የጌዴኦ ስቃይና የሲዳማ ጥያቄ በደቡብ (ኤርሚያስ ታኮማ)

ሰሞኑን በስራ ጉዳይ ወደደቡብ ኢትዮጵያ በተጓዝኩበት አጋጣሚ የጌዴኦ ተፈናቃዮችን ለመጎብኘት እና ስለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጉዳይ ሰዎችን ለማናገር ሞክሬ ነበረ።

ጌዴኦ
ዲላ ከተማ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ በምእራብ ጉጂ ዞን ከሚገኙ የዞኑ ከተሞች ማለትም ኤደራ፣ ብርብርሳ ቤራ፣ ቢሊዳ፣ ኤሌፋርዳ፣ ዲንቱ፣ ዲቢሣ፣ ቃርጫ እና ከተለያዩ የገጠር ወረዳዎች የተፈናቀሉ የጌዴኦ ተወላጆችን ለማየት ችያለሁ። የአካባቢው ተወላጆች እንደሚገልፁት በይርጋጨፌና ወናጎ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ተፈናቃይ እንደሚገኝና ቁጥራቸውም ወደሀምሳ ሺህ እንደሚጠጋ ይገልፃሉ (ዳታው ጥናት ያስፈልገዋል)

እነዚህ የጌዴኦ ወገኖች መፈናቀላቸው አግባብ አለመሆኑ እንዳለ ሆኖ አስቸኳይ እርዳታን የሚሹ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። የአካባቢው ህዝብና አንዳንድ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከሚያደርጉላቸው ድጋፍ ውጭ ሌሎች አካላት ምንም ድጋፍ ሲያደርጉላቸው አይታይም። መንግስት የሚያቀርበው እርዳታም ያን ያህል በቂ ሆኖ አላገኘሁትም። በሌሎቹ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ወገኖች ሲፈናቀሉ ሚዲያው አክቲቪስቱ እና ፖለቲከኛው ጭምር ለተፈናቃዮቹ እንድረስላቸው ሲል ይውላል። በርካታ ገቢ ማሰባሰቢያ እየተዘጋጀ እርዳታዎችን ማድረግ ተችሏል። ጌዴኦ ላይ ለምን እንዲህ ድምፅ ጠፋ? መልሱ ቀላል ነው። ኢትዮጵያውያን ብሄርተኞች ሆነናል፤ ከኛ ብሄር ውጭ ያለ ዜጋ ቢፈናቀል ወይም ቢሞት ጉዳያችን አይደለም። ጌዴኦ ደግሞ ጎጠኛ አይደለም። ኦሮሞ አፈናቀለኝ ብሎ እንኳን ዲላ የሚኖሩ ኦሮሞ ወገኖቹ ላይ ምንም አይነት ክፉ ነገር አላደረገም። ማንም ሰው ዲላ ሄዶ ይህንን ማረጋገጥ ይችላል። በርካታ የቦረና ተወላጆች በስፍራው በነፃነት እየኖሩ ነው። ይህንን ህዝብ ግን አሳዝነንዋል። ልንረዳው ልንቀርበውና አለንልህ ልንልለት ይገባል። በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እባካቹህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅታቹህ ለወገናችን እንድረስለት።

ሲዳማ

የሲዳማ ፖለቲከኞች ሲዳማን ወደክልልነት ለማሳደግ እንቅስቃሴ ከጀመሩ ትንሽ ሰንበትበት ብለዋል። ሆኖም ጥያቄያቸው በሁለት መንገድ ነው እየቀረበ ያለው በህጋዊና በህገወጥ መንገድ። በህጋዊ መንገድ ለክልሉ ምክር ቤት እና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ያቀርባሉ በጎን ደግሞ በህገወጥ መንገድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ አይደግፉም የሚሉ የክልሉ ባለስልጣናትን ኤጄቶ በሚባለው ቡድን አማካኝነት ያስደበድባሉ፣ ያስፈራራሉ እንዲሁም ንብረት ያወድማሉ።
በሀዋሳ ከተማ በሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች በተለይም በወላይታ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው እጅግ የሚያሳዝን ነው። አንድ የከተማው ነዋሪ ያጫወተኝን ላስነብባቹህ

ሁለት የሲዳማ ወጣቶች አንድ የወላይታ ተወላጅ በባለቤትነት በሚያስተዳድረው ቡቲክ ውስጥ ጫማ ለመግዛት ይገቡና የጫማውን ዋጋ ይጠይቃሉ። የቡቲኩ ባለቤት ጫማው 800 ብር እንደሆነ ይነግራቸዋል። እነርሱ 200 ብር እንዲሸጥላቸው ሲጠይቁት ስላልተስማማ ብቻ ኤጄቶ የሚባሉትን የሲዳማ ወጣቶች በመጥራት ቡቲኩን እንዳወደሙበት የከተማው ነዋሪ አጫውቶኛል። ዛሬም በወላይታ ተወላጅ የክልሉ ባለስልጣን ላይ የሆነው ተመሳሳይ ነው።

አብዛኞቹ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት የዘር ሀረጋቸው ከሲዳማ ስለሚመዘዝ የሲዳማ የሆነችውን ሀዋሳ የክልሉን በጀት በመጠቀም በተገቢው መንገድ አሳድገው በአንፃሩ ቀደምት የደቡብ ከተሞች ሆሳእና፣ አርባምንጭ፣ ዲላ ወላይታ ሶዶና ጂንካን ሲያቆረቁዙ ከርመዋል። ሀዋሳ ካደገችና ጥሩ የመዝናኛ ከተማ መሆኗን የተመለከቱት የሲዳማ ፖለቲከኞች ክልል እንሁን ሲሉ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ይገኛሉ። ሲዳማ ክልል ከሆነ ለተቀሩት የደቡብ ክልል ህዝቦች ትልቅ እረፍት ነው። ሀዋሳ ግን ሲዳማ ክልል የሆነ እለት ቁልቁል መራመድ ትጀምራለች። ሰላም የሌላት ከተማ ውስጥ የፀጥታ ኃይል እንጂ ቱሪስት አይመጣም።

 

1 COMMENT

  1. ato Ermiyas Tacoma (Seatac)
    please don’t come to hawassa with such inflated perspective; what would you benefited by antagonizing the most humble society SIDAMA? Was SIDAMA’s self governance question weekly old? what a poisonous person

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.