አቶ በቀለ ገርባ ምን ነካው? (ጌታቸው ሽፈራው)

አቶ በቀለን ምን ነካው?

አቶ በቀለን የማውቀው እስር ቤት ነው። እስር ቤት ውስጥ የተከበረ ስብዕና የነበረው ሰው ነው። የኦሮሞ ልጆች ጋር ሰብሰብ ብሎ እያወራ ኦሮምኛ የማይችል ሰው ሲጨመር “አሁን ወሬውን በአማርኛ አድርጉት፣ ኦሮምኛ አይሰማም” ሲል አስታውሳለሁ። እኔም ገጥሞኛል። ከአምቦ ወጣቶች ባልተናነሰ ውሎው ከኤርትራ ከተመለሱ የአርማጭሆ ልጆች ጋር እንደነበር አውቃለሁ። አንዳንዶቹ ስሙን አንስተው አይጠግቡም ነበር። ለአስር ቀን የርሃብ አድማ አድርጎ በአቶ በቀለ ውትወታ ነፍሱ የተረፈ ሰው አሁንም ድረስ ስለ አቶ በቀለ ያነሳል። አቶ በቀለ በእስር ቤት እያለ ትሁት ሰው ይመስል ነበር። አንዳንድ ወጣቶች ፅንፈኝነት ሲያበዙ የሚገስፃቸው አቶ በቀለ ነበር። አስታውሳለሁ አንድ ቀን። ኬንያና ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ ነበራቸው። ብዙ ወጣቶች ኬንያ ስታስገባ ይጮሃሉ። ቀሪው ወጣት በእነዚህ ልጆች ተናደደና ወደ ንትርክ ተገባ። በዚህ ወቅት አቶ በቀለ በኦሮሞ ወጣቶች ላይ የጮኸባቸውና ጩኸት አስታውሳለሁ። ብዙዎቹ አፍረው ወደየ ክፍላቸው ገብተዋል። ሌላም ጊዜ ፅንፍ ሲይዙ የሚቆጣቸው አቶ በቀለ ነበር።

በሌላ ጊዜ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ብዙ ጉዳት ይደርስባቸዋል። በምርመራ ወቅት። አንድ አማራጭ አመጣን። እንደ አጋጣሚ ይህን አማራጭ ያመጣነው በግንቦት 7 ተጠርጥረን የታሰርን ነበርን። አማራጩ የርሃብ አድማ ነበር። ወጣቶቹ እመኑ የሚባሉትን ክደው ሲቀጠቀጡ ሊሞቱ ሆነ። ስለዚህ የርሃብ አድማ አድርገን ይህን ድብደባ ማስቆም ነበረብን። ከዛ በፊትም አድርገነዋል። ድብደባውን ከማስቆም ባሻገር በጭላንጭል በምትወጣው መረጃ ሕዝብ የሚሆነውን እንዲያውቅልን ነበር።

በ3ኛ ደረጃ ደግሞ ምንም እንኳ በፍርድ ቤት እምነት ባይኖረንም ተገደው ለሚያምኑ ልጆች ምስክርነት ለመስጠት ይመቸናል በሚል ነው። ፍርድ ቤት ላይ ስንመሰክርላቸው የርሃብ አድማው እንደ አንድ የጊዜ ማጣቀሻና ምክንያት ይሆናል፣ በርሃብ አድማው ወቅት የተሰሩ ዜናዎች ካሉም የሰነድ ማስረጃ ይሆናል በሚል አስልተን ነበር። ታዲያ የመጀመርያው ተቃውሞ ከአንድ የኦፌኮ አመራር መጣ። “የግንቦት 7 የርሃብ አድማ ነው” ብሎ የርሃብ አድማ እንዳይደረግ መቀስቀስ ጀመረ። ይህን የርሃብ አድማ ጥሪ የምናስተላልፈው ለሽንት በምንወጣበት ወቅት ከፖሊስ እየተደበቅን በተዘጉት ቤቶች በር እያንሾካሾክንና በምልክት ጭምር ነበር። በወቅቱ አቶ በቀለ ከአብዛኛው እስረኛ ተነጥሎ ታስሮ ነበር። መልዕክቱን አድርሰነው “ይህማ የተቀደሰ ሀሳብ ነው። ቀን ቆርጣችሁ አሳውቁኝ” ከማለት ባሻገር በዛኛው አመራር አመለካከት በፍፁም እንደማይስማማ ነበር የሰማነው። በእርግጥ በመጀመርያው እስሩ ወቅት አቶ በቀለን የሚወቅሱት ሰዎች አጋጥመውኛል። በ2008 ዓም ግን የተለየ ሆኖ ነበር ያገኘሁት። አሁን ከሚባለው አንፃር ቢፃፉ የተጋነኑ መምሰላቸው አይቀርምና ባይፃፉ ይሻላል።

ትናንት ስለ ኦሮምኛ ተናገረው የተባለውን እዚህ ፌስቡክ ላይ አይቼ ገረመኝ። በእርግጥ ዛሬ አይደለም የጀመረው። ጋሽ በቄ እስር ቤት ሲያሳየን የነበረው ትሁትነት የምር አልነበረም ማለት ነው? በኢሳት ላይ የሰጠውን አስተያየትና ሌሎቹም አስገራሚዎች ናቸው።

1 COMMENT

  1. ውድ ጌታቸው፣
    “አቶ በቀለን ምን ነካው?” ኢሳት ላይ ያለው ምን ነበር? በደፈናውማ አንተም ራስህን አታውቅም ማለት ነው!
    ሌላ ማወቅ ያለብህ (አታውቅ እንደ ሆነ) ኢሳት፣ ግንቦት 7 እና እስክንድር ነጋ አንድ ናቸው።
    አቶ በቀለ ከእነርሱ አሳብ ጋር አልተስማማ ይሆናላ! እስቲ አስረዳን፣ ዳር ዳር አትበል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.