ቦይንግ ኩባንያ እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋም ሲውተረተር የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አውሮፕላን መርማሪዎች ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 አውሮፕላን የመረጃ ማጠራቀሚያ ሳጥን ግምገማ በፓሪስ የጀመሩት መርማሪዎች ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አንድ ሒደቱን በቅርብ የሚያውቁ የመረጃ ምንጭ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያው 737 ማክስ አውሮፕላን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ለመከስከስ ያበቃውን ምክንያት ለማወቅ ወራት የሚፈጅ ቢሆንም አምራቹ ቦይንግ ግን የከፋ ጫና ውስጥ ገብቷል። በተለይ በኢትዮጵያው እና ከዚህ ቀደም በኢንዶኔዥያ በተመሳሳይ አውሮፕላን ላይ በተከሰተው አደጋ መካከል “ግልጽ መመሳሰሎች” መኖራቸውን የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ምኒስትር እና የፈረንሳይ የበረራ ደኅንነት ምርመራ ባለሥልጣን ካረጋገጡ በኋላ ቦይንግ 737 ማክስ እንዴት የደኅንነት ማረጋገጫ አገኘ የሚለው ጥያቄ በርትቷል።
ከጃካርታ አውሮፕላን ማረፊያ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የተከሰከሰው የላየን አየር መንገድ አውሮፕላን እንደ ኢትዮጵያው ሁሉ 737 ማክስ 8 ነበር።

የካናዳ የትራንስፖርት ምኒስትር አገራቸው ለ737 ማክስ አውሮፕላን የሰጠችውን የደኅንነት ማረጋገጫ እንደገና እያጤነች መሆኑን መናገራቸው በቦይንግ ኩባንያ ላይ ጫናውን አበርትቶታል። ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሲያትል ታይምስ ጋዜጦች ቦይንግ ለአውሮፕላኑ የደኅንነት ማረጋገጫ ለማግኘት ያለፈበትን ሒደት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ዘገባዎች አስነብበዋል። ሲያትል ታይምስ የአሜሪካ የበረራ አስተዳደር ባለሥልጣናት የ737 ማክስ አውሮፕላንን ደኅንነት የመፈተሽ ኃላፊነታቸውን መልሰው ለቦይንግ ሰጥተዋል ብሏል። ቦይንግ አውሮፕላኑ የበረራ ደኅንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ያሳወቀበት ትንታኔም ጉድለቶች እንዳሉበት ይኸው ጋዜጣ ዘግቧል።

የኢትዮጵያው አደጋ ከተከሰተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ማብራሪያ የሰጡት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሞለንበርግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው ለኩባንያቸው ስም እና ለሚከተለውን አሰራር ጥብቅና ቆመዋል። “በማንኛውም ምክንያት አደጋ ሲፈጠር ያለማቋረጥ ለምን እንደተከሰተ ለማወቅ ትኩረት እናደርጋለን” ያሉት ሞለንበርግ ምርመራው እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል። የቦይንግ ባለሙያዎች ለመርማሪዎች ቴክኒካዊ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ሁለቱን አውሮፕላኖች ለመከስከስ ሳያበቃቸው አይቀርም የተባለውን የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ተሻሽሎ በቅርቡ ሥራ ላይ ይውላል ያሉት ሞለንበርግ የኩባንያው ባለሙያዎች በሚያመርቷቸው አውሮፕላኖች ጥራት እና ደኅነት እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
(ፎቶ፦ ቦይንግ ኩባንያ)

DW

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.