ከዳንሻ ከተማ የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች መንግሥት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2011 ዓ.ም ) ማንነታቸውን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጹ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከዳንሻ ከተማ ተፈናቅለው በጠገዴ ወረዳ ሶሮቃ ንዑስ ወረዳና በሌሎች አጎራባች ወረዳዎች ተጥልለው ይገኛሉ፡፡ ተፈናቃዮቹ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል፡፡

ለመፈናቀሉ ምክንያት የሆነው ለረጅም ዓመታት የአማራ ክልል ሰሌዳ ተለጥፎባቸው ሲሰሩ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳቸውን እንዲቀይሩ ካለበለዚያም ከተማውን ለቅቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው መሆኑን ነዋሪዎች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹በአማርኛ ማስታወቂያና ‹ባነር› አሰርተን የነበርን ባለሆቴሎች ወደ ትግርኛ ቋንቋ እንድንቀይር ተገድደናል›› ብለዋል፡፡

‹‹ማንነታችንን መሠረት በማድረግ አንገታችንን እንድንደፋ ተደርገናል›› ያሉት ተፈናቃዮቹ በማንነታቸው፣ በቋንቋቸውና በባሕላቸው ራሳቸውን እየገለጹ ለመኖር ባለመቻላቸው አካባቢውን ለቅቀው ለመውጣት እንደተገደዱ ነው ያስረዱት፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዳንዶቹ ለአብመድ ሲናገሩ ‹‹ለእንግልት፣ ለድብደባና ለእስር ተዳርገናል፡፡ ታስረውና ተደብድበው የደረሱበት የማይታወቅ ብዙ ወጣቶችም አሉ›› ብለዋል፡፡

ማንነታቸው አማራ በመሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጥሶ ለዘመናት ከኖሩበት ቤታቸው እንደተፈናቀሉም ተናግረዋል፡፡ የሶሮቃ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ አለልኝ በከተማዋ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ተብለው በተዘጋጁ ክፍሎችና የቀበሌ ቤቶች ከ250 በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአጎራባች ወረዳዎችና በሶሮቃ የተለያዩ አካባቢዎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ በርካታ ተፈናቃዮች እንዳሉም ገልፀዋል፡፡

ንዑስ ወረዳው ከጠገዴ ወረዳ ማዘጋጃ ቤት ጋር ለተፈናቃዮች የዕለት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በጀት ቢይዝም የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሆነ ከወረዳው አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ተፈናቃዮችን እንዲረዳና ወደነበሩበት አካባቢ እንዲመልስ፣ እንዲያቋቁምና ሰላምና ደኅንነታቸውን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡

ተፈናቃዮች የሶሮቃ ሕዝብ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ አስቸኳይ ዕለታዊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ዕርዳታ እንዲደረግላቸውም ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ማንነታችን አማራ በመሆኑ መንግሥት ማንነታችንን ያስከብርልን፤ሌላ ገለልተኛ ወገንም በዳንሻ አካባቢ ገብቶ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሔ እስክናገኝ ሊረዳን ይገባል›› ብለዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ የጠየቅነው የትግራይ ክልል መንግሥት ችግሩ የተፈጠረው ‹‹ህገ ወጥ›› የመኪና አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ሥራ በመጀመሩ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡ ነዋሪዎቹ ያቀረቡት ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ- ከሶሮቃ / (አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.