‹‹አሁንም የታገቱ ሰዎች አሉ›› ብ/ጀኔራል አሳምነዉ ፅጌ(የአማራ ክልል የሠላምና የህዝብ ደህንነት ግንባታ ቢሮ ሃላፊ)

ቢቢሲ፦ ሰሞኑን በተለይ ከጎንደር መተማና ከጎንደር ሁመራ በሚወስዱት መንገዶች ላይ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከልክሏል። ከክልከላዉ በኋላም ግን እገታዎች እንደተፈጸሙ እየተነገረ ነዉ። እንዴት ይህን መከላከል አልተቻለም?
ብ/ጀኔራል አሳምነዉ፦ እነዚህ መንገዶች ዓለም አቀፍ መንገዶች ናቸዉ። እነኝህን መንገዶች በራሳችን ፍላጎት መከላከያ በበላይነት ብቻ ሳይሆን በወሳኝነት እንዲቆጣጠራቸው አድርገናል። ሌላውን ሥራ ደግሞ እኛ እንድንሰራ ተደረጓል። ይህም የተልዕኮ ግልጽነት እንዲኖርና በተልዕኮ ላይ አሻሚነትና አወዛጋቢነት እንዳይከሰት ነው።
ክልከላዉ የተካሄደውም አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ሰላማዊ ለማድረግና የሚፈጠሩ እገታዎችን ለመከላከል ታስቦ ነዉ። ይሁን እንጂ ይህ ችግር አልተቀረፈም። ሰሞኑን ሚኒባስ የያዙ ሹፌሮችና ረዳቶች ታግተዋል። ጭልጋ አካባቢም የተወሰነ ችግር ገጥሞናል። ይሄ የቆየና የሚጠበቅ ነዉ አዲስ ነገር አይደለም። መልሰን ለማስተካከል እየሰራን ነው። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የምንጠብቃቸው ችግሮች አሉ።
ቢቢሲ፦ የታገቱት ሰዎችስ የት እንደደረሱ ይታወቃል?
ብ/ጀኔራል አሳምነዉ፦ ይገኙበታን የተባሉበትን ቦታ መለየት ተችሏል። አንዳንዶቹን የመከላከያ ሠራዊት ደረሶ እርምጃ በመውሰድ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። አንዳንዶቹን ደግሞ ፍለጋና ክትትል ላይ ናቸው።

ቢቢሲ፦ በምዕራብ ጎንደር ያለው ችግር ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት አለዎት?
ብ/ጀኔራል አሳምነዉ፦ ጎንደር ለአስተዳደራዊ ሁኔታ ተብሎ የተከፈለ ስለሆነ አንድ ቦታ ላይ ያለዉ ስሜት ሌላ ቦታ ይነበባል። አንድ ቦታ ያለው መልካም ነገር ሌላ ቦታ መልካም ነገር ይዞ ይመጣል። ስለዚህ የአንዱ ተጽዕኖ ሌላው ጋ ሊኖር አይችልም ልንል አንችልም። በጋራ አንድ መስመር የሚጠቀሙ ናቸው።
ስለዚህ አንዱ ቦታ በተነሳዉ ግጭት ምክንያት ተንቀሳቅሰው መስራት ካልቻሉ ችግሩ ሌላም ቦታ ተጽዕኖ አሳድሯል ማለት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተጽዕኖው አይደለምና በሌላው አካባቢ፤ ችግሩ በተከሰተበት ስፍራም እየቀነሰ ስለሆነ ተጽዕኖው የለም ማለት ይቻላል። ህብረተሰቡም ከውድቀቱ እየተማረ ስለመጣ በራሱ ሰላሙን ለማስጠበቅ እየሰራ ነው። ነገር ግን አካባቢውን ማበጣበጥ የሚፈልጉ ኃይሎች አርፈዉ ይቀመጣሉ ብለን አናስብም።
ቢቢሲ፦ እነዚህ ኃይሎች ግን እነማን ናቸዉ?
ብ/ጀኔራል አሳምነዉ፦ እሱን ሌላ ጊዜ እንነጋገረዋለን። ግን ዞሮ ዞሮ ይሄ አካባቢ ድንበር ነው፤ ታውቀዋለህ አይደል? በአብዛኛው ሱዳን ጋር እንዋሰናለን ሌላም ጋር እንዋሰናለን። አንዳንድ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ ከታሪክም ከሌላም በለው እዚህ አካባቢ ችግር እንዲከሰት ያደርጋል።አንዳንድ አካባቢ ደግሞ ይሄ ህዝብ በርካታ ጥያቄዎች ኑረውት በተገቢው መንገድ እንዳያቀርብ ደግሞ አንቅፋት ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ። ይህን በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል ህዝቡ በራሱ መንገድ ይፈታዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.