ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባህር-ዳር ለአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ መዝጊያ ዝግጅት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት {ንግግር}

ተስተካክሎ የቀረበ ትክክለኛ የፅሁፍ ቅጂ
~~~~~<>~~~~~

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ
ክቡር ዶ/ር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
የተከበራችሁ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት
ክቡራትና ክቡራን

በዘመን ሰንሰለት የአማራ ህዝብ ከሌሎች እህቶቹ እና ወንድሞቹ ጋር በመሆን በሃገር ህልውና እና ግንባታ ሂደት – በሰላሙ ጊዜ የልማት አቅም፤ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ወታደር በመሆን ከፍ ያለ የአርበኝነት ታሪክ የሰራ ህዝብ ነው፡፡

የአማራ ህዝብ ሲሻው ድንጋይ አናግሮ፤ ሲሻው ዋሻ ፈልፍሎ፤ ሲሻው ድንጋይ ጠርቦ፤ ሲሻው እንጨት አለዝቦ፤. . . በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ ዛሬ ድረስ የሚደነቁት የኪነ-ህንፃ በረከቶቹ የታሪክ ከፍታውን ማሳያ አብነቶች ናቸው፡፡

በአንፃሩ በዘመኑ የፖለቲካው ገበያ በሚያስተናግዳቸው እኩይ ውላጅ አስተሳሰቦች እና ስንኩል ትርክቶች ምክንያት በተደጋጋሚ የሚደርስበትን የከረረ ስነ-ልቦናዊ ድቁሳት፤ “ሁሉም ያልፋል!” ፤ “ነገም ሌላ ቀን ነው!” በሚል ቀና የአስተሳሰብ ሰሪት ውስጥ ሆኖ መራር ጊዜያትን በትዕግስት ያለፈ አስተዋይ ህዝብ ነው፡፡

የሰው ልጅ ዳና ባረፈበት ሁሉ የሚጎሉ እና የሚሟሉ፤ የሚያስደስቱ እና የማያስከፉ፤ የሚጠፉ እና የሚለሙ ጉዳዮች መኖራቸው ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ተፈጥሯዊ ሃቁን ወደ ጎን በመተው ለአንድ ህዝብ . . . “የታሪክ ዕዳ ከፋይ፤ ተዋረዳዊ በዳይ” አድርጎ መሳል ተገቢነት የለውም፡፡

እንደሌላው ዓለም ሁሉ በየዘመኑ በሃገር ግንባታ ሂደት የሚፈጠሩ ስኬቶች እና ጉድለቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከዘመኑ ታሪክ ሰሪዎች የሚጠበቀው ስህቶተችን በማረም፤ ስኬቶችን እያስፋፉ ለትውልድ ተሸጋሪ ማድረግ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ
ክቡራትና ክቡራን

በዘመናችን የተፈጠሩ ችግሮችን አሟልተን ሳንፈታ፤ ነበሩ በምንላቸው የኋላ ችግሮቻችን ላይ ታጥረን መሳሳባችን ለተቀረው ዓለም የሚያስተላለፈው መልዕክት እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡

ዓለም “ኋላ-ቀርነትን” ብቻ ሳይሆን ወደ “ኋላ-መቅረትን” ፈፅሞ በማይፈቅድበት አስተሳሰብ እየተመራ በሚገኝበት ዘመን ላይ፤ ወደፊት አስፈንጥሮ ሊያሳፍረን በሚችለው አስተሳሰብ እና ተግባር ዙሪያ ማጥበቅ ይገባናል፡፡

አሁን የተጀመረው የለውጥ ምዕራፍ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ከመሆኑም በላይ . . . ዳር እስከ ዳር በዜጎቻችን ዘንድ ትልቅ መነቃቃት እንዲፈጠር እና ሰፊ ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል፡፡
የነፃነት፣ የእኩልነት እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ዕውን መሆኑን በመገንዘብ የአማራ ክልል ህዝብ ዳር እስከ ዳር በግንባር ቀደምትነት በሚባል ደረጃ ድጋፉን ሰጥቶናል፡፡ የክልላችን ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ለለውጡ ባሳየው ድጋፍ ከልብ አኩርቶናል፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ወራቶች ሁሉም በሚጠብቀው ደረጃ ያሟላ ነው ባይባልም፤ በርካታ ዓለምን ያስደመሙ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የዛኑ ያህል ለውጡን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ገጥመዋል፡፡

እንዲህ አይነት የለውጡ ጉዞ በስኬት እና በፈተና ታጅቦ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ለውጡ ያስገኛቸውን ድሎች አለማድነቅ ንፉግነት ሲሆን፤ በለውጡ ስኬታማ ጉዞ መዘናጋት ደግሞ የዋህነት በመሆኑ. . . ሁለቱም ጫፎች አስታርቆ በአስተውሎት እና በጥንቃቄ መራመድ ይጠይቃል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ
ክቡራትና ክቡራን

በለውጡ ሂደት የተለያየ አተያይ ያላቸው ሃይሎች በየፈርጁ ይደመጣሉ፤ “ፈፅሞ ለውጥ የለም!” ወይም “ያለኛ የትም አይደርስም!” የሚሉ አሉ፡፡ በሚታዩ ተግዳሮቶች ለውጡ እንዳይቀለበስ የሚሰጉ እና የሚሰስቱም አሉ፡፡ አንዳንዱ ዘመኑን በግል ቁመቱ ልክ ሰፍቶ . . . “ሲጎድል ግጭት ጠማቂ – ሲሞላ መፍትሄ አፍላቂ” ሆኖ የለውጥ አባዎራነቱን ለብቻው ተከናንቧል፡፡

በዚህ ዙሪያ የሚታዩ የተሳሳቱ አዝማሚያዎች እና የጥርጣሬ ምንጮችን ከስሩ ነቅሎ ማስወገድ፤ “እኔ ያልኩት ካልሆነ” የሚሉ ግትር አቋሞችን እና ብልጣብልጥ አካሄዶችን ደግሞ መግራት እና ማረም ይጠይቃል፡፡ ዋናው ነገር የለውጡን ቀጣይነት ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

የአማራ ህዝብ ክፉ እና ደጉን አልፎ ከደረሰበት የለውጥ ምዕራፍ . . . ተስፋው እንዲከስም፤ ሰላሙ እንዲጠፋ፤ ዕድገቱ እንዲኮላሽ እንዲሁም የግጭት አምባ ሆኖ እንዲዘልቅ ዛሬም የጥፋት ድግሶች በውስጥ እና በውጭ ከበውት ይገኛሉ፡፡

ይህንንም እንደሰሜን ተራሮች ከፍ ብሎ፤ እንደ ጣና እና ጊዮን አባይ ተረጋግቶ፤ እንደላስታ ዓለት ፅኑዕ ሆኖ፤. . . ከሚመጥነው ጋር ብቻ ታግሎ፤ የሚመጥን ውጤት እያስመዘገበ መጓዝ ይጠይቃል፡፡

የትግላችን ከፍታ የሚለካው – በትንንሽ ተግባራት፤ በጊዜያዊ ብሶቶች እና ስሜቶች ሳይሆን በመርህ ላይ ቆመን የክልላችን እና የሃገራችንን ክብር ለማስጠበቅ በሚያስችለን የአሸናፊነት እርካብ ላይ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ
ክቡራትና ክቡራን

በዚህ ዘመን. . . በማናቆር ትርክት ተብትቦ ታፍራ እና ተከብራ ለዘመናት የፀናችውን ታላቅ ሃገር ድንክ ሆና እንድትቀር የሚያደርግ ጨካኝ አሰላለፍ እና የዘረኝነት ዘውግ ይስተዋላል፡፡ ይህንን በጽናት መታገል የወቅቱ ተልዕኳችን ነው፡፡

በብዝሃነት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያ . . . “ብዝሃነትን ጌጥ – አንድነትን ሃብት” አደርጎ የሚያፀናትን ስርዓት እንከኖቹን እና ህፀፆቹን አርሞ የማስቀጠል ብልሃት ይጠይቃል፡፡

የሃገር ግንባታችን ያስቆጠረውን ዕድሜ ያህል ያላለቁ የቤት ስራዎችን በፍጥነት እያቃለልን፤ ሁሉም በጫማው ቁጥር ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፍትሃዊ ስርዓት ለመገንባት የአማራ ክልል ህዝብ ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል፤ ደግሞም ይጠበቃል፡፡

አዲስ አበባን አስመልክቶ የተለያዩ አተያዮች ይደመጣሉ፡፡ አዲስ አበባ ሁሉም ነዋሪዎች በእኩልነት የሚጠቀሙባት እና የሚበለፅጉባት የጋራ መዲናችን ናት፡፡ የከተማዋ ዕድገት ማንንም ሳይገፋ እና ሳይጎዳ፤ ሁሉንም ሊጠቅም በሚችል መልኩ መሆን ይገባዋል፡፡

ከተማዋ ማንም የተለየ ባለቤትነት ስሜት እንደፈለገ የሚያንፀባርቅበት፤ አንዱን ባለቤት ሌላውን ባይተዋር የሚያደርግበት መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ጋር የሚነሱ ጉዳዮች ካሉ ህጎችን መሰረት አድርጎ በጋራ ተወያይቶ መፍታት ይገባል፡፡

በከተማዋ ማደግ እና መስፋፋት ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዝርዝር አጥንቶ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ማድረግ ሃላፊነታችንም – ግዴታችንም ነው፡፡ ይህ ልምድ በሌሎች እያደጉ ባሉ ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በማይጠቅሙ አጀንዳዎች ተገፋፍቶ እና ተደፋፍቶ አሸናፊነትን ከመመኘት ይልቅ፤ ለጋራ በሚጠቅሙን ጉዳዮች ዙሪያ ተቃቅፎ እና ተደጋግፎ ወፍራም ድል የሚሸመትበትን ወርቃማ አጋጣሚ ከወገኖቻችን በጋር እየሮጥን፤ በጋራ ድል እንድንጎናፀፍ ጥሪዬን እያቀረብኩ፤ ዘመኑ የሚጠይቀንን የጋራ ሩጫ በስኬት ለመወጣት በትንንሽ አጀንዳዎች ሳንጠመድ፤ በዕለት ብሶቶችና ስሜቶች ሳንወጠር፤ ባለፈ ታሪክ ውስጥ ሳንሰነከር . . . ይህን ታላቅ ህዝብ እና ታላቅ ሃገር የሚመጥን ታሪክ ሰርተን እንድናልፍ አደራ እላለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!
~~<>~~~
የካቲት 29፣ 2011 ዓ.ም
ባህር-ዳር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.