የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት 157 መንገደኞችና አውሮፕላኑ ሠራተኞች ዜግነታቸው ተለይቷል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ስለተከሰከሰው ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው አውሮፕላኑን ሲያበር የነበረው ከ8 ሺህ ሰአታት በላይ የማብረር ልምድ ያለውና ጥሩ የበረራ ሪከርድ የነበረው ካፒቴን ያሬድ ሙሉጌታ ሲሆን ግማሽ ኢትዮጵያዊና በግማሽ ኬኒያዊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሀመድ ኑር የሚባል ከ200 ሰአት በላይ የበረራ ልምድ ያለው አብራሪ ነበር፡፡

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ አውሮፕላኑ ከተገዛ ገና 4 ወራትን ያስቆጠረና ምንም አይነች ችግር ያልነበረው ንፁህ አውሮፕላን ነበር፡፡

በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ የነበሩ 149 መንገደኞች እና 8 የበረራ አስተናባሪዎች ዜግነታቸው ተለይቷል፡፡ በአደጋው 8 አውሮፕላኑ ሠራተኞችን ጨምሮ 18 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል።

በአውሮፕላኑ ላይ 32 ኬኒያውያን፣18 ካናዳዊያን፣ 9 ኢትዮጵያውያን፣ 8 ጣልያውያን፣ 8 ቻይናዊያን፣ 8 አሜሪካውያን፣ 7 እንግሊዛውያን፣ 7 ፈረንሳውያን፣ 6 ግብፃውያን፣ 5 ጀርመናውያን ሲሆኑ ከ5 የኔዘርላንዳውያን ውስጥ 4ቱ የተባበሩት መንግስታት ፓስፖት የያዙ መንገደኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡

4 ህንዳውያን፣ 4 የስሎቫኪያ ዜጎች፣ 3 የኦስትሪያ ዜጎች፣ 3 ስዊድናውያን፣ 3 የራሻውያን፣ 2 የሞሮኮ ዜጎች፣ 2 የስፔናውያን፣ 2 ፖላንዳውያን፣ 2 እስራኤላውያን፣ 1 የቤልጄማዊ፣ 1 ኢንዶነዌዥያዊ፣ 1 ኡጋንዳዊ፣ 1 የመናዊ፣ 1 ሱዳናዊ፣ 1 ሰርቢያዊ፣ 1 ቶጓዊ፣ 1 ኔፓል፣ 1 ናይጄሪያዊ፣ 1 ሞዛንቢካዊ ዜጋ፣ 1 ሩዋንዳዊ፣ 1 ሶማሊያዊ፣ 1 ኖርዌያዊ፣ 1 የጅቡቲ ዜጋ፣ 1 አየርላንዳዊ እና 1 የሳኡዲ ዜጋ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮቶኮል ሻሀድ አብዲሻኩር በአውሮፕላን አደጋው ከሞቱት አንዱ መሆኑን ራዲዮ ዳልሰን ተብሎ የሚጠራው የሶማሊያ የግል ሚዲያ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ የስሎቫኪያ የፓርላማ አባል ሚስቱንና ልጁን አጥቷል። የስሎቫክ ናሺናል ፓርቲ አባል የሆነው የፓርላማ አባል አንቶን ሄርንኮ ፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው በአደጋው እንዳጡ ገልፀዋል።

የምግብና መስተንግዶ ድርጅት ታማሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆናታን ሴክስ በአደጋው ከሞቱት መካከል አንዱ ናቸው። በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ብዙ ቁጥር ያላቸው ሬስቶራንቶች ባለቤት የሆነው ይህ ድርጅት የህልፈታቸውን ዜና ያሳወቀው በፌስቡክ ገፁ ነው።

በጆሞ ኬንያታ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቤተሰብ፣ ዘመድና ወዳጆቻቸውን እየጠበቁ ለነበሩም የህልፈታቸው ዜና ተነግሯቸዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ የሶስት ሟቾችን በትዊተር ገፁ ላይ ያሰፈረ ሲሆን ከቤተሰቦቻቸውም ጋር ለመገናኘት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።

የአልጀዚራ ጋዜጠኛ በትዊተር ገጿ እንዳሰፈረችውም የተባበሩት መንግስታት መልእክተኞች ከሟቾቹ መካከል ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ስብሰባ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ለመካፈል ሲጓዙ እንደነበር ተገልጿል። በዚህ ስብሰባ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በማትያስ የማነ/EBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.