀጥታና ደህንነት ከየትኛውም እኩይ ሃይል ወይም አካል መከላከልና መጠበቅ ነው ። በእኛ አገር ግን ይህ እውን ሊሆን ስለመቻሉ እንኳን በእርግጠኝነት ለማወቅ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመገመትም የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለንም ።

 

ለምን?

  • በአንድ ወይም በሌላ የራሳቸው ምክንያት ለውጥ የሚባለውን ቃሉን እንኳ መስማት በማይፈልጉ የህወሃት የፖለቲካ ዘዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢህአዴግ ካድሬ የመንግሥት ተብየ መዋቅሩን በተቆጣጠረበት ፖለቲካዊ እውነታ ውስጥ ስለ እውነተኛ የአገር ሰላምና መረጋጋት መደስኮር የትም አያራምድም ።

 

  • እንደ ክልል መስተዳድር ያለንበትን እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በንቃትና ብብቃት አስቀድሞ በመረዳት እና ለእሱው የሚመጥን አቅም እንደሌለ በመገንዘብ ለፌደራል መንግሥት ( ምንም እንኳ እሱም ሽባ ቢሆን) በማሳወቅና ድጋፍ በመጠየቅ ልክ የሌለውን ሰቆቃና መከራ ለማስቀረት ጥረት ማድረግ የአንድ ሃላፊነት የሚሰማው የመንግሥት አካል ተግባር መሆን ነበረበት ።ከዚህ  ይልቅ የፖለቲከኞችን (የለውጥ ሃዋርያ የምንላቸውን ጨምሮ) ገፅታ ውብ ለማስመሰል የተሄደበትና እየተሄደበት ያለውን መንገድ ከቅንነትና ከምር ልብ የሚል ዜጋ በተልፈሰፈሰ የፖለቲካ ቁመናነትና አካሄድ  እንጅ በሌላ ለመተርጎም (ለመረዳት) ይቸግረዋል ።

 

  • ጨርሶ መረዳት የሚያስቸግረው የፖለቲካ ደደብነት (political stupidity) ደግሞ ከተደጋጋሚና ተመሳሳይ የምስቅልቅልና የጥፋት ድርጊቶች ተምሮ እራስን በተሻለ ደረጃ ላይ ለማግኘት አለመቻል ነው ። ይኸው እኮ ከዚህ አይነቱ እጅግ ክፉ አባዜ እንኳን ልንወጣ ትርጉም ባለው አኳኋን እፍይ ሳንል ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላን ነው። ኧረ ልብ የሚል ልብ ይሰጠን! ለነገሩ እርሱስ ሰጥቶን ነበር እኛው ራሳችን ራሳችንን ልበ ቢስ እያደረግነው ተቸገርን እንጅ ።

 

  • ሌላው ስሜት የማይሰጠውና የአሁኑ እኛነታችን መገለጫ የሆነው ጉዳይ  እንደ መንግሥት ግጭትንና ውድመትን ቀድሞ የመከላከሉ ውድቀት አልበቃ ብሎ ከችግሩ (ከውድመቱ) በኋላም ሰለባ የሆኑትን ዜጎች ከጊዜም ሆነ ከብቃት አንፃር ፈጥኖ ያለመታደጉ ውደቀት ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የወግንና የመንግሥት ያለህ !”  በሚሉበት ሁኔታ ውስጥ ፖለቲከኞቻችን (መሪዎቻችን) በአገኙት አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ሙገሳውን የሚያዥጎደጉድ እንጅ  ተጠየቅ !” ብሎ የሚወጥር ታዳሚ የሌለባቸው ልዩ ልዩ መድረኮችን እየፈጠሩ ከመሪሩ ሃቅ ጋር የማይገናኝ አስደናቂዲስኩራቸውን የመደስኮር ክፉ ልማዳቸው ነው ። በዚህ ዲስኩራቸው ያለሃፍረት ደጋግመው ከሚነግሩን ነገሮች መካከል ደግሞ በእጅጉ የሚያመው አመት ሊሞላው ሁለት ወራት ብቻ በቀረው የለውጥ ሂደት ለተፈፀሙና አሁንም እየተፈፀሙ ላሉ አስከፊ ኩነቶች  በማሳመኛነት የሚተርኩልን ትርክት  ነው ። የተፈፀመውንና  እየተፈፀመ ያለውን ምስቅልቅልና ውድመት እንኳን በእንደኛ አይነት ህብረተሰብ በአንፃራዊነት ተሳክቶለታል በሚባል ማህበረሰብ ውስጥ በሚደረግ የለውጥ ሂደትም የሚያጋጥም ነው”  የሚለውን አጠቃላይ እውነት (general truth) የራሳቸውን ሃላፊነትና ተጠያቂነት በወቅቱና በብቃት ለመወጣት ላለመቻላቸው መሸፋፈኛ ሰበብ  ( cover and excuse ) ሲያደርጉት መስማት ከሌላው ጉዳት ላይ ተጨምሮ  በእጅጉ ያማል ።

 

እስኪ በደፈናው የጥፋት ሃይሎች የምንላቸውን ተጠያቂ ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ እየራሳችን ማንነት ፣ ምንነት፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት በጥሞና እና በአርበኝነት መንፈስ እንመልከትና ያለብንን ግዙፍና ጥልቅ ጎደሎ ለማስተካከል ለእራሳችን ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን ሆነንና አድርገን እንደምንገኝ እናረጋግጥለት ።

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.