በመቆጠር ተጠቃሚው ማነው? (ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር)

ዛሬ የካቲት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ቢሮየ ስገባ በማስታወቂያ ሠሌዳው ላይ ዓይኔ በማረፉ የፊታችን መጋቢት ወር መገባደጃ ስለሚካሄደው የኢትዮጵያ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ስለተዘጋጀ ሁሉም ሠራተኛ እንዲገኝ የሚል ማሳሰቢያ አዘል ማስታወቂያ አነበብኩ፡፡

ከዚያም ወደ ቢሮየ አቅንቼ ማስታወሻ ብጤ ይዤ ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ አዘገምኩ፡፡ በአዳራሹ ዙሪያ ብዙም ሰው እንደሌለ በማየቴ የእጅ ሰዓቴን ተመለከትኩ ከጠዋቱ 2፡45 ሰዓት ይላል፡፡ የእኛን አገር ቀጠሮ በእዝነ ልቦናየ በማብሰልሰል የአዳራሹን በር ተደግፌ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡

ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ በየቢሮው በተደረገው ቅስቀሳ ሠራተኛው ወደ አዳራሹ መዝለቅ ጀመረ፡፡ ሁላችንም ቦታ ቦታችን ያዝን፡፡ ከአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ወክላ በመጣች ባለሙያ ስለ 4ኛው አገራዊ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የቀረበውን ሰነድ ለግንዛቤ ባይሆንም በንባብ ተወጣችው፡፡ እኔም የጠላዋ መኮምጠጥ፣ የእንጀራዋ ጆሮ መሳብና የወጧ መጎርነር ማኅበርተኞቿን አንገት ያስደፋ ሙያዋን ሳታናንቅ አረረም መረረም ማኅበሬን ተወጣሁት ያለችውን ባለጥዋ አስታወሰኝ፡፡

የማከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቆጠራውን በበላይነት እንዲመራ በአዋጅ ቢቋቋምም እንዳለመታደል ሆኖ ከመንግስት ተጽእኖና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ሥራውን በትክክል የሠራበትን ጊዜ ግን ትዝ ኣይለኝም። ለዚህ ደግሞ በግንቦት ወር 1999 ዓ.ም የተካሄደው 3ኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እማኝ ነው፡፡

እኔን እጅጉኑ ያስገረመኝና የተረዳሁት  የማከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሚወክል አካል በሌለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱ ብቻ ሳይሆን ለተነሱት ጥያቄዎች ቆጠራውን መሠረት ያደረገ ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመኖሩና የአገሪቱ ሆነ የክልሉ መንግስት እንዲሁም ኤጀንሲው ለቆጠራው ተገቢውን ትኩረት እንዳላሰጡት ነው፡፡

የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ጠቀሜታና አስፈላጊነት ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱም ሆነ በክልሉ ያለው የፖለቲካ ድባብ ቆጠራውን ለማከናወን የሚያስችል እንዳልሆነ መገመት የተለየ አዋቂ ሰው መሆን አያስፈልግም፡፡ እንደኔ አይነቱም ሰው ይህንን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ታዲያ የፖለቲካው ሁኔታና የጸጥታ ሁኔታው ለቆጥራ ፍጹም ነው በማይባልበት ጊዜ፤ እንዲያውም የሃገሪቱ አለመረጋጋት ከፖለቲካው ጋር ቁርኝቱ ከፍ ባለበት ሁኔታና ጽንፈኝነት በነገሰበት በዚህ በአሁኑ ሰአት ቆጠራውን እንዴት በትክክል ማስኬድ ይቻላል? የኔ ጥያቄ ነው፡፡

ለማስረጃ ያህል በአማራ ክልል በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ያለው ሁኔታ እንኳን አገራዊ ተግባር ለማከናወን ይቅርና የዕለት ተዕለት ተግባር ማከናወን አይቻልም፡፡ ከ90 ሺህ ሕዝብ በላይ ከቤት ንብረቱ በተፈናቀለበት፣ የክልሉ የአስተዳደር ወሰን በውል ባልታወቀበትና የማንነት ጥያቄ ምላሽ ባለገኘበት ወቅት ትክክለኛ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ይካሄዳል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡

የህዝብ ቆጠራው አካሄድና ውጤትም ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ታዲያ አሁን ክልሉ ያለበት ሁኔታ የፀጥታና አልፎ አልፎ አለመረጋጋት ችግር እንዳለ እየታወቀ ያውም የአንድ ወር ዕድሜ ለቀረው ቆጠራ አመቺ ይሆናል ተብሎ ይገመታል? በርግጥ ትክክለኛ የህዝብ ቆጠራ ጸጥታና መረጋጋት ስልሚፈልግ እንዴት ይህንን መንግስት ማየት እንዳልቻለ ለኔ ግልጽ አይደለም። ቆጥራው የሚከናወነው በታችኛው የመንግስት መዋቅር ማለትም በወረዳና በቀበሌ በመሆኑ የቆጠራው ትክክለኛነት አጠያያቂ ነው፡፡

ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ማወቅ ብዙ አዎንታዊ ፋይዳዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። መንግስት ወቅታዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፕላን ለማዘጋጀት የህዝቡን ቁጥር በብሄራዊና በክልል ደረጃ ብሎም ወረድ ባሉ የአስተዳደር ደረጃዎች ማወቅ ቢችል ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም። እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የዓለም ህዝብ አካል እንደመሆኑ ሁሉ ቆጠራው የዓለም ህዝብን በትክክል ለመቁጠር አንድ እርምጃ ተደርጎ ሊገመት ይችላል። ለኤጀንሲው ደግሞ ወደፊት ሌላ የህዝብ ቆጠራ እስከሚካሄድ ድረስ አመታዊ የህዝብን ግምታዊ ቁጥር ለመተንበይ (population projection) እና ለሌሎች የኤጀንሲው ቀጣይ ጥናቶች ናሙናዊ ማእቀፍ (sampling frame) ለማዘጋጀት ዋናው ቁልፍ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የሕዝብ ቆጠራን በትክክል ወይም ባልተጋነነ ስህተት መካሄድ እንዳለበት ይታመናል፡፡ ህዝብ ቆጠራ የሚከናወነው በየቆጠራው የካርታ ሥራ ላይ ነው፡፡ ቆጠራውን ያለምንም እንከን ለመፈጸም የቆጠራ ጣቢያዎች ፀጥታና የቆጣሪዎች ደህነነትም ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በጸጥታ ኃይሎች እገዛ ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ ቆጠራ ለመረጃ ብክነት ከመጋለጥም ባሻገር ሰዎች በሚሰጡት መረጃ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ከወዲሁ መገመት ተገቢ ነው። ስለዚህ በወረዳና በቀበሌ አመራር እጀባ የሚካሄድ የቆጠራ ውጤት ላይ ጥያቄ እንደሚጋብዝ ቢታወቅም ከመደበኛ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ውጪ በመሆኑም የመረጃ ጥራት ጉድለት ሊኖረው ይችላል ብየ አስባለሁ።

ታዲያ አሁን ባለው ሁኔታ ይኼ ጉዳይ ፍጹም ሆኖ ሊከናወን ይችላል ወይ? በየቤቱ እየዞረ ቆጠራውን የሚያከናውነው ባለሙያ በቆጠራ መመሪያው መሰረት መስራት ቢፈልግስ ምን ያህል ይሳካለታል? በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ለቆጣሪዎች የተመቻቸ፣ በየአካባቢው የፖለቲካ ተጽእኖ የማይታይበት፣ የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲም የቆጠራ ተልኮውን ያለ እኔ አውቅልሃለሁ የፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ይፈጸማል ብየ አልገምትም፡፡

ስለዚህ የዘንድሮው የቆጠራው መሪ ቃል በመቆጠሬ ተጠቃሚ ነኝ የሚለውን ብሂል ለማሳካት ጊዜውና የአገሪቱ ሁኔታ ስለማይፈቅድ በርካታ ሃብት አፍስሶ ተገቢውን ግንዛቤ አስጨብጦ ቆጠራው ዘግይቶም ቢሆን በትክክለኛ ውጤት ማጠናቀቁ ይሻላል እንጂ በዚህ ሁኔታ በመቆጠሩ የሚጠቀም ሕዝብ ሳይሆን የሚጠቀም ብሔር፣ ብሔረሰብና ፖለቲከኛ ይኖራል ብዬ አስባለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.