የሰማዩ የሥራ ማቆም ሰላማዊ እንቢተኝነት – ምርጥ ዘርና ፍሬ (ሥርጉተ ሥላሴ)

17.05.2014
ከሥርጉተ ሥላሴ  (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ)

 

ፍቅር የተጠረገ ልብን አብዝቶ ይሻል! ሩብ አመት ሆነው የጀግና ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን ሰማይ ዘለቁ የሥራ ማቆም ሰላማዊ እንቢተኝነት ምርጥ ዘርና ፍሬን ዓይናችን በዕውን ከተመለከተ። መንፈሳችን አዲሱን መንገድ ማደነቅና ማክበር ከጀመረ እንሆ ዘጠና ቀናት ሆነው። ወገኖቼ የሥራ ማቆም „አድማ“ አላልኩም። ያላልኩበት ምክንያት „አድማ“ ሁለትና ከዛ በላይ ያሉ ሰዎች በተስማሙበት መንፈስ ውስጥ – አኃቲ አቋም ይዘው ለአጭር ወይንም ለረጅም ጊዜ የአመጽ ወይንም ዬአልገዛምባይነት ናዳ በተቀናቃኛቸው ላይ የሚለቁበት ነው። ናዳው የመንፈስ ወይንም የሌላ ሊሆንም ይችላል። „አድመኞቹ“ በናቸው መንገድ ቁጣቸውን፤ መከፋታቸውን፣ ብሶታቸውን ይገልፃሉ። „አድማውም“ አዎንታዊ ነው፤ ነፃነትን ያህል ክቡር ነገር ከአንባገነን እጅ ፈልቅቆ ለማስወጣት ስለሆነ፤ ቅዱስም ነው ዕንባን ስለሚታደግ። ብሥራትም ነው ጢስ የለበሰውን ባዕት  አድርጎ ተስፋን ስለሚያጎናጽፍ።

 

ጀግናዬ ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን ግን ብቻውን ነው ሰማይ ላይ የዞግ ፖለቲካ ዬበዬነበትን የ2ኛ ማዕረግ ደረጃ ረገጥ አድርጎ፤ ለጣሊያ የተሰጠው ቦታ የሚመጥን ብቃት እናት ሀገር ኢትዮጵያ ልጆቿ አላቸው በማለት ኮሶውን እያባበለ ጋት ያደረገው – ለወያኔ። እግረ – መንገዱንም በአፈና ለጥ – ሰጥ በሎ መገዛት፤ አቤት ወዴት ብሎ መረገጥ፤ ጆሮዋችን ይዘን ቁጭ ብድግ ብሎ ማረግረግ አለመደብን በማለት የተነፋውን የወያኔ ትእቢትንም እያዋዛ ነደል አድርጎ ቀፎ እስኪቀር ድረስ አስተነፈሰው።

በሌላ በኩል በአጥር ቅጥር የተከለለው የአፓርታይድ ነፃ መሬት ላይ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ባይቻልም ሰማይ ላይ ግን የሥራ ማቆም ሰላማዊ እንቢተኝነቱ በድል ተንቆጥቁጦ ለማዬት ግድ ይላችኋል ሲል በነጠረ ትርጉም መልእክቱን አስተላለፈ – ለወያኔ። ከዛም ቀጣዩ የተግባር ቀጠናችሁን በሚመለከትም ደግሞ አለና ጀግና አበራ ሃይለመድህን „መሬት ላይ መጥታችሁ እያፈረሳችሁት ያለውን ብቸኛውን የኢትዮጵያዊነት ተቋም ንብረት መውሰድ ትችላላችሁ፤ ግልማጫችሁን ሆነ የለመደባችሁን እርግጫችሁን ግን ከዚያው ተወት አድርጋችሁ መምጣት ግድ ይላችኋል“  በማለት ፈቃዱን ሰጠ። ይህም ድምጽ የለሽ ቅጣት – መጠኑን አልፎ እጅግ ለተቀናጣው ወያኔ – ሊሸከመው ያልቻለው ውርዴት በመሆኑ ነው ሲያወራው የከረመው። ሃይልዬ የወሰደው ፈጣን እርምጃ በነፍጥ ለተመማነ የዞግ አስተዳደር ህሊናን እንዳሻው አጋድሞ የሚቀጠቅጥ የተሳለ፣ ጥቃትን ያወጣ ገጀሞ ነው።  የረዳት አውሮፕላን አብራሪ አበራ ሃይለመድህን ድፍረትን የሰነቀው ክንውን – እህ! እያሉ መኖር እንዲህ መር ስለመሆኑ፤ የማይቻለውን ሁሉ ችሎ „እንቢታን“ ተግባር ማስታጠቅ የሚያስችል መሆኑን ያመላከተ ታላቅ የትውልድ ተቋም ነው። ይህ ለወያኔ ብቻ ሳይሆን ለነገም በለስ ለሚቀናው ኢትዮጵያዊ  አስተዳደር በቋሚነት የሚያስተምር ወግ ያለው – የድርሻ፣ ነፍስ ያለው – የአርበኝነት ናሙና ነው።  የገዘፈ ተልዕኮ በስኬት ለምቶ እንዲህ ተከወነ።

ጀግናዬን ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን በሚመለከት በሸኘነው ሰሞናት በ09.05.2014 ቴሌ ሲወዝ ቲቪ ትንሽዬ መረጃ ሰጥቶ ነበር። የጥንቃቄያቸው ጥራት እንደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደራቸው የሆነው የሲወዝ ሚዲያ መንፈስ አዲስ ፎቶ እንኳን አልነበረውም፤ በፌስ ቡክ በተገኘው ፎቶ ላይ አይኑ ተከትሮ እጅግ ደረጃውን ባደመጠ ጥበቃ ነበር ዜናው የቀረበው። የዜናው ጭብጥ ከህግ አንፃር ሊታዩ የሚገባቸው ሂደቶች ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እንደሚጀምር ነበር የተገለጸው። ይህ እኛም የምንጠበቀው ሲሆን፤ በጠበቆች በኩል ያለው የአያያዝ ጥበብ ደግሞ ተስፋን የሚያለምልም ሆኖ አግኝቸዋለሁ – እኔ በግሌ። ብሊክ ሹክ እንዳለው ከሆነ እስከ 20 ዓመት የሚለውን የነዘለቦ ጥንዝል ተስፋ ጠበቆቹ አንዝግዝገው ፈርጅ ያለው አምክንዮ ጠቁመዋል።

ሲዊዘርላንድ እራሷ ህግ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ ዴሞክራሲ ባህሏ መሆኑ የመብትና ዬግዴታው ጣረያና ግድግዳ ሳይጣስ፤ ተጓዳኝ አህጉራዊ – ዓለምአቀፋዊ ሆነ ብሄራዊ ህጎች ተጣጥመው ተስፋን የሚቀልብ ውሳኔ ይኖራል የሚል እጅግ አዎንታዊ የመንፈስ ፅንስ ነው ያለኝ እኔ በግሌ። ህገ – መንግሥታቸው አይደለም አባታችን በአምሳሉ ለፈጠረው ለታላቁ ፍጡር ለሰው ልጅ ለእንሰሳት፤ ለዱሩ፤ ለተራራው፤ ለወንዞች ሳይቀር ደህንነታቸውን የሚጠበቅ ድንጋጌዎች አሉት፤ ዘለግ አድርጋችሁ ስታዩት የህጎች ሁሉ እናት የሆነው ህገ – መንግሥታቸውን የኖህ መርከብ ሚስጥርን ያነበበ – የተረጎመ -ያመሳጠረ ነው። ብሄራዊ መዝሙራቸው እራሱ ጥልቅ የሆነ፣ ቅዱስ መንፈስ የረበበት ቃለ ወንጌል ነው። ስለሆነም በጣም መራር ነገር፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ፤ የዕንቡጥን የወደፊት የመኖር ህልም የሚያቀጭጭ ወይንም የሚያቆረፍድ ውሳኔ ይኖራል ብዬም አላስብም። ትልቁና ዋነኛው የሁላችንም ጭንቀት በበላህሰብ እጅ አለመግባቱ ስለነበር፤ ከበቂ በላይ ለመንፈስ ጥግ የሚሰጥ እርምጃ ነው የሲዊዝ መንግሥት ህገ – ውሳኔ ለወያኔ የሰጠው።

ያው ሲዊዞች የማድነቅ ባህላቸው ለራሳቸውም ዜጎች በቀስታ ስለሆነ ነው እንጂ፤ የወጣቱን ከዕድሜው በላይ ያደረገው  የሰብዕዊነት ተፈጥሮ፤ የጸጋው ሁለገብነት – ርቅነት፤ በቆዬባቸው ጊዜያታት ለክተው ባዩት ተጨባጭ ሞራላዊ ሆነ ሥነ  – ምግባራዊ ብቃት አክብሮትም ፍቅርም በልባችው ውስጥ ለጀግና አበራ ሃይለመድህን ጎጆዋን በህሊናቸው እንደሚቀልስም እገምታለሁ። አሳዳጊውን የሚያስከብር እሸት ነውና። ዓይኑ ውስጥ ነፃነትን የሻተ ሰላም ፈላጊነት በቀላሉ ማዬትም ይችላሉና። እኛ እንኳን ፎቶውን ትክ ብለን ስናዬው የሚነግረን ብዙ ነገር አለው።

የሰው ልጅ ግራ ቀኙን አይቶ፣ በውስጡ በተመስጦ እሱኑ የሚጠበቀውን ፍላጎቱንም ሳያውክ፣ በሌላው መኖርን ለሚፈልግ 202 ፍጡራንም ላይም እንግልትና የሞት ፍርድ ሳይበይን፣ እጅግ በሚደንቅ ጥንቃቄ፤ እንዲህ በዚህ ከእሳት ከውሃ በሚባልበት አፍላ ዕድሜ ላይ ሙሉ ሰው ሆኖ – ባለ ግረጫ ፀጉር ሆኖ – ሽበትን በውስጥ መስጥሮ ተልዕኮውን መፈጸም ለተሰጣቸው ብቻ ዬገድል ፏፏቴ የመቅዳት ያህል ነው። ስለሆነም ዳኞቹም ሆኑ ህጉ በራሱ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት የቀንበጥ አበባ እንዳይረግፍ ጥንቃቄ ያደርጉለታል ብዬ እገምታለሁ። እስከ አሁን ባላው አጠቃላይ ሁኔታ እኔ እረክቻለሁ። መከደኑ በእራሱ ለእኔ በመንፈሳዊ ሁኔታዎች ላይ የሚኖረው ትርፍ ዝቀሽ ነው እላለሁ። ዜናው እራሱ ክውን ሽክፍ ክሽን ያለ ነበረና። ሰከን ብሎ፣ ተረጋጋቶ  እንዲህ የሚሄድ ነገር ከብዙ አደጋ የሚታደግ ይሆናል። አይደለም ውሳኔው፤ ሂደቱ እራሱ ….. መምህር – አጽናኝም ነው። እርግጥ ግንኙነት ያለው ሥጋዊ ቤተሰብ ሁሉ የፍላጎቱን ውስጥ በቂ ጥበቃ እንዲያደርጉለት እግረ መንገዴን ማሳሰብ እሻለሁ – በአጽህኖት። ትግሉ የእርስ በእርስ ስለሆነ በዬማዕዘኑ ያሉ ሁነቶች መፈት የለባቸውም። ክድን!

በሌላ በኩል ያው  የክብሬ ጉዳይ ባላበት ሁሉ ጎርጎር እያደረኩኝ መታደም መደበኛ ሥራዬ ስለሆነ፤ አንድ  በእንግሊዘኛ የተጻፈ ዜናም አነበብኩኝ፤ መንፈሱ ያው ከጉዳዩ ባዕት ላይ የተከወነ ስለመሆኑም ገመትኩኝ።  „ሃይጃክ“ የሚለው ቃል በሥሙ ለተከፈተ ፌስ ቡክ ፈጽሞ የተገባ አይደለም። የውጭ ሚዲያው ሆነ ወያኔ ይህን ቃል ደፍሮ እንዲህ ይጠቀምበት – የክሱ አናት አድርጎ ስለያዘው፤ ሌላም መግቢያ ቀዳዳ ስለሌለው፤ ለእኛ ግን ወደ አውነቱ ውስጥ ጠልቆ መግባትን ይጠይቃል። የእርምጃውን መሰረተ ደምና አጥንት አጥንቶ ማግኘት ያስፈልጋል – የድርጊቱን ትንፋሻዊ ኮንፓስ መሰረት በያዘ አስተውሎ በብልህነት መቃኘት ይሻል። ይህን ለማግኘት ዕንባ ቢጠዬቅ ይምለሰዋል። በአራገረገ አልጋ ላይ ከተሆነ አይታይም። ነገር ግን የምልዐቱ ዕንባው እራሱ፤ ቀጥ ብሎ እራሱን በቻለ ፍላጎት ውስጥ ኑሮውን ስለከተመ ህመሙ ከቅርብ ነው። ይጠዘጥዛል።

ጀግናዬ አቅጣጫ ነው የቀዬረው። ይህም ከአጥጋቢ በላይ ምክንያታዊ ነው። መነሻ ቁስል አለው – መግል የሚያዝንብ። ስለሆነም ተግባሩ በእንቢተኝነት፤ በአልገዛምባይነት፤ በበቃ ሰላማዊ ጉዞ ሊሆን የተገባው መንገድ ነው። ግፍን ላልተቀበለ ወጣት በሚመቸው ቦታና በተመቸው ሁኔታ ተቃውሞውን መግለጽ ነበረበት። ሃይላችን – ሥራውን በፈቃዱ ለቋዋል። የሥራ ማቆም አንቢተኝነቱን ሰማይ ላይ በአደባባይ አሳይቷል። የወያኔን ማሃያም አልሻም ብሎ ደምድሟል –  በአፍንጫዬ ይውጣ ብሏል። በዞግ በበከተ አመራርም ምን ሲባል ተቀጣሪነት? እንዴትስ ታስቦ? ብሏል – ወንዱ። ተግባሩ እጅግ ሞደርን ነው፤ አፈጻጸሙ ደግሞ ጥበባዊ – ትዕይነት። በፍላጎቱ ውስጥ የበቀለው ዋርካ ምኞቱ ለሰብዕዊ መብት ተሟጋችነቱን አንጥሮ ውስጡን እንድናይበት አድርጎናል። ሃይሌ ስለሰው ልጅ ይጨነቃል፤ ይጠበባል። ስለሆነም „ሃይጃክ“ ይህን እኛ እራሳችን ስንጽፈው፤ ስንናገረው፤ እውቅና ስንሰጠው በሥሙ በተከፈተ ፌስ ቡክ ላይ ሳናርም እንደ ወረደ ስንለጥፈው ምን ለማለት እንደሆን አንባቢ ይፍረደው፤ ለነገሩ የጸሐፊው ሥምም የለውም፤ ማን ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችልም አላውቅም። ያው ይህ የሲዊዝ የተለመደ ቲያትር ነው። ዝንቅ ፍላጎት ራዕይን ወደ ዳጥ ይልካል። ጥርት ያለ ፍላጎት ግን አቅምን ዙፋን ላይ ያስቀምጣል – ውጤቱም ዝቀሽ ነው – ማሸነፍም ነው። ጥሩ እንጂ ጉሽ ጠላ ዋንጫውም አንኮላውም አያስተናግዱትም እንኳንስ የሰው ልጅ ጉሮሮ ….

 

ታሪክ ትውልድ ነው፤ ታሪክ ህዝብ ነው፤ ታሪክ ሀገር ነው። ታሪክ ሰንደቅዓላማ ነው። ታሪክ እራሱ ነገ ነው። ታሪክ መኖር ነው። „ታሪክ የህይወት ነው“ ታሪኩ ደግሞ የተገፉ፣ በክፉ አይን የሚገረፉት ዬኢትዮጵያ አዬር መንገድ ሠራተኞች ታሪክ ነው። ታሪኩ ዬታላቁ ኢትዮጵያዊው ተቋም የአዬር መንገዱ አንጡራ ታሪክ ነው። ታሪኩ ግፍና በደል በቃ!  የምልዕት ፍላጎትን የመሰጠረ የመንፈስ ህሊና ታሪክ ነው። ታሪኩ የልብ ዕንባ ታሪክ ነው። ታሪኩ የትናንት አርበኞቻችን የአደራ ውል በ21ኛው ምዕተ – አመት በድርጊት ሰማይ ላይ ያረገበት አጥናፈ ወርቅ ታሪክ ነው። ታሪኩ የህልማችን – የራዕያችን – የፍላጎታችን የብሩክ ማግሥት ታሪክ ነው። ታሪኩ በዬዘመኑ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፊት ለፊት እዬወጡ የተቃጠሉበት፤ የነደዱበት፤ የከሰሉበት፤ ወጣትነታቸውን ለዴሞክራሲ ሰውተው ያቀለሙበት ውርሰ – ወጣት ታሪክ ነው።  ይህን መጋፋት የተገባ አይደለም። የጹሑፍን ቀና መንፈስ እንዲሁም ኃያልና ጭብጥ አዘል ጉዳዮችን እርእሱ ይዳፈረዋል; ። „ጠለፋ“ አይደለም ብለን ሽንጣችን ገትረን በፋክት ላይ መሟገት ሲገባን፤ እኛም ይሄውን ካጸድቅን ምን አዎንታዊ ውሳኔ ከሲዊዝ መንግሥት ሆነ ስለ ዴሞክራሲ  – ስለ ሰብዕዊ መብት ያገባናል የሚሉ የአለም ዜጎች ሁሉ ጫና እንዲፈጥሩ ፊርማ ማሰባሰባችን ሆነ፤ ባለን የግልና የማህበራዊ ግንኙት የምንችላትን ለማድረግ መትጋታችን አስፈላጊ ላይሆን ነው። የፍላጎትን ህግ መተላላፍ ችግሩ ይህው ነው።

እንደሚታወቀው ጄኒራል ጉጉል ወዲያው ነው ፖስት የሚያደርገው፤ ሶልዳሪቲ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች፤ ድርጅቶች ሁሉም  በእንግሊዘኛ ስለሆነ ያነቡታል፤ በጎንዮሽ ጉዳዩን የሚከታተሉት ሆነ ጠበቆች እንዲሁም ቀጣዩን ሂደት ለመጀመር መሰናዶውን ያጠናቀቀው የሲዊዝ መንግሥታዊ አካላትም ያነቡታል። ሙግቱ እኮ ከሠለጠነው የሲዊዝ መንግሥት ህግ፤ ሙስና ድርሽ ከማይልበት ሙያዊ ሥነምግባሩን ካሟላ ጠበቃ፤ የዳኝነት ውሎ፤ ከጠንቃቃው ዬፍርድ አደባባይ ጋር ነው። እያንዳንዷ መረጃ ብትን ብላ – ተዘርዝራ ነው ለውሳኔ የሚበቃው – ጥንቃቄ በጎደለን ቁጥር ድላችን ይሸበሸባል —- ናፍቆታችንም አንገቱን ይደፋል።

 

እውነት ለመናገር የካፒቴን አበራ ሃይለመድህን የክብርት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ የህዝብአለም ስዩም በተደራራቢ ችግር፣ መከራ፣ ድንጋጤ ላይ ሆነው በድንገት ለቀረባላቸው ጥያቄ  የሰጡትን ቃለ ምልልስ እስኪ ያገባናል፤ ጉዳዩ ይመለከተናል፤ ባለቤቱ እኛ ነን የምንል ወገኖች፤ እንዲሁም  ቤተሰቦቹንም ጨምሮ በእርጋታ  ደጋግመን ለማድመጥ እንሞክር፤ የአትላንታው ንቁ ጋዜጠኛ ወንድሜ ዳዊትም በአማርኛ ቃል በቃል በፍጥነት ጽፎታል እስኪ ይነበብ።

የክብርት ወ/ሮ የህዝብአለም ስዩም የሰጡት መልስ በተለያዬ ሁኔታ ተዝረክርኮ የነበረውን መረጃ አማክለው፣ ከውነው፣ በሰለጠነ ሁኔታ ጭብጡን በጭብጥ አሰከኑት – አደራጁት – መሩት። ከዛ ቃለ ምልልስ ውስጥ ኬጂቢ፤ ሲአይኤ ወይንስ ሞሳድ የትኞቹ የሰለጠኑት፣ በዝቀሽ ተመክሮ የበሰሉት የሥለላ ድርጅቶች ምን ያገኛሉ? ምንም ….. የጥራቱ – የጥንቃቄው – የድፍረቱ – በራስ የመተማመን ብቃቱ – የሃቅ አመንጭነቱ – የሁሉንም አካልን ፍላጎት ሚዛን ጠባቂነቱ – እናታዊ ሥነምግባሩን አክሎ ምን እንዲያው – ምን እንከን ይወጣለታል? እግረ መንገዱንም የሴቶችን ብቃት አውጇል።

 

ወገኖቼ –  የዚህ ቀንበጥ ወጣት ታሪክ በዚህ መልክ እዬተገነባ፤ መሰረት እዬያዘ፤ በተገቢው ሙቀትና ዬአዬር ጠባይ ተኮትኩቶ እንዲያድግ ማስተዋልን አብዝቶ ይማጸናል – ይጠይቃል። የልጅነት ህልሙን፤  የምህንድስና ሙያውን አቋርጦ፣ ዕድሜውን ተሻምቶ ሰልጥኖ ያገኘውን ወርቅ ጥረቱን እኮ ነው ካለ ይግባኝ የፈረደበት፤ በሀገሩ፣ በመሬቱ፤ በቀዩ ተመርቆ ተወዶ ባደገበት በባዕቱ „ወንድሜ ብር ይዞ መጣ ሲበር፣ ሙሽራዬ ሙሽራዬ ዬወይን አባባዬ“ የሚባልለትን የቤተሰብ – ጉጉት አንገት አስደፍቶ እኮ ነው የቀለጠው፤ ይህ ወጣት በዚህ ብቃቱ ሌላ ሀገር ሄዶ ተቀጥሮ ቢሆን ኖሮ፤ አይደለም ዋና አብራሪነት የመምህርነት ብቁነትን የከፍተኛ ሙያ የአይነታነት ደረጃ የማግኘት ቀጣይ ዕድሉን እኮ ነው ኩምትርትር ያደረገው፤ ታሪኩ በግልብ ፈረስ መጪ የሚባልበት ፈጽሞ አይደለም። ቢያንስ ለታሪኩ እኛ የነፃነት ቤተሰቦች ስስታም መሆን እንዴት ይሳነናል? ፍቅራችን፤ አክብሮታችን ትጋታችን ሁሉ ስለምን አፈር እንዲቅም እንወስንበታለን? „ሃይጃክ“ ለጠቆረው ዘመን ዕንባ  ከአጠገቡ ድርሽ ሊል የማይገባው ቀፋፊ ቃል ነው። አዝናለሁ። ደግሞ እኮ እርእሱ ላይ ነው „ሃይጃክ“ የሚለው። http://www.freeabera.com/archives/614

 

ክወና …. የጀግናዬ አበራ ሃይለመድህ ድርጊት ምርጥ ዘርም ነው – ፍሬም ነው። አንድ ምርጥ ዘር ሲዘራ ቡቃያው እራሱ ዘንጣፋ – ሎጋ ነው – ሸበላ፤ ፍሬውም ዝቀሽ ነው ዘመን አሻጋሪ፤ – የራህብ ደራሽ ነው እናት፤ – አቅም አራሽ ነው ጎን፤ -ኃይል አምንጪ ነው ብርታት፤ – ጉልበት ሰጪ ነው ማሸነፍ፤ – ነፍስ አንባች ነው የመንፈስ ሃብት፤ – ህሊና አብሪ ነው – ጠሐይ። ጥምር ውጤት ከጥምር ጥረት ጋር በፍቅር በጥንድነት ያቀለመ፤ ነገን ያለመ፤ ዛሬን ያደመጠ የህዝብ ሃብተ – ታሪክ ነው የሠራው – ጀግናችን። ይህ ወጣት ሁሉንም የሰጠ፤ – ሁሉንም መሆን ያቻለ፤ ሁሉንም መከራ ለመቀበል የቆረጠ አርበኛ – የተመረጠ – ንቁ  – የበቃ – ወጣት ነው።

በመጨረሻ ለአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ የህግ ባለሙያ እጅግ የላቀ የክብር ምስጋና ዝቅ ብዬ አቀርባለሁ። እውነትን እንዲህ ማዬት። ስቃዩ እንዴት ቢያንሰፈስፋቸው ነው ዶር/ ሼክስፔር ፈይሳ ሲዊዝ – ጄኔባ ድረስ መጥተው ጉዳዩን ለማጥናት የቆረጡት። አብነትነቱ ትንግርት ነው። የነጠረ – ተግባርነት፤ – የፍቅር መለዮ እሩህሩሃዊ እናትንት፤ – ፍጹም ክንድ የጋሻነት፤ – አለሁነት የልባዊነትና የሙያ ሥነ -ምግባር፤ እግዚአብሄር ሁሉንም የልብዎትን ይሙላለዎት። እኔስ ኮረሁበዎት – የተመስገኑ ምርጥ ወንድም! ይኑሩልን! http://ecadforum.com/Amharic/archives/12279/

 

የእኔዎቹ ውዶቼ ዛሬ የጀግናችን የሩብ ዓመት የድንቅነት ማዕልት ስለሆነ – እንደቻልነው አድርገን እናክብረው፤ ያው ፌስ ቡክ ቲተር ሎጊን የምትጠቀሙ ወገኖቼም የጀግናን ፎቶ መንበራችሁ ላይ አድርጋችሁ ፍቅራችሁን ቀልቡት፤ አቅም ያላችሁ፣ ህይወቱ ያላችሁ የእምነት አቮውና እማዎችም ደግሞ በጸሎታችሁ ልጃችሁን እስቡት – ትእዛዝ አይደለም ለማስታወስ ….. በተረፈ የእኔ ውብ አድማጮቼ መመስገን ሲያንሳችሁ፣ መከበርም ሲያንሳችሁ ስለሆነ የማህሏን ለማንም ፈቃድ ተስጥታ የማታውቀውን የምሳሳላትን ልቤን ወስዱ …. እወዳችኋለሁ! ያው እንደተለመደው የሩብ አመቱ የጀግና ዝግጅት በልዩ ቅንብር ግንቦት 22.05.2014 ከ15 እስክ 16 ሰዓት ዕለተ ሃሙስ www.tsegaye.ethio.info Aktuell Radio Lora Sendung www.lora.ch.tsegaye ቃተኛ ይሻላል ቦዘና? ብቻ ሁሉም ተዘጋጅቶ ይጠብቃል ፍሩንዱሱም ኮረፌውም አለ …. ምን ገዶ?  ከአብርኃሙ ቤት — ተጸጋዬ!

 

የጀግና ማስተዋል – በማሰተዋል ይደመጥ!

አብነት ያለው ጀግና – ቅዱስ መንፈስ አይለዬውም!

 

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.