አማርኛ ቋንቋ የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ እንደሆነ ጥያቄ ቀረበ

ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሁለተኛ ደረጃና የመስናዶ ትምህርታቸውን ጨርሰው ለዩኒቨርሲቲ ብቁ ሆነው የሚገቡ ተማሪዎች፣ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን በቅጡ የማያውቁ እየሆኑና ቁጥራቹውም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ወደፊት ሊፈጥረው የሚችለውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ምን እያከናወነ እንደሆነ ተጠየቀ፡፡

ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ባለፈው ማክሰኞ ለፓርላማው ካቀረቡ በኋላ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ማብራርያ የሚሹ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡

ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ከላይ የተገለጸው አማርኛ ቋንቋ የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥር መጨመር ሊፈጥረው የሚችለውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ሚኒስቴሩ ምን እያደረገ እንደሆነ፣ ወይም ምን ዓይነት መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚችል የኢሕአዴግ አባል የሆኑት የፓርላማ ተመራጭ አቶ መሐመድ አብዶሽ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡

አቶ መሐመድ በፓርላማው የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ውስጥ አንድ የፌዴራል ሥርዓቱ ቋንቋ መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅት በመላ አገሪቱ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ተማሪዎቹ ያረጋገጡት ታች ያለው ተማሪ አማርኛ ቋንቋ መናገር አለመቻሉን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ መጥተውም በአማርኛ ቋንቋ ፈጽሞ መግባባት አለመቻላቸውን ጠቅሰው ጥያቄያቸውን በሚያደረጁበት ወቅት፣ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ያሰሙት መጠነኛ ማጉረምረም ንግግራቸውን ለአፍታ ያህል ገታ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡

ይሁን አንጂ አቶ መሐመድ ወደ ጥያቄያቸው በመመለስ ለችግሩ ትኩረት መስጠት ያለበት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች አብራርተዋል፡፡

‹‹በመንግሥት የረዥም ጊዜ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ብሔራዊ ቋንቋን ማወቅና በቋንቋው ማግባባት መቻል ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ወጣቶች የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገር ግንባታ ሥራ በሚገቡበት ወቅት ቢያንስ የፌዴራል ቋንቋውን መቻል አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በእርግጥ የቀድሞ ሥርዓቶች በየማኅበረሰቡ ላይ ያደረሱት የመብትና የማንነት ረገጣ ተፅዕኖ ውጤት ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት የፓርላማው አባል፣ በክረምቱ ውይይት ወቅት ተማሪዎቹ እንዳስረዱት በየክልላቸው ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ አማርኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጣቸው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹አሥራ ሁለት ዓመት የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ተምረዋል፡፡ ነገር ግን ምንም አያውቁም፡፡ ታዲያ ይህ ወደፊት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በምናደርገው ጥረት ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም? ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሠራ ነው? ምንስ አስቧል?›› የሚል ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ለቀረበው ጥያቄ ምለሽ የሰጡት ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዳለው ሁሉ ክልሎችም የራሳቸውን ቋንቋ መወሰን እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ውስጥ ያሉ መስተጋብሮችን በተሟላ መንገድ አስተሳስሮ መሄድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት በየትኞቹ አካባቢ በስፋት የሚታይ ችግር ነው? ችግሩ ካለስ እንዴት ነው የሚፈታው? የሚባለውን በራሱ መድረክ ስናይ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ሊደረግባቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ችግሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ካምፖሶች የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ በመጨረሻዎቹ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በአማርኛ መግባባት ችለው የሚወጡ በመሆናቸው ለችግሩ እስከዛሬ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተውት እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡

Amharic Flag

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.