መቀመጫቸውን ኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩት የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ትብብር/ትሕዴን/ መሪዎች አዲስ አበባ ገቡ

በትሕዴን ሊቀመንበር አቶ መኮንን ተስፋዬና በዋና ጸሃፊው አቶ ግደይ አሰፋ የተመራው የልኡካን ቡድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል ተቀብለውታል።

ትላንት ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2011 አዲስ አበባ የገቡት የትህዴን መሪዎች ላለፉት 17 አመታት ያህል የሕወሃት/ኢሕአዴግን መንግስት በመቃወም በትጥቅ ትግል ላይ መቆየታቸው ተመልክቷል።

ትህዴን ትጥቁን ፈቶ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የወሰነው በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ አበረታች በመሆኑ እንደሆነም አመልክቷል።

የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃላፊ በጄኔራል አደም መሃመድ ከተመራ የኢትዮጵያ መንግስት ልኡክ ጋር በነሐሴ ወር አስመራ ላይ ተወያይተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የመጀመሪያ ሊቀመንበር አቶ ፍስሃ ሃይለማርያም በሰው እጅ ሕይወታቸው ሲያልፍ 2ኛው ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ጥቂት ወታደሮች አስከትለው በ2007 አዲስ አመት ዋዜማ መክዳታቸው አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለም መቀመጫቸውን ኤርትራ አድርገው ትግል ከሚያካሂዱት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራ ልኡካን በተመሳሳይ የፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢሳት ዲሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.