ለውጥ አለ ሲባል…ሳይቃጠል በቅጠል የሚያሰኝ ለውጥ እንዳይሆን!!!    (ከህዝባዊ ሰልፉ)          

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል የአዲስ አበባን የህዝብ ስርጭት ለመቀየር በማሰብ አሮሞን አዲስ አበባ ላይ ማስፈር ማለት ነው እንዴ? በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆችን ቤት በዶዘር እያፈረሱ ሜዳ ላይ በመጣል ኦሮሞን ከሶማሌና ከሃራሪ ክልሎች በታቀደ መንገድ እያፈናቀሉ በነዚህ አካባቢዎች ማስፈር ነው እንዴ ለውጥ እየተባለ ያለው? የሚገርመው ደግሞ ይህን በታቀደና በተጠና መንገድ የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት ሲባል ኦሮሞው እድሜ ልኩን ከኖረበት አከባቢ እያፈናቀሉ አዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሰፍር መደረጉን እንደ ጀብዱ የሚያወሩት የለውጡ መሪ ተደርገው የሚወደሱት አቶ ለማ መገርሳ መሆናቸው ነው። እኝህ ሰው በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው በማለት ሲምሉ ሲገዘቱ ይሰማሉ። በሌላ በኩል በህዝብ ስርጭት ስም በየአከባቢው ባሉ ከተሞች አዲስ አበባን ጭምሮ ኦሮሞ የበላይ እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ እያየን ነው። ለነገሩ አቶ ለማ ይህን ሲናገሩ ጠቅላይ ሚ/ሩም ከጎናቸው ነበሩ። ከዚህ አንፃር ሲታይ እነዚህ በኢትዮጵያዊነት ስም እየተገዘቱ ግን ውስጥ ለውስጥ የራሳቸውን ብሄር የበላይነት ለማስፈን እየጣሩ ያሉ ሁለት ሰዎች የፖለቲካ ሙስና (Political Corruption) እየፈፀሙ እንደሆነ የገባቸው አይመስሉም።

አሁን ደግሞ ህዝቡ እየተፈፀመ ያለውን ደባ በመቃወም ድምፅ ማሰማት ሲጀምር አቶ ለማ በተለመደው የማታለል ዘዴያቸው “ለውጡን ለመቀልበስ ከሚሰሩ ወገኖች በላይ እርስ በእርሳችን የምናደርገው ፍትጊያ የመጣውን ለውጥ ወደኋላ ይጎትታል” በሚል ሌላ የማደንዘዣ ዲስኩር በማሰማት የሴራ እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመሸፈን በመሞከር ላይ ይገኛሉ።  ይህ ንግግር በህዝብ ላይ በፈፀሙት ግፍና በደል ምክንያት ተንኮታኩተው የወዳደቁ የህወሃት ሰዎች ገና ለገና ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ በሚል የማስፈራሪያ ቅዠት ከህወሓት ሰዎች የበለጡ የኦዴፓ ሴረኞችን ዝም ብላችሁ ተሸክማችሁ ተጓዙ ከሚል የማታለያ ንግግር አያልፍም።

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል ከፍትፍቱ ፊቱ የሚለውን አባባል ለርሳቸው በሚያመቻቸው መንገድ ተጠቅመው በፊታቸው ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በመሸንገል ፍትፍቱን ግን ዘሬ ነው ለሚሉት ወገን ሊያጎርሱ የሚታትሩ ጠቅላይ ሚ/ር እንዲኖሩን መደረጉ ማለት ነው እንዴ?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል ኦሮሞን ከያከባቢው እያፈናቀሉ አዲስ አበባ ላይ እንዲሰፍር በማድረግ ህገወጥ በሆነ መንገድ የከተማ ነዋሪነት መታወቂያ በገፍ ማደል ነው እንዴ? ይህ ሂደት ትክክል አለመሆን በመረዳት ችግሩ እንዲስተካከል ድምጻቸውን ያሰሙ ዜጎችን ከስራ ማፈናቀልስ ለውጥ አለ ያስብላል እንዴ? በሌላ በኩልስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲናና የህዝቧ መኖሪያ የሆነቸው አዲስ አበባ መተንፈስ የምትችለው በኦዲፓና በዙሪያቸው ባሉ እንደ ጃዋር አይነት ሰዎች መልካም ፈቃድ እንዲሆን ለማድረግ መሞከር ነው እንዴ ለውጥ የሚባለው?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል “መጤና” “ሰፋሪ” በሚል ቅኝት ቡራዩና ለገዳዲ አከባቢዎች የሚኖሩ ከኦሮኦሞ ውጭ ያሉ የብሄር ብሄረስብ አባላት የሆኑ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶች፣ ወንድሞች፣ ህጻናት፣ አቅመ ደካማዎችና በሽተኞች ቤታቸውን በዶዘር እያፈረሱ መጠለያ ማሳጣት ነው እንዴ? እነዚህ ዜጎች ችግር ደረሰብን በሚል ለክልሉ ፕረዚደንትና ለጠቅላይ ሚንስትሩ አቤት ለማለት ሲሄዱ አንሰማችሁም የሚል አካል መፈጠሩ ነው እንዴ ለውጡ? ይህ ከተባለ በኋላስ ጩኸቱ ሲበረታ እኔ የከተማ አስተዳዳሪ አይደለሁም የማውቀው ነገር የለም ብለው የሚናገሩ ጠቅላይ ሚ/ር ስልጣን ላይ መሆናቸው ነው እንዴ ለውጡ? እጅግ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ የህዝብ መፈናቀል እንዲፈጠር የፖለቲካ ውሳኔውን ያሳለፈው አካል ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኦዴፓ መሆኑ ነው። ታዲያ ለውጡ የት ነው??? ችግሩ መፈጠሩን ሰምተው የፕሬስ ሴክሬታሪያቸውን (አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ማለት ነው) ወደቦታው ልከው የነበሩ ሰው በኋላ ላይ ስለጉዳዩ ሲጠየቁ የማውቀው ነገር የለም ብለው የተዘበራረቀ መልስ የሚሰጡ ጠቅላይ ሚ/ር ስልጣን መያዛቸው ነው እንዴ ለውጥ አለ የሚያስብለው?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል የህዝቡን ትግል በመጠቀም የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ከህወሃት እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ኦዴፓ እንዲቆጥጠረው ማድረግ ማለት ይሆን እንዴ? መቸም ይህ አልሆነም ብሎ የሚከራከር ሃይል ወይም አካል አይኖርም። ምክንያቱም አገርን ለማስተዳደር ወሳኝ ናቸው የሚባሉ ተቋማት በኦዲፓ ሰዎች እየተዘወሩ እንዳለ ግልፅ ስለሆነ ነው። ለዚህም ውጭ ጉዳይ፣ ገቢዎች፣ ቤተመንግስት አከባቢ ያሉ ሃላፊነቶች፣ ባንኮች፣ መከላከያ ማለትም አየር ሃይል፣ ም/ኤታማዦር ሹም እያሉ መቀጠል ቻላል።

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል ለኦዴፓ የቀረቡ አካላት በአድሎ ያለአግባብ ሊጠቀሙ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ነው እንዴ? በዚህ ረገድ ሰሞኑን አብን (NAMA) የሚሉት የአማራ የፖለቲካ ድርጅት እያቀረበ ያለውን ሮሮ እየሰማን ነው። ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ቀድሜ የተከራየሁትን የሚሊንየም ፓርክ በአድሎ ለ ኦ ኤም ኤን (OMN) ተሰጠብኝ እያለ ነው። ታዲያ ለውጡ ይሄ ነው እንዴ?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል ጃዋርና የሚመራው ሚዲያ እንዲሁም ሌሎች የኦሮሞ ልሂቃን የሚፈልጉትና ያሉት ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው እንዴ? ጃዋር ትላንትና የአንድ ቡድን የበላይነት ነገሰ፤ በዚህ ቡድን የሚፈፀም አፈናም በረከተ ብሎ ሲከራከርና ሲሟገት የነበረ ሰው ነው። አሁን ደግሞ የራሱንና ይመስሉኛል የሚላቸውን አካላት የበላይነት ለማስፈን ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑ የሚካድ አይደም። ታዲያ ሲፈለግ የነበረው ለውጥ ይሄ ነው እንዴ?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል እንዳፈተታቸው ከፋፋይ የሆነ ንግግርም ጭምር የሚናገሩ ጠቅላይ ሚ/ር ስልጣን እንዲይዙ መደረጉ ነው እንዴ? እኝህ ሰው ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ሲሰብኩ ይደመጣሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ እገሌ የኩሽ ዘር ነህ ስለዚህ የምትቀርበው ለኛ እንጅ ለሌላው አይደለም የሚል በጎጠኝነት ላይ የተመሰረተ የኦሮሞነት ታምቡራቸውን ሲደልቁ ይሰማሉ። የሰውየው ከፋፋይነት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ባለፈው የተወሰኑ የሰራዊቱ አባላት ቤተመንግስት ዘልቀው በመግባት እንዲያናግራቸው ባደረጉ ጊዜ ይበሉ ቢባሉም እንኳ የአዲስ አበባ ህዝብ በዙሪያቸው እያለ ኪሎሜትሮችን ርቀው ሄደው የሰበታና የአካባቢው ህዝብ መንግስታችን ተነካ ብሎ ግልብጥ ብሎ መምጣት ጀምሮ ነበር ሲሉ ነገሩን። ለውጡ ይህን አይነት አንድ ወጥ የሆነ መርህና አቋም የሌላቸው ጠቅላይ ሚ/ር እንዲኖሩን መደረጉ ነው እንዴ?

 

 1. ለውጥ አለ ሲባል እመራዋለሁ የሚሉት ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ተሳክሮ እያለ እንኳ አቅጣጫ ማስያዝ የማይችሉ የበላይ ሃላፊ ማየታችን ነው እንዴ? አሁን አሁን ደግሞ ይህንኑ ግራ የገባው ድርጅት አፍርሸ ሌላ አገራዊ ፓርቲ እንዲቋቋም አደርጋለሁ እያሉን ነው። በሌላ በኩል ርሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኦዴፓ ከፌደራሊዝም ውጭ ላሳር ነው የሚል መግለጫ ሰጥቷል። የተቸገርነው ነገር ቢኖር ይህ አይነት መሳከር ወዴት እንደሚያደርሰን ያላወቅን ሰዎች በለውጥ አለ እምቢልታ ልባችን ውልቅ ብሎ ሊፈርስ መሆኑ ነው።

 

 1. በርግጥ ለውጦች መኖራቸው አይካድም። ምክንያቱም እስረኞች ተፈትተዋል፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በሚል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ እንዲንቀሳቀሱ እድል ተሰጥቷቸዋል፣ የመገናኛ ብዙሃንም ልጓሙ ተፈትቶላቸው በነፃ መፃፍና መናገር ችለዋል። በነገራችን ላይ ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ ሆኖ እየቆየ ሲሄድ የግፍ መአት አወረደብን እንጅ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግም ቢሆን ሃገራችን ከተቆጣጠረ በኋላ ባሉት ጥቂት ጊዚያት ውስጥ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ያከናወነ የሚመስልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

 

 1. ለማጠቃለል ያህል አሁን ባለው ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ ወቅት እዚህም እዛም የሚታዩ የተቀባቡ ለውጦች (Cosmetic Changes) ቢኖሩም እነዚህ ለውጦች ተፈልቅቀው ሲታዩ ግን አሁንም “ዘመኑ የኛ ነው” የሚል ስሜት ያደረባቸው የኦዴፓ ሰዎች ልክ እንደ ህወሓት ሰዎች ሁሉ ምን አልባትም ደግሞ በከፋ መንገድ የበላይነታቸውን ለማስፈን እንደሽፋን እየተጠቀሙባቸው ያሉ መሳሪያዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ ምልክቶች በርክተዋል። ስለዚህ አለ የሚባለው ለውጥ እውነተኛና ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊከታተለው የሚገባ መሆኑ ለነገ የሚባል ሃላፊነት አይደለም። ሳይቃጠል በቅጠል ይላሉ ቅድመ አያቶቻችን ሲተርቱ እንዲህ አይነት ሴራ ሲያጋጥማቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.