የኢህአደግ አባል ድርጅቶች የተናጠል መግለጫዎች ጋጋታ ምንድነው? 

አደፓ ፤ ኦዴፓና ህወሃት ባለፈው 24 ሰአት ውስጥ በየግላቸው አንዳንድ መግለጫዎችን አውጥተዋል። በሲዳማ ጉዳይ ውስጣዊ አንድነቱ እየተናጠ ያለው የደቡብ ክልል ሲቀነስ ከ4ቱ የኢህ አደግ ድርጅቱች 3ቱ በየግላቸው ይፋ ያደረጉት መግለጫ አጠቃላይ አንድምታ ሁሉም በተናጠል ለመፋለም የተዘጋጁበት ጦርነት ያለ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ኦዲፓ በአዲስ አበባ ዙሪያ ስለተሰሩ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ጉዳይ ባወጣው መግለጫ ከክልሉ መንግሥትና ከሚያስተዳድረው የኦሮሞ ህዝብ ፈቃድና እውቅና ውጪ ቤቶቹን ለባለ እድለኞች የማስተላለፍ ጉዳይ እንዲቆም ከመጠየቅ አልፎ አዲስ አበባን አስመልክቶ የኦሮሞ ጽንፈኞች ለዘመናት ሲያቀነቅኑት የኖሩትን የባለቤትነት ጥያቄ መቀላቀሉን በማያሻማ ቋንቋ ግልጽ አድርጎአል። ይህ አቋም ከ80 % በላይ ኦሮሞ ያልሆነው ማህበረሰብ ለሚኖርባት አዲስ አበባ የጦርነት ነጋሪት መስሎአል። አዲፓ በበኩሉ ባወጣው በመግለጫ “የትግራይ ክልል እያካሄደብኝ ያለውን የጦርነት ቅስቀሳ ያቁም” ሲል ጠይቆአል። ህወሃት ደግሞ ለአዲፓ መግለጫ በሰጠው አጸፋ በትግራይ ህዝብ ላይ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ያሉት “ጽንፈኞች እንጂ እኔ አይደለሁም” በማለት በመግለጫው ላይ የስፈረው አቋሙ እንደገና እንዲብራራለት ጠይቆአል። ህወሃት ከማብራሪያ ጥያቄው ጎን ድርጅቱና የትግራይ ህዝብ ጦርነትን ከማንም በላይ አሳምረው እንደሚያውቁና እንዳለፉበት ገልጾ ለሰላምና ለወንድማዊ ግንኙነት ሲል ትእግስትን እንደሚያስቀድም ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፎአል።
ይህ ማለት እንግዲህ ሶስቱም የኢህ አደግ ድርጅቶች በተናጠል የሚዘጋጁበት ወይም ለመዘጋጀት የወሰኑት ጦርነት እንዳለ አመላክተዋል። ከነዚህ መግለጫዎች በመነሳት ወደ አአምሮአችን የሚመጣው የመጀመሪያው ጥያቄ የአንድ ድርጅት አባላት ሆኖ ሳለ እንዲህ አይነት ጦርነት ነጋሪ መግለጫ በአደባባይ ማውጣት ላይ የደረሱት በመካከላቸው መነጋገር ቁሞአል እንዴ? የሚል ነው። በተለይም አዲፓና ኦዲፓ ህወሃትን ከጫንቃቸው ላይ አሽቀንጥረው ከጣሉና ሰፊ የሆነ የህብረተሰብ ድጋፍ ካገኙ ቦኋላ በእጃቸው ላይ የወደቀው ሥልጣን ገና በቂ የሆነ መደላድል ሳያገኝ በዋናነት የሚፈልገውን ሠላምና መረጋጋት የሚያናጋ እንዲህ አይነት መግለጫዎችን በየፊናቸው ለማውጣት እያስገደዳቸው ያለ ችግር ምንድነው ?

ይህንን ጉዳይ በግርድፉ መመርመር ብንሞክር የምናገኘው ፤
1ኛ ህወሃት ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው እንዲመቸው በአገዛዝ ዘመኑ ሁሉ በራሳቸው መተማመን የማይችሉ ፤ በእውቀታቸውና በችሎታቸው የኮሰሱና እዚህ ግባ የማይባሉትን ሰብስቦ በየድርጅቶቹ አጎሮ እንደኖረ ስለሚታወቅ እነዚህ ሰዎች አሁን በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ በከፍተኛ ፍርሃትና ጥርጣሬ ሊመለከቱት እንደሚችል መገመት ይቻላል።
2ኛ በየክልሉ ባሉት የሥልጣን ተዋረድ ያሉት አብዛኞቹ ሹመኞች ወይም የድርጅቶቹ አባላትና ካድሬዎች ቀድሞውኑ ወደየድርጅቶቹ የተቀላቀሉት ለግል ጥቅም ስለሆነ ከመሬት ዘረፋና ሽያጭ ጋር በተያያዘ ወንጀል ፤ እንዲሁም በአገር ሃብት ዘረፋና በሙስና የተነካኩ ናቸው ብሎ ማሰብ ይቻላል ። ስለሆነም ለለመዱት የኢኮኖሚና የሥልጣን ጥቅም ከለውጡ መንገድ ይልቅ ብቻል የቀድሞው ቢመለስ ካልሆነ ደግሞ የቀድሞው ሥር ዓት በዋናነት የሚያቀነቅነው የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ እምነት የበላይነት የሚያገኝበት ሁኔታ ቢፈጠር የበለጠ ዋስትና ይኖረናል የሚል ስሌት ሊኖራቸው እንደሚችል መጠርጠር ይችላል። ለዚህ ደግሞ በተለይ በሁለቱ ክልሎች ( በኦሮሚያና በአማራ) ይህንን የብሄር ማንነትን የሙጥኝ ያሉ ፖለቲካ ሃይሎች በሽ በሽ እየሆኑ ነው። ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦች ከኦዲፓና ከአደፓ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ሳይበጥሱ ከውስጥ ሆነው ለነዚህ ጽንፈኞች መሣሪያ በመሆን ከቻሉ የለውጥ ሃይሉን ማጥፋት ካልሆነ ደግሞ በማዳከም የለውጥ ሂደቱ እነርሱ ወደሚፈልጉትና የኑሮና የህይወት ዋስትናቸውን ይበልጥ ያስጠብቅልናል ወደሚሉት መንዳት መንዳት የሚጠበቅ ነው። በሁለቱም ክልሎች አሁን እየሆነ ያለው ይሄ ይመስለኛል ።

ለምክረ ሃሳብነት ቢያገለግል
1ኛ/ አዲስ አበባ በሁለቱም ጎራ ያሉ ጽንፈኞች (“ፊንፊኔን ከኛ” ና አዲስ አበባ “በረራ” ናት) እያራመዱት ያለው የጦርነት ሰላባ እንዳትሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ባለው መንገድ በእንዲህ አይነት ጦርነት የትኛውም ወገን አሸናፊ መሆን እንደማይችልና ሊመጣ ከሚችለው ቀውስ ማንም እንደማያተርፍ በጽናት መንገር ያስፈልጋል
2ኛ / ይሄ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ በኢህ አደግ አመራር ውስጥ ባሉ ጥቂት ቀናና የነቁ አገር ወዳድ ዜጎች የሚቀነቀን እንጂ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ መሠረት ያልያዘ መሆኑን በመረዳት ችግሮች ሲገጥሙ ተስፋ አለመቁረጥና የለውጥ ሃይሉን የሚያዳክም አቋም ለመያዝ አለመጣደፍ ይጠቅማል።
3ኛ / ህወሃት የመንግሥት ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የዘረጋው የዘረኝነት መዋቅር እንዲህ በአጭር ጊዜ ከሥሩ ተመንግሎ ይጠፋል ብሎ አለመጠበቅና ጊዜ እንደሚወስድ አውቆ በጽናትና በትዕግስት ከለውጥ ህይሉ ጎን በመቆም ለውጡ እንዲቀጥል ማድረግ ።
4ኛ / ጽንፈኞች ለሚያራምዱት ጥላቻ ፤ አንዱን ዘር ከፍ ሌላውን ዝቅ የማድረግ ዘመቻ ጆሮ አለመስጠት ( በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ና በነዚህ ጽንፈኞች የሚተላለፉ የሬዲዮና ቴለቪዥን ስርጭቶች ቁብ አለመስጠት )
5ኛ/ በሽግግር ዘመኑ የሚከናወኑትን ተግባራትንና ከሽግግር ጊዜ ቦኋላ መፍትሄ ማግኘት የሚገባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማወቅ ( የሽግግር ዘመኑ ዋና ተግባራት የሚሆኑት ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን ፤፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማሻሻልና ማጠናከር ፤ ወደ ግጭትና ሁከት የሚወስዱትን ቀዳዳዎች መድፈን መጣር ፤ የአገር መከላኪያ ፤ የጸጥታ፤ የደህንነትና ፖሊስ ተቋማት ከየትኛውም ፖለቲካ ድርጅቶች ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ብቻ በሚያገለግለበት መንገድ ማዋቀር ፤ የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች አላማቸውን በነጻነት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው እንዲያስተምሩ ፤ ህዝብ እንዲቀሰቅሱ ፤ እንዲያደራጁ ማስቻል ፤ ነጻ፤ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ የሚደረግበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ፤የመሳሰሉት ናቸው ። ሌሎች ከህገመንግሥቱ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ከማንነትናት ከወሰን ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትና ክፍፍል የመሳሰሉቱ ከሽግግር ዘመኑ ቦኋላ በህዝብ ተመርጦ ሥልጣን ለሚይዘው መንግሥት ለይደር መተው ያለባቸው ናቸው )
6ኛ/ ህወሃት ለ27 አመታት በአገራችን ላይ ያሰፈነው የብሄር ፖለቲካ አሁን ለገባንበት ችግርም ሆነ ከፊት ለፊታችን ለተደቀነው አደጋ ብቸኛ ምክንያት እንደሆነ በግልጽ በመወያየት ዘላዊ መፍትሄ መሻት እንድንችል ከሚለያዩን ጉዳዮች ይልቅ የሚያመሳስሉንን ፤ ከሚያጋጩን ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቡንን ፤ ከሚያጣሉን ጉዳዮች ይልቅ የሚያፋቅሩን ጉዳዮች ላይ ማተኮር ፤
7ኛ / በፖለቲካ አመለካከት እንደምንለያይ ሁሉ ለአገራችን ችግሮችም የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ልንለያይ እንደምንችል አውቀን እራሳችንና ብቸኛ መፍትሄ አመንጭ አድርገን ከመቁጠር ግብዝነትና ኋላ ቀር አስተሳሰብ መራቅ ብንችል ከፊት ለፊታችን የተከፈተውን ገደል እንደፍናለን ፤ አገራችንንም ከከፋ አደጋ እንታደጋለን ። ሁላችንም ተጠቃሚ የሚንሆነውም ያኔ ነው።
8ኛ / በተለይ በዲያስፖራ ሆነን ኢሳት ላይ ነዳጅ ለማርከፍከፍ እረፍት የምናጣ ሁሉ መርሳት የሌለብን አያት ቅድመ አያቶቻችን ባላቀኑት የተሰደድንባቸው የሰሜን አሜሪካ ፤ አውሮጳና አውስትራሊያ ከአገሩ ዜጎች እኩል ተንደላቀን እየኖርን አያት ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት የህይወትና የአጥንት መስዋዕትነት በተገነባቺው አገራችን የሚኖሩ ወገኖቻችን በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው እንዳይኖሩ የምንረጨውን መርዝ ማቆም አለብን። በቆዳ ቀለም ጭምር የማይመስሉን በሰውነታችን እውቅና ሰጥተውን በነጻነት እየኖርን በቀለም ቀርቶ በባህልና በስነልቦና የሚመሳሰለውን አንድ ህዝብ እርስ በርስ በማጋጨት የሚገኘው ጥቅም ፋዳው እስከምን ድረስ እንደሆነ እራሳችንን እንጠይቅ። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት! ማንም ለማንም የመኖሪያና የሥራ ቦታ ሊመርጥ መብት የለውም ፤ ዘመኑ የድንቁርና ሳይሆን የሥልጣኔ ነው። ኦቦ ለማ መገርሳ በአንድ ወቅት እንደተናገረው የሰው ነፍስ ብሄር የላትም !
አትረብሹን ተደናቁራችሁ አታደናቁሩን ! በሥራ አጥነት የወላጆቹ ሸክም የሆነን ወጣት የሚጠቅመው በህበረትና በአንድነት ድህነትን እንዴት ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል የአደጉ አገሮችን ተሞከሮ ማስተማር እንጂ ጎዳና ላይ ወጥቶ መንገድ በመዝጋት ለራሱ ጥቅም የሚውል አገልግሎት እንዲያውክና ድህነት እንዲያባብስ መሆን የለበትም! የኛን Ego ለማሟላት ይህ ደሃ ህዝብ በተለይም የወጣት ዕድሜውን በችግር እየገፋ ያለው ለስንት አመት ድህነት ውስጥ ይማቅቅ? ኤረ በፈጠራችሁ እንለመን
አላህ አንቆ ከያዘን ድንቁርናና እብደት ይሰውረን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.