“አብሬው የታገልኩት ህወሃት ወደእስር ቤት ሲጥለኝ/ ሲወረውረኝ፣ አንድነት ፓርቲ ግን ተማር ብሎ ይኼው ወደውጪ (ዩኒቨርሲቲ) እየላከኝ ነው”

አቶ ስዬ አብርሃ በአንድ ወቅት የተናገሩት

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፤ አንዱ አመራር የነበሩትን አቶ ስዬ አብርሃን ወደውጪ ሃገር ለትምህርት ለመላክ በአዲስ ቪው ሆቴል የሽኝት ፕሮግራም አድርጎላቸው ነበር። በዚህ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ እኔ፣ ዘሪሁን ሙሉጌታ፣ ሪፓርተር ጋዜጣ ከሚዲያዎች ተጠርተን ሁነቱን ተከታትለናል።

ከሌሎች የፓርቲው አመራሮች ንግግር ቀጥሎ የመጨረሻ ንግግር አድርገው የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ነበሩ።…ከአቶ ስዬ ከንግግራቸው መካከል ይህቺን ጠንከር ባለ አገላለጽ መናገራቸው ይታወቃል። “አብሬው የታገልኩት ህወሃት ወደእስር ቤት ሲክትተኝ/ሲወረውረኝ፣ አንድነት ፓርቲ ግን ትምህርት ተማር ብሎ ወደውጪ (ዩኒቨርሲቲ) ይኼው እየላከኝ ነው። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።” በማለት ምስጋናቸውን ደጋግመው ገለጹ። አቶ ስዬ ትምህርታቸውን ቢጨርሱም ከተቃውሞ “ትግል” ርቀው ኖረዋል። ይኸው ዛሬ ደግሞ “አብሬው የታገልኩትና እስር ቤት የወረወረኝ” ያሉትን የህወሃት 44ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር በግልጽ በመቀሌ ተገኝተዋል። ጎዱኝ ሲሏቸው የከረሙትን የህወሃት አመራሮች ከልብ ይቅር ብለው ከሆነ [ከልብ ይቅር ባይነት ቀላል መሆኑ ሳይዘነጋ] መልካም። ነገር ግን ዛሬም ህወሃት በውስጣቸው ካለና ሊያግዙትም ከሆነ ዳርዳርታው ‘የከርሞ/የከረመ ፍቅር’ የሚለውን የሙዚቃ ዜማ እያስታወስን የሚሰሩትን በሂደት እናያለን።

ኤልያስ ገብሩ

1 COMMENT

  1. ውጭ ተማሩ አልተማሩ ወያኔዎች እይታቸው ከመንደርና ከጎጥ አያልፍም። በይፋ የሚለፉትና በስውር የሚፈጽሙት ደባ አይገናኝም። ሰው አፍነው ወስደው ከገደሉ በህዋላ በድኑ ተጥሎ ሲገኝና ቤተሰብ ቀብሮ ለሃዘን ሲቀመጥ አብረው የሚያላቅሱ ጉዶች ናቸው። በአንድ ወቅት አቶ ስዬ አብርሃ (ወንድማቸው በደርግና በወያኔ ዘመን ተሰቃይተው የሞቱ) እንዲህ ብለውን ነበር። “እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛ ይናገራል”. ያን ግፍ የፈጸመውና አሁንም በእጅ አዙር የሃገሪቱን ሰላም የሚያውከው ወጀብ መሰረቱ ከትግራይ ነው። ወንድምና እህትን ገድሎ እንደ ጀግንነት የሚፎከርበት ሃገር ኢትዪጵያ ብቻ ነው። ልብ ያለው እንደ አቶ ስየ እና እንደ አቶ ገብሩ አሥራት ያለው ወያኔ አሁን የትግራይን ህዝብ ለዳግም ጦርነት ሲያሰለጥንና ለጦርነት ሲያዘጋጅ ይህ አይበጅም ማለት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ የተካፈሉት ጽዋ አንድ በመሆኑ ዛሬም ክራር እየተከረከረለት፤ ከበሮ እየተመታለት ወንድምና እህቱን ለመግደል የጦር ዝግጅት ላይ እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግልጽ አቋም የለሹ ዶ/ር ደ/ጽዮንም አንድ ጊዜ ሲደመሩ ሌላ ጊዜ ሲቀነሱ ቆይተው አሁን የጦርነት አዋጅ ማወጃቸው አስገራሚ አይደለም። የሚያሳዝነው ግን እነዚህ አረሞች (የፕሮፌስር መስፍን ወ/ማሪያም) ቃል ልዋስና ዓለማዊውን የፓለቲካ አሰላለፍና እይታ የማይከተሉ በራሳቸው ታምቡር ብቻ የሚደንሱ ናቸው። አሁን ባለንበት ዓለም እንኳን የአንድ ሃገር የእርስ በርስ ጦርነት ቀርቶ ድንበር ዘሎ ከመጣ ጠላትም ጋር መቆራቆስ እንደ ኋላቀርነት ነው የሚታይ። ነገርን በክብ ጠረጴዛ ላይ መፍታት ነው ጎበዝ የሚያሰኘው። ሌላው ሽለላና ቀረርቶ ድንቁርና ነው። ከየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ይመንጭ ይህ ኑና ግጠሙኝ አተላ አስተሳሰብ ነው።
    በመሰረቱ የትግራይን ህዝብ ማንም አያጠቃውም። የውጭም ሆነ ሃገር በቀል ወራሪ ጭራሽ አይከጅልም። ግን ወያኔ ለራሱ የጊዜ መግዣ አሁንም የትግራይን ህዝብ በማስቀደም ለራሱ መደበቂያ ዋሻ ለማበጀት የሚጠቀምበት በእነ ስብሃት ነጋና መሰሎቹ የተገመደ የሴራ ገመድ ነው። ያለፈና የአሁን የዓለም ታሪክ ግን የተሞላው የተማሰው ጉድጓድ የከፋፋዮችና በህዝብ ስም የሚነግድ መቃብር መሆኑን ነው። ምሳሌ – የኡጋንዳው ኢዲአሚን ታንዛኒያን ሲወር የታንዛኒያ ምላሽ ካምፓላ ድረስ ይመጣል ብሎ አልገመተም። የሩማኒያው ኒኮላስ ቻስቻስኩ (Nicolae Ceaușescu) በመድረክ ላይ በሚደነፋበት ሰዓት ግርግር ሲነሳ ያቺ ቀን የመጨረሻው እንደሆነች አልገመተም። ከሩቅ ታሪክ የጣሊያኑ ሞሶሎኒ ሚላን ላይ አስከሬኑ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል የጀርመኑ ናዚ ዜናውን ሲሰማ አስከሬኑ በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅ ጥብቅ ትዕዛዝ በመስጠት ወድጁና እሱ ሞትን በጋራ ተጎነጩ። የጉረኞችና የጦር ናፋቂዎች ዜና እረፍት ይህን ነው የሚመስለው። ችግሩ መከራውና ሃበሳው ለንጽሃን ወገናችንም መትረፉ ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠላ፤ ዘረኛና አጥፊ የማፊያ ድርጅት እንደሆነ አለም ሁሉ ያውቃል። በማን ሃገር ነው በብዙ ሺ ቶን ቡና ከዋና ከተማው ከካዝና ተሰርቆ ዝም የሚባለው? ግን ቀበሮን የዶሮ ጫጩት ጠባቂ ያረጋት ያ መንግስት ተብዬ እንዳሻው የሚፈነጥዝባት ለ 27 ዓመት ሌላው ህዝብ ሃበሳ የቆጠረበት ዘመን ለወያኔ ደንታ አይሰጠውም። በራሱና ለራሱ የሚያስብ፤ ከጎጥና ከክልል አልፎ ለሌላው ወገን ጠቃሚ ሃሳብ ማፍለቅ በወያኔ ሃራም ነው። 44 አመት ባለህበት ሂድ! አታድርስ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.