አባ ማቲያስ; በምንኩስና የሚያገኙት ክብር ይቅርብዎት፤ ባይሆን በጥምቀት ያገኙት ጸጋ ይበቃዎታል። ( መስቀሉ አየለ)

እግዚአብሔር ቀድሞውንም ይጠቀም ብሎ ሰውን በህገ ልቦና ፈጠረው። በዚያ ጸንቶ መኖር ባይቻለው ከስጋ ፍርድ ይድንበት ዘንድ ህገ ኦሪትን ሰራለት። በህገ ኦሪት ጸድቆ ወደቀደመ ክብሩ መመለስ ባይሆንለት አንድ ልጁን በስጋ ማሪያም ገልጾ ህገ ወንጌልን ሰራ፤ስጋውን ደሙን ሰጠ። ሁዋላ ደግሞ ፍጹም መሆን ቢፈልግ ብሎ ስርአትን ምንኩስናን አራተኛ ህግ አድርጎ ሰራለት። ይህን የፍጹምነት መንገድ አንድ ብሎ ሲጀምር ለዚህ ክብር የጠራው የመጀመሪያውን ገዳማዊ አባት አባ እንጦንዮስን ነበር። በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል ዕጅ አምስቱን የጸሎት ጊዜያት ከነስግደት ስርአቱ (ኪዳነ አዳም፤ኪዳነ ኖህ፤ ኪዳነ አብርሃም፤ ኪዳነ ሙሴ እና የሃዲስ ኪዳን ፮ኛውንና ፯ኛውን የጨመረው እራሱ ነው) አስተምሮ ቆቡን በአክሊለ እሾህ፤ ቀሚሱ የመጎናፀፊያ፤ መቀነቱ የመግነዝ፤ አስኬማው የትንሳኤ ሙታን አንድም መቀነቱና ቀሚሱ አይነቱ ቀድሞ እመቤታችን ብስራተ መለአከን ስትሰማ
የለበሰችው በንጽሀ ስጋ፤ ቆቡን በንጽሀ ነፍስ እንዲሁም አስኬማውን በንጽሃ ልቦና መስሎ አልብሶ አመንኩሶታል።

እንግዲህ ምንኩስና ግብሩ አለመ መላዕክት ሲሆን ይህም የፍጹምነት መንገድ ከግብጽ በረሃ ጀምሮ እያደገና እየሰፋ እስከ ሀገራችን ድረስ ለክርስትና ህይወት እስትንፋስ ሆኖ ብዙዎች ሰማያዊ ክብርን የወረሱበት ኢትዮጵያም መሬቱን ከፍለው ገሀነም እሳትን እስከማየት የደረሱ ብጹአን አባቶችን እስከማፍራትየደረሰችበት በዚህ ፬ኛ በሆነው የምንኩስና ኪዳን ነው።

ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው። ግንኙነቱ የተቃርኖ ነው። ቤተክርስቲያኑን እንመራለን ብለው እራሳቸውን በጴጥሮስ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ቦታ ያስቀመጡ ባለባበስ ሰማያዊ በግብር ምድራዊ የሆኑ መነኮሳትና ጳጳሳት አቡነ ማቲያስና አንጋሾቻቸው እየሄዱበት ያለው መንገድና እየፈጸሙት ያለው በደል ሲታይ አቡነ ጳውሎስ ተክለው የሄዱት አባ ማቲያስም የወረሱት ሰንኮፋ ዛሬ ድረስ ያልተነቀለበት፣ የለውጡ ንፋስ ገና ሰርጾ ያልገባበት አንዱ ተቋም የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን እያየን ነው።

ብዙዎቹ ገዳማውያን ቀርቶ ገና ያልተጠመቁ ጀማሪ ምእመናን ሳይቀሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር አንገታቸውን በሰይፍ እየተቀሉ በገዛ ደማቸው እየተጠመቁ የእግዚአብሔርን መንግስት በወረሱባት ቤተክርስቲያን ዛሬ ግን የቀደምት አባቶቻችን ገድላቸው አፈታሪክ በሆነበት፣ የደገኛ አባቶቻችን የነቅዱስ ዮሀንስ አፈዎርቅና አትናቴዎስ ዘእስክንድሪያ ድካማቸው ከንቱ የሆነበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እውነተኛ የፍርድ መፅሀፍ ይዘው እውነተኛውን ቃል ለመናገር ጉሮሮዋቸው አጥንት የሆነባቸው አባቶች የሞሉበት፣ ቤተክርስቲያንን ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እነሱን ጳጳሳት አድርጎ
የሾመበት አላማ ግቡን የሳተበት፣ ስዩመ ደደቢታውያን ግን በክህነትና በምንኩስና ካባ ብቻቸውን የነገሱበትና ጸጋ እግዚያብሔር የተለየበት ቤት መሆኑን ይህ ዘመን
አሳይቶናል።

ሳይገባን ክርስቲያን በሚለው ስም የተጠራን እኛ ዛሬ በዚህ በመጨረሻው ሰአት ስለእግዚያብሔር ፍቅር ይህን አለም ከነክፉ መሻቱ ሰቅለው ስጋቸውን ሊቀጡ በበረሃ ገድመው የተቀመጡ አረጋውያን መነኮሳት ዛሬም ድረስ በንጹህ ኢትዮጵያዉያን ደም በደለቡ የ አጋዚ ጭፍሮች በአታቸውን መድፈሩ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ መቀጠሉንና መከራችን አለመቆሙን እያየን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው።

ክርስቶስ በስጋ ማርያም መምጣቱ የሰውን ባህሪ ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ነበር። በሃጢያት ያጣነውን የእግዚያብሔር ልጅነት ይመልስልን ዘንድ ነበር። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ የእግዚያብሔር ልጅ ይሆን ዘንድ፤ የእግዚያብሄር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ ማለት ነው። የእግዚያብሔር ልጅነት የመጨረሻው ጸጋ መሆኑ ነው። ለእግዚያብሄር ልጅ የመሆን መብት የተገኘው ደግሞ በክርስቶስ እንደሆነ ሃዋርያው ሲገልጽ “የእግዚያብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ እንዲሁም ነን። ወዳጆቼ ሆይ አሁን የእግዚያብሄር ልጆች ነን ምን እንደሆንን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ሲገለጥ እርሱ እንዳለ እናያዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን በርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹህ እንደሆነ ራሱን ያነጻል” ፩ኛ ዮሐ። ፫

እግዚያብሔር ለመረጣቸውና ለወደዳቸው ሁሉ ይህንን የፍቅሩን ጸጋና በረከት በልቦናቸው ውስጥ እንዲኖር አድርጉዋል። ፍቅሩ በልቦናችን እንዲኖር ያደረገው የሰጠን የተስፋው ቃል የማይቀርና እውነተኛ መሆኑን ከመመስከር ጋር ነው። ስለዚህ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚያብሄር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም የተባለው።በዚህም ነፍስና ስጋ፤ ሰውና መላእክት፤ ሰማይና መሬት ጭምር ታረቁ። ይህ እለት ቀድሞ በሐመረ ኖህ በምሳሌ የታየውና እርጊቢትዋ በዘንባባ ያበሰረችው ሰላም ተፍጻሜተ ትንቢት ነው። የእውነተኛው ሰላም ጥላ ነው። በመስቀሉ ሰላምን አደረገ እንደተባለው። ሲኦል እንደተማረከው።ሰይጣን ድል እንደተነሳው። ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ ወዴት
አለ፧ ብሎ ነቢዩ ሆሴእ እንደጠየቀው። መቃብር እንደደነገጠው።

እንግዲህ አሮጌው ሰውነታችን ተወግዶ ባዲስ ሰውነት የምንፈጽመው በጎ ምግባር ለእግዚያብሔር የምናቀርበው በጎ ማአዛ ያለው ሰውነታችን መሆኑ ግልጽ ነው። ቅዱሱን እግዚያብሔሄን በሃጢያተኛ ሰውነት መዋሃድ አይቻልም እና።ለዚህም ነው በአለም ተቀምጠው ምጽዋትን በመመጽወት ከሚኖሩ ክርስቲያኖች ይልቅ ሰውነታቸውን በጥም በረሀብ በስግደት በጸሎትና በትግሀ-ሌሊት ቀጥቅጠው ለእግዚያብሄር የተቀደሰ መስዋእት ያደረጉ መነኮሳት ክብራቸው የበዛ የሚሆነው። በዚህም ክርስቶስ ለኛ ያለው የተገለጠበትን ጸጋ ልጅነትን የሰጠበትን እና ራሱን በጎ መስዋእት አድርጎ ያቀረበበትን መዋእለ ስጋዌ ፈለግ ተከትለው በስሙ የተጠመቁበትን ክርስቶስን በግብር የመሰሉት። “ተመሰሉ በእግዚያብሄር ከመውሉደ ፍቁራን” እንዲል ቅዱሱን እግዚያብሔርን የመምሰል ህይወት ለሚናፍቁ መልካም አርአያ በመሆን ለአልጫው አለም ጨው፤ ለጨለማው አለም የተራራ ላይ መብራት በመሆን በሞት አዘቅት ውስጥ የሚዳክሩትን ሁሉ ህይወት ላለው የክርስትና ህይወት ያበቁት። በዚህም ክርስትና በሰው ህይወት ላይ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል መአዛውም እንደምን መልካም እንደሆነ ምሳሌ ሆነዋል። የዚህ ሁሉ የበረከት ምንጭ የሆነውን እግዚያብሔርንም ተከብረው አስከብረዋል። ምክንያቱም ለአንድ ሰው የጸጋና የበረከት ሚስጢር ማወቅና ማመን በራሱ ቀላል ነገር አይደለም። የመጀመሪያው በረከት እግዚያብሔር ከጸጋ የወረድነውን እና የቀኝ እጁ ስራ የሆነውን አዳማውያን ጠፍተን እንዳንቀር በልጁ አማካኝነት የሚያመለክት ነው። ስለዚህ እግዚያብሄር እኛን ነውር የሌለብን ቅዱሳን አድርጎ ወደሱ ሊያቀርበን በፊቱ
ሊያቆመን በፍቅሩም ሊያኖረን ማሰቡን እና በልጁም አማካኝነት ይህን እንደፈጸመው ቃሉ ያስረዳል። የጌታችን ትንሳኤ በቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ በምድር ከተገለጠና ከተሰበከ የሃዋርያት ድምጽ በምድር ዳርቻ ሁሉ ከደረሰ፤ ክርስትና ማፍራት ከጀመረ፤ ከቤተ እስራኤል ቅዱስ ጳውሎስ ያህል ሐዋሪያ ከተጠራና ቤተ ክርስትያን ከአይሁድ ዛኒጋባ ወጣ ወደ ብሄረ አህዛብ ከተስፋፋች በሁዋላ ክርስቲያን ከስሙ ጀምሮ እስከ ተግባሩ የክርስቶስን ስምና ተግባሩን ተሸክሞ የሚኖር መሆኑ በተግባር ታይቱዋል። ቅዱስ ጳውሎስም “የእየሱስ ህይወት በህይወታችን ይገለጽ ዘንድ ሁል ጊዜ የእየሱስን መሞት በስጋችን ተሸክመን እንዞራለን” ፪ኛቆሮንቶስ ምዕ ፬ እንዳለ።

ይህ የሚያሳየው ሁለንተናችን ለእግዚያብሔር የተሰጠ ወይም በደሙ የተገዛን የደም ዋጋ መሆናችንን አምነን መላ ሰውነታችንን “እግዚያብሔርን ደስ የሚያሰኝና ህያው ቅዱስም መሰዋእት አድረገን ማቅረብ የሚገባን” መሆኑን ለማመልከት ነው። ሃዋሪያው ጳውሎስም “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” ሲል ራሱን ክዶ መስቀሉን ተሸክሞ ህይወቱን ለክርስቶሳ አሳልፎ መስጠቱን በዚህም በዘመኑ ከነበረው የፈሪሳውያን ባህልና አሸዋው ልባቸው ከወለደው ደረቅ አስተሳሰብ ጋር ያደረገውን የተጋድሎ ህይወት ሲገልጽ ነው።

እንግዲህ ሦሥተኛውን ኪዳን ይፈጸም ዘንድ አንድ በክርስቶስ ስም የተጠመቀ ክርስቲያን ክርስቲያን በመሆን ሊኖረው የሚገባው ገጽታ ይህን መምሰል ካለበት እራሱን ከአምላኩ ጋር በአራተኛው የኪዳን ህግ ማለትም ከአለም ድሎትና ፍትወት የተለየበትን የቆብ ምልክቱንና የተገነዘበትን ሰንሰለቱን በውስጡ ታጥቆ መሞቱን ካወጀና በስርአተ ምንኩስና ራሱን ከአምላኩ ጋር ካቆራኘ በሁዋላ ሊሄደው የሚገባው ክርስቲያናዊ ጉዞ ምን መምሰል እንዳለበት ማወቅ አይከብድም።ቀደም ባለው የኦሪቱ ዘመን እስራኤል ዘስጋ ከስደት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለሱ አስራ አንዱ ነገድ እጣ ተጣጥለው መሬታቸውን ሲወስዱ የቀረው አንድ ነገድ (ቤተ ሌዋውያን) ግን እርስታቸውን እግዚያብሔርን አድርገዋልና ምድረ እርስትን አልተካፈሉም። በስጋ ለተሰራ ሃጢያት በእንሣት ደም መርገመ ስጋን ያነጹ ዘንድ ስልጣን የተሰጣቸው ሌዋውያን ካህነት ይህን ያህል ከአለም ሀብትና
ንብረት ከተለዩ የቅዱሱን የእግዚያብሔርን ልጅ ደም በመሰዊያው ፊት የሚፈትቱት በስጋና በነፍስ ላይ ስልጣን ያላቸውና የመንግስተ ሰማይን ቁልፍ በእጃቸው የያዙ የአዲስ ኪዳን ጳጳሳት ወመነኮሳት ምን ያህል ራሳቸውን ከዚህ አለም ሀብትና ክብር መለየት ይገባቸው ነበር ይሆን፧ ለመሆኑ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል ከደፋ በሁዋላ ወደ አለም ተመልሶአልን፧ ወደመቃብር ነው የወረደው። “መንኮሰ- ሞተ” እንዲባል፤ ሞተ ተብሎ ተገንዞ፣ ተስካሩን አውጥቶና መሞቱን እንዳይረሳ ከዚህ አለም ህይወት የተፋታበትን አስኬማ ታጥቆ የሚኖር፣ እንድሁም ቤተክርስትያኒቱንና ምእመኑን እጠብቃለሁ ብሎ እረኝነት የተሾመ አንድ የቤተክርትያን መሪ የፊተኛው ፓትሪያሪክ ጥለውት የሄዱት ጥይተ ከላ መኪና አልበቃ ብሎ “ቦዲ ጋርድ ካልተሾመልኝ እከዳለሁ” አይነት ዛቻ መስቀል ተሸክሞ ፍርሃት፣ በነፍስ እኖራለሁ ብሎ ስጋን መሞሽር፣ ሰማያዊ ነኝ ብሎ አሜሪካዊነት፣ ጸሎተ ማርያምን እደግማለሁ ብሎ አጃቢ አጋዚ ካልመጣልኝ የሚለው እሰጥ እገባ ሁሉ ኢትዮጵያን አፍርሶ የቁልቋሏን ሪፐብሊክ ለማዋለድ የሚደረገው ቅዠት አካል እንደሆነ ለኛ አይነግሩንም።ሁለት ወር ያልሞላ ግዜ መታገስ አቅቷቸው አብይ ዖምን የሚያህል የአጽዋማት ሁሉ በኩር ተራምደው እንበለ ቀኖና ቤተክርስቲያንን ከበሮ አስደልዘው የተሾሙበትና ወደ መንበሩ የወጡበትን ሂደት ቁጭ ብሎ ላስተዋለው ሰው ገና ሳይወለድ የጨነገፈ የኑፋቄ መንገድ እንደነበር ግልጽ ነው። ለማንኛውም ምኞትዎ ስጋና ደም ገዝቶ በተግባር እንዲገለጥ የእኛም ጸሎታችን መሆኑን እንዲያውቁት ይሁን።

ዛሬ የቤተክርስትያኒቱን አንጡራ ሃብት የዘረኞች መጫወቻ ሲሆን በገጠር አቢያተ ክርስቲያናት ካባ ጠፍቶ በሴት ቀሚስ ይቀደሳል፤ በሴት ዣንጥላ ታቦት ይወጣል፤ መገበሪያ ጠፍቶ ስብሃተ እግዚአብሄር እየተስተጉዋጎለ በተክርስትያናት እየተዘጉ ነው።ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ ሰረገላ አዘጋጁልኝ እንዳላለ ይልቁንም በተናቀች የአህያ ውርንጭላ መሄዱን ረስተዋል። በትርጉዋሜ ዮሃንስ እንደተጻፈው ሰለአዳም የተረገመችውን መሬት በቅዱሳተ እግሮቹ ይቀድሳት ዘንድ ያለጫማ በባዶ እግሩ ተመላለሰ የሚለው ቃል ዛሬ ለነሱ ተረት ነው።

ምንኩስናቸው ለስልጣን መውጫ ሳይሆን ህጉን አክብረው ንጽህናቸውን ጠብቀው በተጋድሎ እየኖሩ በአእምሮ ጠባይ የማይመረመር የክርስቶስን ጸጋ እንዲያገኙበት፤ ልኡል በፍህ ወደሚሆን ብርሃን እስኪጠጉ ድረስ ሚስጢር የሚያዩበት ከዚህ አለም በሞት ሳይለዩ የጥልቅና ሰማያዊ ሚስጢር ባለቤቶች የሚሆኑበት፤ ከመሎት በሚሰጥ በተወደደ ብርሃን አሸብርቀው ወደ ልኡል ብርሃን የሚወጡበት፤ እንደ ትጋታቸውና እንደመጠበቃቸው መጠን የክርስቶስን ብርሃን ተዋህደው በመልክ ጌታችንን የሚመስሉበት እንዲሆኑ ነበር።ክመስዋእቱ እየዘረፉ የበሉት አስራት ያሰከራቸው፣ የጎሳ ተስቦ፣ ከንቱ ውዳሴ፣ እብሪትና ድንቁርና ተጋግዘው ያቆሟቸው ከደደቢት ተቆርጠው በመሃል ሸዋ የቀሩ አበጋዞች ከጥቂት አመታት በፊት ከመንበረ ጸባዖት የታዘዘው ሰይፍ አንዱን ከቤተክህነት አንዱን ዘንዶ ደግሞ ከቤተመንግስት ስለቀነጠሰው ሞተ በኩር የሰሙት ነገር ያለ አይመስልም። ፈርኦን እንደደነደነ ደንድነዋልና ፈሮንን የዋጠ ቀይ ባህር ሳይውጣቸው አይቀርም።

# ፍትሕ ለኤርሚያስ አመልጋ !!
# ትኩረት ለጅጅ ሽባባው!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.