ለዉጡ – ተስፋዎቹና ተግዳሮቶቹ (ኆኀተብርሃን ጌጡ)

ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እንቆርጣቸዋለን.. ! (ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ)

… ኑና በምርጫና በሀሳብ ልዕልና ካሸነፋቹህን ሥሜና አቅፌ- ደግፌ ሥልጣኔን ለማስረከብ  ዝግጁ ነኝ… ! (ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ)

ለዉጡ - ተስፋዎቹና ተግዳሮቶቹ  (ኆኀተብርሃን ጌጡ) 1ልብ በሉልኝ፤ በሁለቱ አባባሎች ልዩነት ብቻ ለዉጥ እናያለን። ግን  ሁለቱም ኢሕአዴጎች ናቸዉ። የመጀመሪያዉን አባባል በምርጫ 97 ቅንጅት እንዴት እግሩ እንደተቆረጠ ስላየን፤ የሁለተኛዉን አባባል ወደ ተግባር መተርጎም ሁላችንም ወደፊት ከሚቀጥለዉ ምርጫ በሁዋላ፤ ቃል ተግባር ሲሆን በጋራ የምናየዉ ይሆናል። ችግሩ ግን የፖለቲካዉ ኩዋስ ሜዳ ጨዋታ ሲደራ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች በተቃዋሚዉ (በተፎካካሪዉ) ጎራ የሚገኙ መስለዉ አለመታየታቸዉ ነዉ። ይህን የተነሳሁበት ርዕስ ስላልሆነ፤ እዚህ ላይ ልግታና ወደምፈልገዉ ነጥብ ላምራ።

ለመሆኑ ለዉጥ ምንድነዉ? በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን በየትኛዉም አዉድ እየተዘወተረ የሚነገረዉ፣ … የተጀመረዉ ለዉጥ እንዳይቀለበስ ሁሉም ዘብ ሊቆምለት ይገባል! ወዘተ ወዘተ የተሰኙ ንግግሮች ከአዉራ ባለሥልጣኖች አንደበትም፤ ከዉሎ-ገብ ዜጋዉም ልሳን ተደጋግመዉ ሲነገሩ ይደመጣል። ለዉጥ (change) የሚለዉን ቃል የተለያዩ መዝገበ ቃላት ተመሳሳይ ፍቺ ሰጥተዉታል። ወደዚህ ዓይነቱ አጠቃላይ የለዉጥ ትርጉም ዉስጥ አልገባም። የተነሳሁበት የፅሁፌ ነጥብ እንብርት አይደለምና። ከጽሁፌ ጋር የሚዛመደዉ ትርጉም ግን …. ለዉጥ በአንድ አገር ዉስጥ የአንድን ኅብረተሰብ የፖለቲካ ሥርዓት ወይም የመንግሥትን መዋቅር በሌላ የፖለቲካ ሂደት የመተካቱን ክንዉን ለዉጥ ብለን መጥራት እንችላለን… የሚለዉን ስለ ለዉጥ የተሰጠዉን ትርጉዋሜ ነዉ። ከዚህ ትርጉም በመነሳትም ነዉ፤ ስለ ለዉጥ መኖር አለመኖር መነጋገር የምንችለዉ።

በሀገሪቱ መሠረታዊ ለዉጥ እየተካሄደ ነዉ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር የሚከብድ ይመስላል። ግን ደግሞ ለዉጥ የለም፤ ለዉጥ አልተደረገም ብሎ መካድም አይቻልም። በአፍሪካ አህጉር ባልተለመደ ሁኔታ እራሱ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸዉ ሥልጣን መልቀቅ በራሱ …ለዉጥ ነዉ.. የነበረ ሰዉ በሌላ አዲስ ሰዉ ተተክቷል። ይህም አዲስ ሰዉ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ይዞ ብቅ ብሏል። ግን ምን ዓይነት ለዉጥ? ከዶ/ር ዓቢይ አህመድ ሥልጣን መያዝ ጋር ተያይዞ በ 27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ብዙ አይተናቸዉ የማናዉቃቸዉ ድርጊቶች እየተከናወኑ እንደሆነ፤ ጆሮ ሰምቶ ለማመን የሚከብደዉ ክስተትም እየተፈጸመ እንደሆነ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ሌላኛዉን የሰቆቃ ዘመን መናፈቅ ይሆናል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት …ዳቮስ-ስዊዘርላንድ በተካሄደዉ ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም… (Davos- World Economic Forum) ላይ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ …በአሁኑ ጊዜ በሀገሬ በኢትዮጵያ አንድም ጋዜጠኛ እስር ቤት አይገኝም… ብለዉ በኩራት ሲናገሩ መስማት አይደለም፤  እንደ ሀገር መሪ እንኩዋን እርሳቸዉ ተራዉ ዜጋም ኩራት ተስምቶታል። ትናንት እርጉዟ ጋዜጠኛ (ሰርካለም ፋሲል) እስር ቤት ልጅዋን የወለደችበት ጊዜ ገና አልተረሳምና። በሀገሪቱ እየተፈጸመ የነበረዉን ግፍና ሰቆቃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ላለፉት ዓመታት ሕዝብን በመንፈስ ያሸፈቱት እሳቶቹ የኢሳት ጋዜጠኞች ትናንት በአሸባሪነት እንዳልተፈረጁ ሰሞኑን ወደ ሀገር ሲገቡ መንግሥት በእቅፍ አበባ ተቀብሏቸዋል። ይህን በዓይናችንም እያየን ለማመንም የሚከብደን በተግባር ግን እዉን እየሆነ ያለ እዉነታ ነዉ። የሞት መጥፎነቱ ግን ለደቂቃም ቢሆን ተነስቶ እየተፈጸመ ያለን ነባራዊ ክስተት ለማየት አለማስቻሉ ነዉ። ያ ባይሆኖ ኖሮ ግን እነ አበበ ገላዉን መንግሥት በቀይ ምንጣፍና በ VIP ላዉንች ሲቀበላቸዉ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለደቂቃም ቢሆን መመልከት ቢችሉ ኖሮ ሊኖራቸዉ የሚችለዉን ስሜት መረዳት እንዴት ያስገርም ነበር። እናም ተዓምር እንጂ ለዉጥ ብቻም አይመስልም። ለልጆቻችን ታሪክ ይሆናል ያልነዉ ነዉ በእኛ ጊዜ እየተፈጸመ እያየን ነዉ ያለነዉ። እናም ለዉጥ የለም ብሎ ማሰብም ጨለምተኝነት ነዉ። ግን ምን ዓይነት ለዉጥ? ገና እየደጋገምን የምናቀርበዉ ጥያቄ ነዉ። ተገቢዉን መልስ በተግባር እስክምናገኝ፣ በዓይናችንም እስክናይ ድረስ።

የሃያ ሰባት ዓመቱ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም ዶክትሪን ..አብዮታዊ ዴሞክራሲ.. ግን አሁንም የድርጅቱ መመሪያ ነዉ።  ግን ይህ ፍልስፍና እንደ ተቀየረ የሚያስመስል …የመደመር… ፖለቲካ (አረጋጊ ንግግር) ለዉጥ ለዉጥ የመሽተት ባሕርይ ያለዉ፤ በታኝ ሳይሆን አሰባሳቢ ፕሮፓጋንዳ በስፋት እየተሰበከ ነዉ። ሁሉም እንደሚያዉቀዉ ከዶ/ር ዓቢይ ሥልጣን መዉጣት በፊት ሀገሪቱ ለመበታተን ቁዋፍ ላይ ስለነበረች የመደመርን ወይም የአብሮነት ፖለቲካን አስተሳሰብ ይዘዉ ብቅ ማለታቸዉ በመላ ሀገሪቱ ተቀባይነታቸዉን አስመስክሮላቸዋል። ጭራሽ የኢሕዴግ ሰዉ መሆናቸዉም ተረስቶላቸዋል። መደመርም እንበለዉ ሌላም ሥም እንስጠዉ የለዉጥ ዘዋሪዉ ቡድን ከሃያ ሰባት ዓመቱ የተንሸዋረረ ፀረ ኢትዮጵያ አካሄድና አቁዋም እራሱን ቀይሮ  …ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገ… ነጠላ ዜማ እያዜመ ብቅ በማለቱ የሕዝብ ድጋፍ ተችሮታል። ኢትዮጵያዊነትን የሚያሽሞነሙኑ ንግግሮችም እስከሚበቃን ተነግሮናል። እንደ አሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያ በንግግር ደረጃ አልተሽሞነሞነችም ማለቱም ሳይቀል አይቀርም። በዚህ ብቻም ሳይበቃ ሀገሪቷ እራሷ ሱሳችን እንደሆነችና በእዚህ ሱስ የተጠመደም ለዘላለሙ ከእሷ ጋር ተቆራኝቶና ሥጋዎ ደሙ ተቀብሎ  ከመኖር ዉጭ ሌላ እድልም እንደማይኖረዉ የለዉጡ ደቀ መዛሙርት አበክረዉ ነግረዉናል። ለእዚህ አቁዋማቸዉም በቂ መወድስ ቀርቦላቸዋል።

ማልኮም ኤክስ የተባለ ጸሐፊ … እኔና አንተ ዴሞክራሲን እስካሁን በፍጹም አላየንም፤ እስካሁን ያየነዉ ማስመሰልን ብቻ ነዉ… ይለናል። በሀገራችን እየተካሄደ ያለዉ ለዉጥ በእርግጥም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ግንባታ አስተማማኝ መሠረቶችን እየጣለ ነዉ? ወይስ በመፈራረስ  ቁዋፍ ላይ የነበረችዉን አገር በማረጋጋት እራሳቸዉን ለማዳንና ድርጅታቸዉ ኢሕአዴግን እንደገና  ነፍስ እንዲዘራመበት ለማድረግ የሚደረግ ለዉጥ መሰል የዘመነ አካሄድ ጅማሮ ነዉ? እንግዲህ ሽልም እንደሁ ይገፋል ነዉና ማመንን የሚያጠናክረዉ ማየት በመሆኑ ጅማሮዉን በአንክሮ እንከታተለዉ። የለዉጡ ጋሬጣዎች እንድንሆንም አይጠበቅብንም። እነሱም (የለዉጡ አራማጆች)  ከመጋረጃዉ በስተጀርባ የተደበቀ አጀንዳ ሳይኖራቸዉ የሚሉትን ሆነዉ እንዲገኙ ይጠበቅባቸዋል።

ለዉጡንም በለዉጥነቱ እንድናየዉና እንድንቀበለዉ የሚያስገድዱን ሁኔታዎች ዛሬን ከትናንት ጋር የግድ በንፅፅር ማየት ስላለብን ነዉ። ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በአሜሪካ ጉብኝታቸዉ ወቅት ለአንዲት ጋዜጠኛ በሰጡት የጥያቄ ማብራሪያ መልስ … የትናንቱ የሃያ ሰባት ዓመት ጊዜ የቆሸሸ ዘመን ነበር… በማለት ገልጸዉታል። ትናንትን ከዚህ በተሻለ አባባል ለመግለፅ ቃላት ማግኘት ይከብዳል። ግን ኀይለ መለኮት መዋዕል የተባሉ ፀሐፊ እንካስላንትያ በተባለ መፅሓፋቸዉ

የባሰ አታምጣ አትበሉ፤

የተሻለ እንዲገኝ ታገሉ።

በማለት እንደገለጹት ከትናንት የባሰ እንዲመጣ አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ዛሬና ነገ ከትናንቱ የተሻለ፤ እጅግ የተሻለ እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዉጡም የሚፈለገዉ ዛሬና ነገ ከትናንቱ በዓይነቱ የተለየ መሆኑን ዋስትና እንዲሰጠን ነዉ። ዋስትናዉ ግን የታዋቂዉን ጋዜጠኛና  የነፃነት ታጋይ የተመስገን ደሳለኝን አባባል ልዋስና ..ከስብሐት ወደ ሙፈሪያት.. መሸጋገር አይደለም። ወይም ከሐጎስ ወደ ገመቹ ማዘንበል መሆን የለበትም። ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገ  የመደመር ፍልስፍና ለዉጥ፤ ጫልቱንም፤ ከበደንም፤ ጠንክርንም፤ ቶሎሳንም፤ ወለተኪዳንንም ወዘተ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያንን በእኩልነት ዓይን ሊያስተናግዳቸዉ ይገባል። ያንየ የለዉጡ ተስፋዎች በሁሉም አእምሮ ያንዣብባሉ። ሁሉም  ለዉጡ የመጣዉ ለሁላችንም ነዉ ብሎ ኢትዮጵያዊነት ስሜቱን ይተረጉምበታል። አዲስ አበባም የከተማዋ ኗሪዎች ከተማ እንጅ፤ ሌላ ባለቤት እንደሌላት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያስፈልጋል። ምክንያቱም ለአዲስ አበባ የእኔነት የባለቤትነት ንትርክ መነሻዉ ሕገ መንግሥቱ … ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይኖራታል፤ ይህም ወደፊት በሕግ ይወሰናል… ስለሚል ልዩ ጥቅም ሲባል ባለቤትነትንም ሊያካትት ይችላል። አሻሚ ነዉ ትርጉሙ። ለብዙዎቹ የሀገሪቱ ችግሮች ምንጩ ሕገ መንግሥቱ ሆኖ ሳለ፤ አሁን እተደረገ ያለዉ ሩጫ ግን ምርጫ ማካሄድ ነዉ። የምርጫዉ መደረግ በራሱ ግን ብቻዉን ችግሮቻችንን አይፈታም። የተዳፈነ እሳት ሲነድ ሁሉንም ማቃጠሉ አይቀሬ ነዉና።

ግራም  ነፈሰ ቀኝ የዶ/ር ዳኛቸዉ አሰፋን አባባል ልዋስና ለዉጥ አዎ, ግጥም ያለ ለዉጥ አለ። የተገኙትና እየታዩ ያሉት የለዉጡ ትሩፋቶችም በተደጋጋሚና በየአጋጣሚዉም  የተገለጹና እየተገለጹም ስለሆነ ወደዚያ ዝርዝር በመግባት የአንባቢን ጊዜ መሻማት አልሻም። ለአንድ መሠረታዊ ለዉጥ አስተማማኝ የሆኑት የመሠረታዊ ተቁዋማት ግንባታም ጅማሮዉ ተስፋ ሰጭ ነዉ። በማጠናከር ፋይዳ እንዲኖረዉ ማድረግ ነዉ። ግን ቀሪዎቹ ተስፋዎች በአብዛኛዉ በንግግር የታጀቡ እንጂ፤ በለዉጥ መርህ ደረጃ እንደ ፍልስፍና የሚታዩ አይደሉም። የለዉጡ የመርህ ፍልስፍና ገና ነጥሮ አልወጣም። ምንድነዉ በአሁኑ ጊዜ የኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ርዕዮተዓለማዊ ፍልስፍናዉ? የቀድሞዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ? ወይስ……? መቼም መደመርን እንደ ድርጅቱ እንደሚመራበት አይዲዮሎጂ አድርገን እንደማንወስደዉ ግልፅ ነዉ። የደርግ … ኢትዮጵያ ትቅደም… የተሰኘዉ አሰባሳቢ መፈክር ከሰኔ 1966 እስከ ህዳር 1967 ዓ.ም ሶሻሊዝም ርዕዮተዓለማዊ መርሁ መሆኑን እስካወጀበት ጊዜ ድረስ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን የሚያስቀድም መሆኑን በቅስቀሳ መልክ ተጠቅሞበታል። ምኞቱ ሌላ ተቃራኒዉን ድርጊት አስከተለ እንጂ ያዉም …ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም… በሚል ምኞት የታጀበ ምኞት ነበር።

ዶ/ር ዓቢይና የለዉጡ ቡድንም የመደመርን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ዙሪያ የማሳባሰብ ዘመቻ በስፋት እየሰራበት ይገኛል። ላለፉት 27 ዓመታት ደቃቅ ክልሎች እንደ ሀገር ተፈጥረዋል። የየክልል ንጉሶችም  በብዛት ዘዉድ ጭነዋል። ኢትዮጵያዊነትን ረስተዋል። ታሪክንም በመቶ ዓመት ገድበዋል። ባጭሩ ኢትዮጵያዊነት እንዲከስም ተዘምቶበታል። ይህን ፀረ ኢትዮጵያዊነት መንግሥታዊ አቁዋምና አስተሳሰብ  ነዉ፤ እነ ዶ/ር ዓቢይ እያፈረሱ ያሉት። በመደመር ፍልስፍና ግንብ ላይ ኢትዮጵያዊነትን እየገነቡ ያሉት። እሰየዉ ነዉ። ግን እንደ መንግሥት ርዕዮተዓለማዊ መርሃቸዉ ምንድነዉ? የብዙ አገር መሪዎች በምርጫ ዘመቻ ወቅት የሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ መሪ ቃል አላቸዉ። ለምሳሌ ከቅርቦቹ የአሜሪካ ፕሬዚዴንቶች የምርጭ ቅስቀሳ ብንነሳ ባራክ ኦባማ …yes, we can… ወይም ዶናልድ ትራም… America first!… በማለት የመራጮቻቸዉን ቀልብ መሳብም መመረጥም  ችለዋል። ይህ ግን የአሜሪካ መንግሥት  እንደ መንግሥት የሚመራበት አይዶሎጂ አይደለም። ከምርጫ በሁዋላ ፋይሉ የተዘጋ ሰነድ ሆኖ ነዉ የሚቀረዉ።

በተወሰነ ወቅት ለተወሰነ ዓላማ አንድን ሕዝብ በአንድ ማዕከላዊ ማሰባሰቢያ መሪ ደወል በዙሪያ ማሰለፍ ይቻላል። በመርህ ደረጃ ግን አሁንም ኢሕአዲግ አይዶሎጂዉን ስለ መቀየሩ እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም። እንዲያዉም በሰሞኑ ዜና የአንድ ሬድዮ ጋዜጠኛ…የቀድሞ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ የነበሩት ባለሥልጣን አቶ በረከት ስምኦን…. በማለት ዜና ሲያስተላልፍ ጆሮዬ ዜናዉን አስተናግዷል። የቀድሞዉ መንግሥት…? ለመሆኑ የትኛዉ አዲስ መንግሥት ነዉ ሀገሪቱን እየመራ ያለው? በዚህ ብቻም ሳንወሰን ይህን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ እያለሁ ለዚህ ለታየዉ የነጻነት ብልጭታ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኝና የዕድሜ ልክ ፍርደኛ የነበረ አንድ የማከብረዉ ሰዉ ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጠዉ ቃለ መጠይቅ …. ኢሕአዴግ የት አለ አሁን? ብሎ ሲገልፅ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ። ኢሕአዴግ የለም ካልን አዲሱ መንግሥት … ቲም ለማ… የሚባለዉ መሆኑ ነዉ። የቲም ለማ ሀገራዊ አይዶሎጂ ምንድነዉ? መደመር? ኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑ? በጄ ከዚያስ ሲቀጥል…….. ሁሉንም መሥሪያ ቤቶች በአንድ ብሔር ተወላጆች ለማስያዝ መሯሯጥ? ይህ አሉባልታ ሳይሆን በአዲስ አበባ በሰሞኑ የባንክና መሰል መሥሪያ ቤቶች ድልድልና ሹመት አሰጣጥ አግጦ የሚታይ እዉነታ ስለመሆኑ አዲስ አበቤዎች የዓይን ምስክሮች ናቸዉ። ከየአቅጣጫዉ ወደ አዲስ አበባ ለሚጎርፉ ወዘ ልዉጥ ሰዎች የአዲስ አበባ ኗሪነት መታወቂያ አየሰጡ ማስፈርም  የአደባባይ ምሥጢር እየሆነ ነዉ። ይህን ምስጢር ያዋጣቸዉ  ወ/ሮ ሰናይት ታደገ ከሥራ ገበታዋ እንድትባረር (በሁዋላ ተመልሳለች ቢባልም) የማድረጉ አንድምታስ ምን የሚሉት እርምጃ ነዉ? አላግባብ የሚፈጸምን ብልሹ መንግሥታዊ አሰራር ለሚያጋልጥ የመንግስት ሰራተኛ ሽልማት ይገባዋል እንጂ ከስራዉ ሊፈናቀል  ከቶዉኑ አይታሰብም። ዘረኝነት ደዌ ነዉ፤ ዘረኝነት ነቀርሳ ነዉ ካልን እንጸየፈዉ፤ እንራቀዉ እንጂ፤ የትናንቱን የዘረኝነት አሰራር አንድገመዉ። ለመተቸት ተቸኮለ እንዳይባል፤ በእንቁላሉ ሃይ ያልተባለ (ያልተቀጣ) ሌባ ነገ ዝሆን ወይም በሬ ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ ላለመያዙ ማስተማመኛ አይኖርም። የተጀመረዉ ለዉጥ ስር እንዲሰድ እንሻለን። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ምድር እንዲያብብ እንፈልጋለን። እናም የትናንቱን ችግር ላለመድገም ካሁኑ ለዉጥ አራማጆችን እየሄስን በተመሳሳይም ድጋፋችንን ልንሰጣቸዉ ይገባል። ከሁሉም በላይ የተጀመረዉ ለዉጥ ስር እንዲሰድና እንዲሰምር ከተፈለገ፤ መንግሥትም፤ ሕዝቡም አካፋዉን አካፋ፤ ዶማዉን ዶማ ብሎ ደፍሮ መናገር መቻል ይኖርበታል። ለዉጡ እንዳይደናቀፍ በሚል ሥጋት ብቻ ነገሮች እየተዳፈኑ ከታለፉ፤ ዘግይተዉ ለሚፈነዱ የተቀበሩ ቦንቦች መፍትሔያቸዉም  የዘገየ ይሆናልና ጥንቃቄ የሚያሻዉ አካሄድን መምረጥ ግድ ይላል።

ሕወሓት/ኢሕአዴግ የለም ወይም ሞቷል ማለት የምንችለዉም ላለፉት ሃያሰባት ዓመታት ከተለከፍንበት የዘር በሽታ ሙሉ ለሙሉ መፈወስ ስንችል ነዉ። የበሽታዉ ሰንኮፍ ሲነቀል ነዉ። የሀገር ሌቦች በብሔር ጫካ መደበቃቸዉ ሲቀርና በፍትሕ አደባባይ ቀርበዉ በሕግ ፊት እንደ ማንኛዉም ዜጋ መጠየቅ ሲችሉ ነዉ። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለማዊ መመሪያዉ ተገንዞ ሲቀበር ነዉ። ነፍሱ ከሥጋዉ ተለይታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወሪደ መቃብር መዉረዷን ስናረጋግጥ ነዉ። ከላይ ከአናት የጀመረዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ እስከ ታች ወርዶ መዋቅሩን መዘርጋት ሲችል ነዉ። ዶ/ር ደብረፅዮን እንደ ቲም ለማ ቡድን ሲያስብ ነዉ። ጭቃና ምስለኔዉ ሹም በለዉጡ የፈለገ ዮርዳኖስ ውኃ ከልቡ ሲጠመቅ ነዉ። አያድርገዉና የሰይጣን ጆሮም ይደፈንና የቲም ለማ ቡድን የሚባለዉ አዳልጦት፤  ወይንም ዳዊድ ኢብሳ እንቅፋት ሆኖበት ቢወድቅ፤ ወይንም የመቀሌዎቹ ሽማግሌዎች እርግማን ቢደርስ፤  ምንድነዉ የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ? ዳዊድ ኢብሳ? ወይስ እንደገና ሞንጀሪኖ…? የቀድሞዉ የሶቪዬት ሕብረት ፕሪዚደንትና ዓለምን በመቀየር ታሪካዊ አሻራቸዉን ያስቀመጡት ሚካኤል ጎርባቾቭ በአንድ ወቅት የጀርመን አገር ጉብኝታቸዉ አንድ ጋዜጠኛ …ሶሻሊዝም ሞቷል ወይስ አለ….? ብሎ ለጠየቃቸዉ ጥያቄ …ሞቷልም፤ አለም አልልህም፤ በእርግጠኝነት የምነግርህ ግን በጸና መታመሙን ነዉ… ብለዉ እንደመለሱለት በእርግጥም ኢሕአዴግ ታሟል። ርዕዮተዓለሙም ቆስሏል። ግን ማነዉ ቀጣዩ ባለ ወር ተረኛ ባለ ፅዋ? ፅዋዉን ተረካቢ? ይታወቃል? ኢሕአዴግ በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ሞቷል ባይባልም ስለመታመሙ አስረጅ አያስፈልግም። ስላለመሞቱ ግን በየቦታዉ የሚታዩ ርችቶች አሉ። በየቀኑ የሚያዘዉ ቁጥር ስፍር የሌለዉ ገንዘብና በየአቅጣጫዉ ሲዘዋወር የሚያዘዉ የጦር መሳሪያ ነገ የእርስ በርስ ጦርነት ለማካሄጃ ስላለመሆኑ ማስተማመኛ የለም። እንዲያዉም አሁን ባለዉ ሁኔታ ከቀጠለ (ማለትም ሰላምና መረጋጋት ካልተገኘ) በብዙ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎችም መክፈት እንደማይቻል ነቢይ መሆን አያስፈልግም።

ዶ/ር ዓቢይ የመደመርን አስተሳሰብ ለምርጫ ቅስቀሳ ዓይነት ዘመቻ ለመጠቀም ሳይሆን በየብሔሩ የአገር ካርታ ሰርቶ አካኪ ዘራፍ ለሚለዉ ብሔርተኛ ቡድን ያለን አንድ አገር ነዉ፤ ከመደመር ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖረንም በማለት የማረጋጊያ ኢትዮያዊነት ንግግሮችን ከበቂ በላይ የገለጹበትና የተጠቀሙበት አካሄድ ይመስላል። ይህ መሆኑንም ከአካሄዳቸዉ እንገነዘባለን። በዚህ አስተሳሰባቸዉም በብዙ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ክብርና ሞገስ አግኝተዉበታል። ነጠላ ዜማም ወጥቶላቸዋል። ወደ ወለጋ ነዉ እንጅ፤ ብቅ ማለት ያልቻሉት ወደ ባሕርዳርና ጎንደር ጎራ ሲሉም ቄጠማ ተጎዝጉዞላቸዋል። እቅፍ አበባም ተበርክቶላቸዋል። … ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገዉ.. የመደመር አስተሳሰባቸዉ ቅቡልነትን አግኝቶላቸዋል። ግን በሁሉም ክልሎች አይደለም። በእራሳቸዉ አንደበት እንደተነገረዉ አንደኛዉ ክልል እሳቸዉን ለመግደል የእሳቸዉን ወዳለበት አካባቢ የመምጣት ጉብኝት ይጠባበቃል። ሌላኛዉ ክልል ደግሞ በወንጀል ተጠርጥረዉ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዉ ተፈላጊ ወንጀለኞችን ደብቆ የሽፍትነት ተግባር ይፈጽማል። ለማዕከላዊ መንግሥት አልታዘዝም ማለት፤ እኔ ነኝ እንጅ መንግሥት አንተ አይደለህም፤ አንተን አላውቅህም እንደ ማለትም ይመስላል። … በእኛ ጊዜ  መንግሥታችን ጠንካራ ስለነበር ..አሸባሪ.. መስሎ የታየንን የመን አገር ድረስ ርቀን ሂደን ማስመጣት እየቻልን በነፍሰ በላነቱ የሚታወቀዉን ጌታቸዉ አሰፋን እንኩዋ ከመቀሌ አዲስ አበባ ማስመጣት ያልቻለ መንግሥት ነዉ ያለን… በማለት የለዉጥ አራማጁን መንግሥት ሲያፌዙበት ይደመጣሉ። ምክንያቱም ለእነሱ መንግሥት ማለት የሃያ ሰባት ዓመቱ ጥፍር ነቃዩ ወይንም ሴት ልጅ በወንድ ልጅ ላይ ሽንት አሸኝ ዓይነት መንግሥት ነበራ የለመዱት!  በታሪካችን እንዲህ ዓይነት መንግሥት ላይኖረን የዚያን ዓይነቱ ቆሻሻ የታሪክ ምዕራፋችን እስከ ወዲያኛዉ መዘጋቱ ገና አልገባቸዉም። በእርግጥ ዶ/ር ዓቢይም ገና መንግሥታቸዉ ስላልተረጋጋና በሁለት እግሩም ስላልቆመ፤ እራሳቸዉንም ወልዶ አሳድጎ ለዚህ ያበቃቸዉ  መንግሥት  ስለሆነ፤ ከዚህ በላይ ተራምደዉ የመንግሥትነት ሥልጣናቸዉንም መቶ በመቶ ለመጠቀም የተቸገሩ መስሎ ይታይባቸዋል። በእርግጥ ጊዜ የሚፈታቸዉ ሀገራዊ ችግሮች መኖራቸዉንም ልንረዳላቸዉ ይገባል። በእርግጥ ቸኩለዉ አላስፈላጊ እርምጃ እንዲወስዱ ለመገፋፋትም እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ቢያንስ መጀመሪያ ቃል እንደገቡት … መንግሥት ሁሉንም ነገር ለሕዝብ ግልፅ ያደርጋል… እንደተባለዉ ከሰኔ አስራ ስድስቱ በእሳቸዉ ላይ የግድያ ሙክራ ያደረጉትን ጨምሮ እስካሁን ለሕዝብ ይፋ አለማድረግ  የቃልን ወደ ተግባርነት አለመቀየር ስንመለከት ኪሎ ባይቀንስም የቃልና የተግባርን ሆድና ጀርባነት ስለሚፈታተንባቸዉ ሊያስቡበት ይገባል።

ይህም ለዉጡን እየተፈታተነ ያለዉ አንዱ ችግር ነዉ። በእርግጥ እርሳቸዉ … ኢትዮጵያ ዉስጥ ወንጀል ሰርቶ ያልታሰረ የለም፤ ልዩነቱ እራሱን ያሰረና በመንግሥት እስር ቤት ሆኖ ቤተሰብ እየጠየቀዉ፤ ቲቪ እያየ መፅሐፍ እያነበበ  መገኘት መቻሉ ነዉ … በማለት አሽሞንሙነዉና እንዲያዉም ሸዉደዉ አልፈዋል ማለቱም የሚቀል ይመስለኛል። ይህን ሲሉም ሁሉም ፈገግታዉን ችሯቸዋል። ጭብጨባዉንም አልነፈጋቸዉ። እዉነታዉ ግን የፌዴራል መንግሥት በሁሉም ክልሎች ትዕዛዝ የመስጠትም ሆነ የማስፈጸም ሥልጣንን ገና በእጁ አለመጨበጡን ያመላክታል። ልክ በአንድ ወቅት 250 የሚሆኑ ታጣቂ ወታደሮች ወደ ቤተ መንግሥት ባመሩበት ወቅት እስፖርት አሰርተዉ ከላኩዋቸዉ በሁዋላ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መልሰዉ …እርር ድብን እያልኩም ቢሆን ሸኘዋሁዋቸዉ … እንዳሉት ዓይነት ምፀታዊ አነጋገር መሆኑ ነዉ። ይህ እንደ ቀላል የሚታይ ችግር ሳይሆን በአንድ አገር ዉስጥ ጀርባዉን የሰጠ፤ ለማዕከላዊ መንግሥት የማይታዘዝ ያመፀ ቡድን አለ። በወንጀል ተጠርጣሪ ግለስቦች በዓለም አቀፍ የ…ኢንተርፖል… ሕግ እንኩዋ እንዳይፈለጉ የመሸጉት እዚያ አገር ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያ ማለት አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም። ከሁሉም በላይ የፌዴራል መንግሥቱ የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ መረጋገጥ መቻል አለበት። ያንዬም ነዉ ስለምርጫ መነጋገርም የሚያስፈልገዉ። ምርጫ ብቻዉን ግን ግጭቶችን አይፈታም። ሰላምም አያሰፍንም። እራሳቸዉን እንደ መንግሥት የቆጠሩ የከተማ ሽፍታ አክቲቪስቶች እንደ ፈለጉ ትዕዛዝ በመስጠት እንዲህ… ማድረግ እንችላለን… እያሉ  በየአደባባዩ እየፎከሩ ባሉበት ሁኔታ፤ ምን ዓይነት ሰላማዊና ፍትሐዊ  ምርጫ ሊካሄድ እንደታሰበም ግልፅ አይደለም።

ሌላዉና ዋናው ተግዳሮት ባሁኗ ኢትዮጵያ የፖለቲካዉ ባሕርይ ተሳክሮ ወይም እጅና እግሩን አጥቶ መገኘቱ ነዉ። በተለይም የማንነትና የዜግነት አደረጃጀት የፖለቲካ አካሄድ ፖለቲካዉን አጡዞታል። እንዲያዉም ምስቅልቅሉንም አዉጥቶታል ማለቱ ሳይቀል አይቀርም።። ኢትዮጵያን የማዳን፤ የዲሞክራሲ ሥርዓት መስፈኛዉ የመንግሥተ ሰማይ መግቢያዉ በር ትክክለኛዉ  አካሄድና አደረጃጀት የትኛዉ መንገድ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መሲህ አልተገኘም። ሁሉም መንገድ የጨረባ ተስካር ሆኗል። የማንነትና የዜግነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት ችግሮችን ሳንፈታ፤ በፌዴራሊዝም አወቃቀር ሥርዓተ መንግሥት ይዘት፣ በሕገ መንግሥት መሻሻል ጥያቄ ዙሪያ ለዉጦች ሳይደረጉ ወይም አንድ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ምርጫዉ ይራዘም፤ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄድ በሚለዉ ሀሳብ ጊዜ መግደል መሠረታዊ ችግሩን ደብቆ ላይ ላዩን መጋለብ ያስመስላል። የሚፈለገዉ ኢሕአዴግ ወቅት ጠብቆ ማርጫ አካሄደ መባሉ ነዉ? ወይንስ በምርጫዉ ከእስካሁኑ በተለየ ለዉጥ ማስገኘቱ ነዉ ችግራችንን በዘላቂነት መፍትሔ የሚያስገኘዉ?

በለዉጡ ዙሪያ እንደ መሠረታዊ ችግርም ባይሆን ሌላዉ እንደ ቀላል የማይታየዉ ችግር ከሙገሳና መወድስ ከማቅረብ ባሻገር ለዉጥ አራማጆችን መንቀፍ ወይም በእነሱ ላይ አግባብ ያለዉ ሂስም ማቅረብ እንደ ለዉጥ አደናቃፊ የመታየት አዝማሚያ እያደገና እየጎለበተ መምጣቱ ነዉ። ይህ በቀላሉ መታየት የሌለበት አደገኛ አካሄድ ነዉ። አንዱም አምባገነኖችን የሚወልደዉ እነሱን ሰዉ አይደሉም ብሎ ሥዕል መሳል ነዉ። የግብፆችን ሳይሆን የእራሳችንን ፈርኦኖች  እራሳችን እንዳንፈጥራቸዉ  ፍቅርም በድርበቡ ቢሆን ይመረጣል። በተለይም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና  የሚዲያ ሰዎች ከባሕላዊ የአዝማሪነት ተጫዋቾች ተለይተዉ መገኘት መቻል ይኖርባቸዋል። በተለምዶ አዝማሪነት (አመስጋኝ) ሰዎችን እያወደሱ፤ የማይገባቸዉን ክብርም እየሰጡ የዕለት ጉርስን ለማግኘት መሯሯጥን ያጣቃልላል። ልክ ባንድ ወቅት ባንድ አጋጣሚ፤

ከወለዱም አይቀር ከተንበረከኩ፤

መሪ እንደ መንግሥቱ ወንድ እንደ መላኩ።

ተብሎ እንደተሸለለዉ፤ በተከታዩም መንግሥት ደግሞ …. ለባለ ራዕዩ መሪም

…የዓይኑ ቅንድብ ማማሩ…

ተብሎ እንደ ተዘፈነላቸዉ ማለት ነዉ። በእንደዚህ ዓይነቶቹ ሆድ አደር አዝማሪዎች አስተሳሰብ የህብረተስቡ ህሊና መበረዝ አይኖርበትም። ፕሮፓጋንዳ ሲደጋገም እዉነት የመመስል ባሕርይ አለዉና። ጊል ከርቲማንቺ የተባለ ጸሐፊ … ፕሮፓጋንዳ እንደ ሄሮይን አደገኛ ነዉ። ሰዎች ሳያጤኑት ሙሉ የማሰብ አቅማቸዉን ያሟሟል…። እንዳለዉ እንዳይሆን በእጅጉ ጥንቃቄ ያሻዋል። አሁን በሀገራችን እየታየ ላለዉ ለዉጥም እንዲህ ዓይነት አዝማሪዎች ብቅ ብቅ ማለታቸዉ አልቀረም። በርካታ ነጠላ ዜማዎችንም አዉጥተዋል። በአራት ሰዎች ብቻ ለዉጥ አልመጣም። ግን እዉነት እንነጋገር ከተባለ የለዉጡ ባለቤት ማነዉ? አንድ ጸሐፊ

…. ቀን ይወስዳል አንጂ፤ ሞቆ እስከሚጋጋል፤

የተበደለ ሕዝብ የትም (ምንጊዜም) ድል ያደርጋል….

እንዳለዉ የድሉና የለዉጡ ባለቤት ማንም ሳይሆን ሕዝብ ነዉ። በሕዝብ መካከል እራሳቸዉን እንደ ሻማ ያቀለጡ የሕዝብ ልጆች ግን አሉ። የነፃነት ቀንዲሎቹ እነሱ ናቸዉ። ሥማቸዉ ሳይዘረዘር ሕዝቡ የቁርጥ ቀን ልጆቹን ያዉቃቸዋል። ሕዝብ ባሕር ነዉ። ባሕሩን እንደ ሙሴ ቀዝፈዉ  በሕይወታቸዉ ቤዛነት ዋኝተዉ አሻግረዉታል። በሕይወት የሌሉም፤ ለምሳሌ በሥርዓቱ ተንግፍግፎ እራሱን በእሳት አቃጥሎ  የሞተዉ መምሕር የእኔ ሰዉ ገብሬ (ቢቢሲ ሳይቀር በወቅቱ ዜና ያቀረበበት)  ዓይነቶቹም ግንባር ቀደም የለዉጡ ባለቤቶች መሆናቸዉ ሊካድ አይገባም። ግን አንድ ፀሐፊ …ማመፅ ከፈለግህ በሥርዓቱ ዉስጥ ሆነህ አምፅ። ምክንያቱም በሥርዓቱ ዉስጥ ሆኖ ማመፅ ከሥርዓቱ ዉጭ ሆኖ ከማመፅ ይበልጥ ኃይል አለዉና… እንዳለዉ የቲም ለማ ቡድን ከዉስጥ ሆኖ ዉጭ ሆኖ ያመጸዉን ኃይል በመቀላቀሉ የሕዝብ ድል ሊገኝ ችሏል። የዉስጥ ኃይሉ ደግሞ ይህን እርምጃ ለመዉሰድ የተገደደበት ጥበብ መንግሥታቸዉ በነበረበት መንገድ ጉዞዉን ከቀጠለ ተያይዘዉ መጥፋታቸዉን በሚገባ መገንዘብ በመቻላቸዉ ነዉ። ሌላ ታሪክ ሳንበርዝና ሳንደልዝ የድሉ ባለቤት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነዉ። ቁምነገሩ ግን የድሉ ባለቤት ማን መሆኑን ማረጋገጡ ላይ አይደለም። እሱ ላይ ጊዜ ማጥፋትም አያሻም። ይህን ወደፊትም ታሪክ ጸሐፊዎች በታሪክ ዓምዶች ላይ ማስፈራቸዉ አይቀሬ ነዉና ለእነሱ እንተዉላቸዉ። ቁምነገሩ የተገኘዉ ድል (ለዉጥ) በተፈለገዉ መንገድ ተጉዞ በሀገራችን ነፃነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን መቻል ነዉ። ይህ ተግባር ደግሞ በለዉጥ አራማጁ ትከሻ ላይ ብቻ የወደቀ አደራ ብቻ አይደለም። የሁሉም ዜጎች ሀገራዊ ግዴታ መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ግድ ይላል።

እንደ ማጠቃለያም፤ ፖለቲከኞቻችን ብቻ ሳይሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች በአጠቃላይ የአስተሳሰብ ለዉጥ ልናድርግና ከእራሳችን ጋርም እርቅ እንድናደርግ ይጠበቅብናል። ያለፉ ሥርዓቶችንና መንግሥታትን የመራገምና በእሬሳ ላይ የመፎከር፤ የዛሬን የማወደስ፤ (የቀን ሰዉ የመሆን ምልክት) ጎታች ከሆነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመላቀቅ ለነገዉ ትውልድ ጭምር የሚበጅ አሸጋግሮ የሚያሳይ የሩቅ እይታ ማነጣጠሪያ መነፅር ልንጠቀም ግድ ይለናል። በተለይ የመገናኛ አዉታሮች (ፕሬስ በአጠቃላይ)  የቂም በቀል አስተሳሰብን፤ ዘረኝነትን በመዋጋት ዛሬን ብቻ ከማወደስ የትንሽ ኪሎ ሜትር ርቀት በመጉዋዝ  ነገን አሸጋግሮ የማየት አስተሳሰብ በሕዝባችን አእምሮ ለማስረፅ ቀን ከሌት ተግተዉ ሊሰሩ ይገባቸዋል። ከይደልዎና ከአሸርጋጅነት የወረብ ሸብሸቦ ማሳያ ማህሌት ዝማሬያቸዉን አቁመዉ እንዲሁም ካለፈ እርግማን ፖለቲካ (የወደቀ ግንድ ምሳር የማብዛት) ቅስቀሳ ላይ አብዛኛዉን ጊዜያቸዉን  ማጥፋት አላስፈላጊ መሆኑንም ሊያጤኑት ግድ ይላቸዋል። በባሕላችንም ዘወትር በእሬሳ ላይ የሚፎክር ጀግና ተብሎ ተወድሶ አያዉቅምና። ይች አገር የእኔ፤ የሁላችንም ናት፤ የሚል እምነት በሕዝባችን አዕምሮ መስረፅ ሲችል ነዉ፤ ችግሮቻችን ሁሉ በጋራ ሊወገዱ የሚችሉት።

ከሁሉም በላይ ለጋራ የሆኑ እዉነቶች አለመገዛትና በእራስ ሜዳ ብቻ እየሮጡ ሌላኛዉን ለማሸነፍ የፖለቲካ እሽቅድድም ማድረግ ሁልጊዜም አድሮ ጥጃነት ነዉ። አንድ ከተማ ባለቤትነቷ የከተማይቱ ኗሪዎች መሆኗ እየታወቀ፤ የእኔ ነች እንጅ ያንተ አይደለችም በሚል እሰጥ አገባ ፉክቻ ጀምሮ አይቀሬ እስከሚመስለዉ  ጦር ሰበቃ ድረስ በሶሻል ሚዲያና በየመገናኛ አዉታሮች እንካስላንትያ ሲገጥሙ መዋሉ የምሁርነት መለኪያ ሳይሆን በፊደል ገበታ አቡጌዳና መልዕከተ ዮሓንስ ገበታ ላይ ተገትሮ መቅረት ነዉ። የብሽሽቅ ፖለቲካ እንኩዋንስ አገር ሊያድን ወንዝ አያሻግርም። ከጎረቤት ኗሪ ጋርም በጎሪጥ ከመተያየት አልፎ እሳት እንኩዋ አያጫጭርም። አክቲቪስቶችም ሆኑ አጉራ ዘለል ፖለቲከኞቻችን በሆነ ባልሆነዉ አርስት ሶሻል ሚዲያዉን ሲያተራምሱትና ሕዝባችንንም ግራ ሲያጋቡት ከሚኖሩ መንግሥት የማድፈጥ አቁዋሙን ሰብሮ በመዉጣት በሀገራዊ ጉዳዮች ትክክለኛዉን አቅጣጫ ማሳየት መቻል ይኖርበታል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ጉዳይና በሰንደቅ ዓላማ ጥያቄ ዙሪያ መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ?

የመንግሥት አቁዋም ከየትኛዉ ወገን ነዉ? መቼም በአንድ አገር የፌዴራል ክልል መንግስታት የየራሳቸዉ መለያ ሰንደቅ ዓላማ ኖሯቸዉ የሀገሪቱ መለያ ዓርማ ግን አንድ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነዉ መኖር የሚገባዉ። እስከ መቼ ነዉ የነገ ሕልመኛ … መንግሥታት… ሰንደቅ ዓላማ እየተያዘ በየአደባባዩ የሚፎከረዉ? የአዲስ አበባ ጉዳይም እንደዚያዉ ነዉ። አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎችና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወይንስ የነገዋ ኦሮሚያ ፊንፊኔ የሚል ስያሜ አግኝታ ለዋና ከተማነት እየታጨች ያለች?

አክቲቪስቶቻችን ግራ ያጋባሉ፤

ጫካዉ ቀርቶባቸዉ ዋና ከተማ ላይ ትግል ይገጥማሉ፤

ፊንፊኔ የእኛ ናት፤

በረራ የእኛ ናት፤

እየተባባሉ የሸገር ሰዎችን ግራ ያጋባሉ፤

የኗሪዉን መብት በቁም ይገፋሉ።

እነ ሥም አይጠሬስ ታዉቁዋል ዓላማቸዉ፤

እኛን  የናፈቀን የመንግሥት አቁዋም ነዉ።

እንዲህ ዓይነት አወዛጋቢ ጉዳዮችን መንግሥት ማድፈጡን አቁሞና ሰምቶ እንዳልሰማ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ከማለፍ መፍትሔ እንዲሰጥ (ካስፈለገም ሕዝበ-ዉሳኔ) በማሰጠት እልባት ሊያስገኝለት ይገባል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለኢትዮጵያዉያን …ሱስ.. ናት ከተባለ፤ አዲስ አበባም እንደ ከተማ ለሸገር ልጆች ሱሳቸዉ ናት። አራት ነጥብ። ሌላ ሂሳባዊ የፖለቲካ ሎጅክና የምርምር ሳይንስ አያስፈልገዉም። ከንቲቫዉም ሸገሮች የመረጡት ከንቲቫቸዉ ይሆናል እንጂ፤ በብሔር ዘር ቆጥሮ ከጋይንት፤ ወይም ከደንቢዶሎ፤ ወይም ከከሚሴ፤ ወይም ከሰመሃር፤ ወይም ከደብረብርሃን የመጣ አያስተዳድራቸዉም። ዓይናችሁን ጨፍኑ አና በጠራራ ፀሐይ እናሞኛችሁ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ክእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ላይሰራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስንብት ማድረግ ይኖርበታል። አንዱን በበር አባሮ ሌላኛዉን በመስኮት ማስገባት የአደባባዩን የኢትዮጵያዊነት ስብከት ያረክሰዋል። ኢትዮጵያዊነትን  አዘዉትሮ ከሚሰብክ የፖለቲካ ኃይልም አይጠበቅም። ኢትዮጵያ ሱስ ናት እያሉ በየአደባባዩ የሚነግሩን መሪዎቻችን ለምን አዲስ አበባ ጥያቄ ላይ አንደበታቸዉ ተዘጋ?  ለምን የማጣፊያዉ ቃል አጠራቸዉ? ለምን በእጅ አዙር  (በወኪል አክቲቪስቶች)  መልክት  ይተላልፍልናል? የተገኘዉን ለዉጥ እንደ ዓይን ብሌናችን እየተንከባከብን ያሉንን የቅሬታ ጥያቄዎች ደግሞ እንደ ዜጋ የመጠየቅ መብታችን መሆኑን ለአንዳፍታም መዘንጋት የለብንም። ለለዉጡ የጥንካሬ ምንጭ የሚሆነዉ ነጋ ጠባ መወድስ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም  የሚታዩ ሕጸጾችንም በወቅቱ እንዲስተካከሉ ለማድረግ መሄስ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑንም ተገንዝቦ በተግባርም ልንተረጉመዉ ስንችል መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል።

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የእኔ ነዉ የሚል እምነት የሚያድርበት ሕገ መንግሥት መቅረፅና በዚህ ሕግም ሁሉም እንዲዳኝበትና እንዲጠየቅበትም፤ እንዲያከበረዉም  የሚያደርግ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገዉ የለዉጥ ጉዞ ሃዲድ ለመጉዋዝ  መንደራችንን ሳይሆን ከፍ ብለን ኢትዮጵያን አሸጋግረን እንመልከት። ከሁሉም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚያደርጉዋቸዉ ንግግሮች  …ኢትዮጵያ አትፍርስም፤ እንደ ጭቃ ዝምብላ ተጠፍጥፋ የተሰራችም  ሸክላ አይደለችም …. በማለት አበክረዉ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህን የሚሉትም እንዲሁ ያለምክንያት አለመሆኑን መረዳት ብዙም ሳይንሳዊ ምርምር የሚያስፈልገዉ አይደለም። እንደ ሀገር መሪ የሚታያቸዉ ሥጋት አላቸዉ ማለት ነዉ። ከሀገር መኖር ባሻገር ሌላዉ አጃንዳ ሁሉ ኢትዮጵያዉያን ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር ባለመሆኑ ከሕፃን እስከ አረጋዊ፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በአብሮነት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከሚያደርግ ሀገራዊ ራዕይና ሕልም ውጭ የምናስቀድመዉ እንደሌለ የችግሮቻችንን ቀዳዳዎች ሁሉ መድፈን መቻል ይኖርብናል። ሸክላ ሲሰበር ገል ነዉ፤ ሹም ሲሻር ሕዝብ ነዉ የሚለዉ አባባል በሀገራችን በተግባር ተተርጉሞ እንድናየዉ የዘመኑ ገዥዎቻችን ሲሻሩ ሕዝብ እንጂ ሌባ ከመባል ድነዉ ልጆቻቸዉም፤ ቤተሰባቸዉም፤ ሀገርም እንትኮራባቸዉ የሚያደርግ ኀሊና ይስጣቸዉ።

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.