ተሃድሶ ተፋፋምብኝ ከማለት ተዋህዶን ማፋፋም!(ቃልኪዳን ኃይሉ)

ሰሞኑን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው ፓስተር ወዳጄነህ በኤክሶደስ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ከቤቴልሄም ታፈሰ ጋር ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ ውይይቱን ደጋግሜ ተመለከትኩት፡፡ ፓስተር ወዳጄነህ በውይይቱ ውስጥ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም በተለይም “ነብያትን” እና “ፓስተሮቹ” ላይ በሰላና በበሰለ መንገድ ትችቱን አቅርቧል፡፡ አዳዲስና ከቀድሞዋ ፕሮቴስታንት አስተምህሮ ወጣ እያለ የመጣውን መጥፎና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አሰራር በጣም በድፍረት እንዲሁም በእውቀት ድባቅ መቶታል፡፡
.
በተቃራኒው ደግሞ ስለ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በብዙ ፕሮቴስታንቶች ላይ ያለውን ሸወራራ አተያይ ለማጥራትና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባልዋለችበት ላዋሏት፤ ያላለችውን አለች፤ ያላደረገችውን አደረገች እያሉ ሲከሷት ለከረሙት እንደ ፓስተር ዳዊት ሞላልኝና መሰሎቹ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምን እንደምትመስል ከ’ዴቭና ቤተሰቦቹ’ በተቃራኒና እውነት ላይ ቆሞ የኦርቶዶክስን እውነተኛ አስተምህሮ ገልጧል፡፡
.
ይህን ድርጊቱን በብዙ ኦርቶዶክሶች ዘንድ ከበሬታንና አድናቆትን ሲያተርፍለት፤ ጥቂት በማይባሉና ኦርቶዶክስንና አስተምህሮዋን በሚያውቁ መምህራኖች ዘንድ “መስካሪ አያስፈልገንም” ተብሏል፡፡ ነገር ግን በዚህ ትችት እኔ አልስማም፡፡ ምክንያቱም ከፕሮቴታስታንት ቤተክርስቲያን አካባቢ ለቁጥር የሚታክቱ፤ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ስድብና ትችቶች ተሰምተዋል ተነበዋል፡፡ በዚህም ብዙ የኦርቶዶክስ ምእመን ተቀይሟልም ምላሽም ለመስጠት ተሞክሯል።
.
ፓስተር ወዳጄነህ በተቃራኒው ቆሞ “ኦርቶዶክሰ ኢየሱስን አታውቅም ማለት ስህተት ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም በህቱም ድንግልና ቅድመና ድህረ ውልደት ድንግልናዋ አልተለወጠም፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ቅደስናዋንና ለእኔም እናቴ መሆኗን አምናለሁ እቀበላለሁ፤ ኦርቶዶክሶች እሮብና አርብ ሲጾሙ ኢየሱስን እያሰቡ ነው፤ ከኦርቶዶክሶች ዘጠኝ በአሎች ስምንቱ ኢየሱስን የሚያስቡ ናቸው፤ አብይ ጾም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመው ነው የሚጾሙት፤ መላእከትን በጣም እውደቸዋለሁ አከብራቸዋለሁ፤ መላእክት እኔ እልካለሁ ለሚሉ ፓስተሮችም መላእክት ለሰው በፍጹም አይላኩም የጎረምሶች ድፍረት….” ማለቱ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? ምስክርነቱ ለኦርቶዶክስ ምእመናን አስተምህሮ ወይም ማባበያ ታስቦም አይመስልም፡፡
.
ይልቁንስ ይህ ንግግሩ በፕሮቴስታንቱ አካባቢ ያለውን ሽወራራ እይታ ለማጥራት የተደረገ የዶክተር ፓስተር ወዳጄነህ ጥረት ሆኖ ነው የታየኝ፡፡ ይህ ጥረቱ ይበል ያሰኘዋል እንጂ ኩርኩም አያስፈልገውም፡፡ ንግግሩ በተለይ ለፕሮቴስታንቱ ምእመናን ጥሩ መስታወት ነው ብዬ እምናለሁ፡፡
.
መሰደባችንን ያልሆነውን ናችሁ ተባልን ብለን ቅር ካለን፤ የሆነውንና ያደረግነው ሲታወቅልን ሲከበር ቢቻል ማመሰግን ካልተቻለ ደግሞ ዝምታ መልካም ይመስለኛል፡፡
.
የዶክተሩ ንግግር ከዚያኛው አካባቢ ግርግር አስነስቶ ዳግም እንደ አዲስ የዶክተንሩ የግል ጉዳይ እያነሱ የራሳቸውን ግንድ ትተው የዶክተሩን ጉድፍ የሚጠነቁሉ ብዙዎች ተስተውለዋል። ስለዚህም ዶክተሩን አለንልህ ልክ ልንለው ይገልባል።
.
ተሃድሶ ተፋፋመብን ከማለት ተዋህዶን ማፋፋም
.
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በገሃድ እየተፋፋማ መሆኑ ለፕሮቴስታንቱም ለኦርቶዶክሱም ምእመን ገሀድ የሆነ ሀቅ ነው፡፡ ተሃድሶውን የሚያፋፍሙት በጥንቃቄ እንደጦርነት እቅድ ነድፈው አካሄዳውቸ አስልተው የሚጓዙ ናቸው።
.
እነዚህ አካላት ከሚጠቀሙት አካሄድ አንዱ የፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮዎችን አንሸራታው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚያስገቡ ሰዎችን ከሚገባውን ከተባለው በላይ ማድነቅና ማደናነቅ፤ እንኳን የእነሱን ሃሳብ ደግፈው አይደለም ኦርቶዶክስን ብቻ ስለነቀፉ ታላቅ አድቅቆትና ክብር ይቸራቸዋል። ይህ አንዱና ዋነኛው የተሃድሶው አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ቀላል የማይባል ውጤትና ስኬት አስመዝገበዋል፡፡
.
መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ እርግብ የዋህ እንድ እባብ ብልህ ሁኑ” ይላል፡፡ ስለዚህም የዶክተር ወዳጄነህን ንግግር ይበልጣ ማጎልበት ማድነቅ፤ ዶክተር ወዳጄነህ ውስጥ ያለውን እውነትና ብዙ ሊናገር የፈለጋቸውንና ፈርቶ ያላወጣቸው እውነቶች ካሉ በማድነቅና ሀሳቡን በማክበር በማበረታት ማስወጣት ይገባል እንጂ ማሳቀቅና ምን አገባህ ብሎ ኩም ማድረግ አይገባም።
.
ይህ በጋዜጠኞች አካሄድ ስፓይራል ኦፍ ሳይለንስ (Spiral of silence) ከሚባለው የንድፈ ሀሳብ አካሄድ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ምን ማለት ነው ሰው እውነት ይኖረውና ግን ብዙ የሚጮኽውና አየሩን የተቆጣጠረው ወሬ ከእሱ እውነት ተቃራኒ ሲሆን በብዙሃኑ ላለመገለል ሲል ዝምታን ይመርጣል፡፡
.
ስዚህም ዶክተር ወዳጄነህ የዚህ የንድፈ ሀሳብ ተጠቂ እንዳይሆን አይዞህ ማለት፤ እንዲሁም ሌሎች እውነቶችን እንዲናገር ማበረታታትና አለሁልህ እያሉ ማድነቅ አስፈላጊና የጸረ ተሃድሶ አካሄዱ አንድ አካል ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህም ብዙ በጎ ነገር እንደሚገኝ ባለ ብዙ ተስፋ ነኝ።
.
እንዲህ ካደረግን ተሀድሶ ተፋፋመብን ብሎ ከመብከንከን ተዋሕዶን በሌሎች አብያተ ክርቲያናት እያፋፋሙ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ይቻላል፡፡
.
ዘመኑ እውነት ብቻ ሳይሆን ውበትን፤ መረጃ ብቻ ሳይሆን ጥበብንም፤ ጉልበት ብቻ ሳይሆን አእምሮን፤ ልፋትን ብቻ ሳይሆን ብልሀትንም ይጠይቃል፡፡ ጸረ ተሃድሶ ትግሉ ለተነሱ ጥያቆዎች ሁሉ መልስ እየሰጡ መሄድ ብቻ በቂ አይደለም፤ ጉባኤን እየዘረጉ የራስ አስተምህሮ ብቻ ማስተማሩ ብቻ ከጥቃቱ አያድንም፤ ከዚያም ከፍ ብሎ ለመጣብን ብቻ መከላከል ሳይሆን ገፋ ብሎ ሄዶ መነሻውን መቆጣጠር፤ የተሃድሶውን አስኳል በጥያቄና በእውነት መምታት ግድ ይላል፡፡
.
እንደ ዶክተር ወዳጄነህ አይነት ሀሳብ የያዘ ሰው ሲመጣ ደግሞ ማድነቅና ማንቆለጳጰስ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ ወገን ሌሎች ያልሆኑትን “የወንጌል አርበኛ፤ ኢየሱስን ያፈነዳ…” የመሳሰሉትን አድናቆቶች ዞር አድርጎ እንደ ዶክተር ላሉ ሰዎች “እውነትን የተናገረ፤ በወንጌላውያን መሀል የተዋህዶው ሰው…” የመሳሰሉትን አድናቆቶቹ ከግብሩ ጋር የሚመሳሉ አክብሮቶች መስጠቱ መልካም ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ከሆነ ከመከላከል ወደ መልሶ ማጥቃት ተሄደ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍም ዘመኑን ዋጁት ይላል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.