ሰበር ዜና፡- የአይኤስ ሽብር ድርጊትን ለማውገዝ የተጠራው ሠልፍ ላይ ፖሊስና ሠልፈኞች ተጋጩ

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በአሸባሪው የአይኤስ ቡድን አረመኔያዊ ድርጊት ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያውያን የግፍ ግድያ ለመቃወም በመስቀል አደባባይ በዛሬው ዕለት ታላቅ ሰላማዊ ሠልፍ ተካሄደ፡፡ በሠልፉ ማጠናቀቂያ ላይ ሠልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ሠልፍ ለመታደም ሕዝቡ ወደ መስቀል አደባባይ ያመራው ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡

በዕለቱ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በአይኤስ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡ በደረሰው መራር በሐዘን በእጅጉ የተነኩና እርማቸውን ለማውጣት ሠልፉ ላይ የተገኙ በርካቶች ነበሩ፡፡ መንግሥትን የሚቃወምና የሚደግፍ መፈክር ያነገቡ የተወሰኑ ሠልፈኞችም ነበሩ፡፡

በሠልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ እርሳቸው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት በሠልፈኞችና በፖሊስ መካከል ግጭት ተፈጥሮ የተወሰኑ ሠልፈኞች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እንደተጠናቀቀ የተወሰኑ ሠልፈኞች በሥፍራው በነበሩት የፌደራል ፖሊስ አድማ በታኝ ፖሊሶች ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሞዋአቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ አድማ በታኝ አባላትም አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ሠልፉን ለመበተን ሞክረዋል፡፡

በመሀሉም ጭሱን የሚሸሹ በርካቶች እርስ በእርስ ሲጋፉ የመረጋገጥ አደጋ ሲደርስባቸው፣ የአስለቃሽ ጭሱን ኃይል መቋቋም ያቃታቸው በርካቶችም አስፋልት ላይ ወድቀው ይታዩ ነበር፡፡ የተወሰኑት ሠልፈኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ውኃ ፊታቸው ላይ በማፍሰስ እንዲነቁ ለማድረግ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡

የወደቁትና መረጋገጥ የደረሰባቸውን ሠልፈኞች በአምቡላንስ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ፖሊስ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ተቃውሞ ያሰሙ ሠልፈኞችንም በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.