የፌደራል ፖሊስ በአቶ ኢሳያስ ዳኛቸው ላይ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

የፌደራል ፖሊስ አቶ ኢሳያስ ዳኛቸው በዋስ ሊለቀቁ አይገባም በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ፡፡

በመሆኑም ከዚህ ቀደም በተወሰነው መሰረት በ50 ሺህ ብር ዋስና ከአገር እንዳይወጡ በተጣለ እገዳ በዋስ እንዲለቀቁ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን አፅንቷል፡፡

በህግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ 3 ወራትን የዘለሉት የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም የስራ ሃላፊ አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ ጉዳያቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ተፈቅዶላቸው ነበር።

ዋስትናውን የተቃወመው የፌዴራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ይግባኙን ውድቅ አድርጓል።

ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ ግለሰቡን በሌላ የሙስና ወንጀል ድርጊት ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል በአዲስ ምርመራ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ስለጠየቀባቸው በከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛው ወንጀል ችሎት የድርጊቱ ፍሬ ነገር ቀርቦ ነበር።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛው ወንጀል ችሎትም የተጠርጣሪ ጠበቆችና የአመልካችን ክርክር ካደመጠ በኋላ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲወጡ ውሳኔ ቢሰጥም በውሳኔው ቅር የተሰኘው መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ እንዳስረዳው ተጠርጣሪው በኢትዮ ቴሌኮም ‘ኤንጂፒኦ’ የተባለ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ያለውድድርና ጨረታ ‘ኢዲኤም’ የተባለ የውጭ አማካሪ ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም መጠርጠራቸውን ገልጿል።

ግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ፤ ከዚህ በፊት የተደረጉ ክርክሮችን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ባሳለፈው ውሳኔ የከፍተኛው ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል።

EBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.