የዶክተር አቢይ የአድዋ ድል መልእክት ውስጥ ተሳስቶም አንዴም እንኳ ምንሊክንና ጣይቱን በስማቸው ማንሳት አልደፈረም (ያሬድ ጥበቡ)

የዶክተር አቢይ የአድዋ ድል መልእክት ረጅምና ብዙ ቁምነገሮችን ያዘለና ትምህርታዊ ነው። ሆኖም በነዚህ አራት ገፆች በወሰደ መልእክት ውስጥ ተሳስቶም አንዴም እንኳ ምንሊክንና ጣይቱን በስማቸው ማንሳት አልደፈረም። ያለምንሊክና ጣይቱ አመራር አድዋ ምንም ነው። በእኔ ግምት ዶክተር አቢይ ምንሊክን በስሙ አንስቶ ማመስገን ጠልቶ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ያልተቀበለውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፈርቶ ነው። ግን እስከመቼ? እስከመቼ የኦሮሞን ብሄርተኝነት እሹሩሩ ብለህ ትችለዋለህ?

ዶር አቢይ ስለኦሮሞ ብሄርተኝነት ማወቅ ያለበት ነገር፣ ሁለት ስለት ያለው ካራ መሆኑን ነው። በአንዱ ስለት ኢትዮጵያን የሚገዘግዘውን ያህል፣ በሌላ ስለቱ መንግስትንም የሚገዘግዝ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ዛሬ የምንሊክን ስም መጥራት ከፈራህ ነገ ደግሞ “አድዋ የትግሬዎች እዳ ነው አንተን ምን አገባህ” ይመጣል ። ውሎ ሲያድር ደግሞ “የነፍጠኞች ንጉስ ሃውልት ከፊንፊኔ መነሳት አለበት” ይሉሃል። ዛሬ ላይ በመተክል ላይ ቆመህ ካላስቆምካቸው፣ እኔ የበለጥኩ ኦሮሞ ነኝ በሚለው የቁንጅና ውድድር አትችላቸውም። ያ ውድድር ሁሌም እጅግ ያከረረው ብቻ የሚያሸንፍበት ውድድር ነው። ዘረኝነትን ተፀየፈው፣ አትንበርከክለት።

ጀምረኸው የነበረውን ኢትዮጵያዊነት የሙጥኝ ብለህ፣ እንዳሰብከው ኢህአዴግን አንድወጥ ፓርቲ አድርገህ፣ ምርጫው ፕሬዚዳንታዊ እንዲሆን ህገመንግስታዊ ማስተካከያ አስደርገህ፣ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ መሪ ሁን። በዚህ አካሄድ የኦሮሚያ ክልልን 1/3ኛ ድጋፍ እንኳ ብታገኝ ማሸነፍ ትችላለህ። ይህን ለማድረግ አመንትተህ ፣ ሰሞኑን ሲደረግ እንደከረመው ግን አንተ በተሰየምክበት ጉባኤ አዲስአበባን በኦሮሞ ተፈናቃዮች ለመክበብ ሲዘከር ዝም እያልክ፣ በአድዋ 123ኛ የድል በአል መልእክትህ ላይ የምንሊክንና ጣይቱን ስም አንስተህ ለማመስገን እየፈራህ የዘር ፖለቲካን መቋቋም አትችልም። ተወዳድረህም አታሸንፋቸውም።

ደረስኩባቸው ስትል መመዘኛውን ከፍ ያደርጉብሃል። ነገ፣ ግማሽ አማራነትህ ጥያቄ ይሆናል። ኢትዮጵያዊ ስሜትህ ወንጀል ይሆናል። ኦህዴድ/ኢህአዴግ ውስጥ የነበረህ ስልጣንና የተሰራ ስህተት መክሰሻ ይሆናል። ስለሆነም በማታሸንፍበት የቁንጅና ውድድር ውስጥ አትግባ ። ያንን ለነዳውድና ጃዋር ተወው፣ አይመጥንህም፣ ደግሞም ያጠፋሃል! ከዓመት በፊት ልባችንን ያማለልክባትን ኢትዪጵያን ይዘህ ግን መንገድህ ቀና ነው፣ አታመንታ! ፈጣሪ ቀናውን ያሳይህ!

1 COMMENT

  1. አቶ ያሬድ ጥበቡ አቢይ ሲበዛ ብልህና አስተዋይ መሪ ናቸው፣፣ አትሳሳቱ፣፣ እምዬ ምንልክን ሺህ ጊዜ ቢያወድሳቸው ከሁለቱም ያለው አክራሪ በሽሙጥና ስድብ ናዳ ብቻም ሳይሆን የተንሳፈፈውን አስተዳደራቸውን ይፈታተናል፣፣አሁን እንደው ስንት እልባት የሚያሻው ጉዳይ እያለ ሰውዬውን በዚህም ስማቸውን አንስቶ ሁሉም ፎከስ እንዲያረግበት አላስፈላጊ ትችት ምን የሚሉት ነው? አቢይና ሁሉም ቲም ለማ ተብዬ የለውጥ ሀይላት እግራቸው ፈንጂ ላይ ረግጦ ወደላይ ወደጎን መርገጡን ፈርተውት ይመስለኛል፣፣ አገራችሁን የምትወዱ ወገኖች የምመክራችሁ እስከምርጫዋ ቀን ድረስ እነዚህን በታሪክ አጋጣሚና በፈጣሪ ቸርነት እዛች መንበር የተቀመጡትን ሰዎች ሲሆን ቀና ጉልበት እየሰጠናቸው ወደምርጫው በሰላም ቢያሸጋግሩን ይሻላል፣፣ ካልሆነ ደሞ ቅጥ ያጣ ፀጉር ስንጠቃ ውስጥ መግባቱ ያስተዛዝባል፣፣ ሳስበው “ምነው የኢትዮጵያ ህዝብ እግራችን የቆመበትን ፈንጂ እያየ እንዳላየ ሆነብን ” እያሉ በምሬት ከየባለቤቶቻቸው ጋር የሚያወሩ ሁሉ ይመስለኛል፣፣ የኛ ህዝብ ለአስተዳደር አደለም ዛሬ እንዲህ በጎጥ ተቆላልፎ ይቅርና ጥንትም በንጉሱ ጊዜ የማይመች ህዝብ ነውና፣፣ እኒህ አቢይ ከጃንሆይ በላይ ዘዴኛ ይመስሉኛል ነገረስራቸው፣፣ ምንሊክን ለማወደስ አደለም ዖሮሞ የሆነ የአገር መሪ ቀርቶ ምንም ስልጣን የሌለን እንደው ከአክራሪው የወገን ውረፋ ሽሽት ብለን ስማቸውን በበጎ ለማንሳት ስንቶች እንደፍራለን? ማን ይሙት ከኔ በቀር የምንሊክን የጥቁር ህዝብ ኩራትነት የማይረዳ ዖሮሞ ኢትዮጵያዊ ሳይኖር ቀርቶ መስሎህ ነው? አብሮ ለመኖር እየተባለ እንጂ፣፣ እናም ይልቅ ሰውዬውን ከለየላቸው ፅልመቶች በላይ በአደባባይ አበሳውን ሲዘክር የሚውለው በተለይ ፊደል ቆጠር መሆኑ ነው፣፣ ማንን ይጠቅማል እስቲ እንዲህ ብሎ ትችት አቶ ያሬድ? አትፍራ ብሎ ነገር፣፣ በውትድርናውም ይሁን በብቃቱ እስካሁን ካየናቸው መሪዎች በላይ እጅግ አርቆ ተመልካችና አገናዛቢ የሆነን መሪ፣ ያውም ወጣት ሆኖ? ከማናችንም በላይ እረ በኢትዮጵያ ይሁንባችሁ አደብ ግዙ፣፣ ጊዜ ማሳለፍያ ከጠፋ ሀይስኩል፣ ኤሌሜንተሩ ብዙ በጎ አድራጎት ስራ አይጠፋም እኮ? መቼ ይሆን የተማረው ወገናችን ከነካልዲስ ቤት ክሪቲክነት ወደስራ የሚገባው? ካልተዳፈርክ “ያጠፉሀል”? አይ ምክር ፣፣ ከዚህ ቀደምም ብየዋለሁ የንቀታችሁ መጠን ቅጥ አጣ፣፣ ደግነቱ ሰውዬውስ ይህ አባባልህ የሚያስቃቸው ሁሉ ይመስለኛል እኔን ነደደኝ እንጂ፣፣ ሰላም ሁን አቶ ያሬድ፣፣

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.