“ሙያ በልብ ኑው።” በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ሐሰብን  ለመግለጽ

ዳግመኛ ገብቼ በልሜ  ተማሪ ቤት
እማር ይመስለኛል ንባብና ጽሕፈት፡፡
ድርሰት ነበርና የያዝሁት ሥራዬ
የኔታ ምናልባት ያስረዱኛል ብዬ
ብዬ ጠየቅኋቸው
—እንዴት አድርጎ ነው ሐሳብ አስተያየት
የሚገልጸው ሰው?
የኔታ መለሱ
—ይህ አስቸጋሪ ነው፡፡
ከመነፅር ውጪ እኔን አግድም አይተው
ተረት ስማኝ አሉ፡፡
 ባአንድ ቤት ሲወለድ ልጅ ከነቃጭሉ
ደስታ ያድርጋል ቤተሰብ በሙሉ፡፡
ገና ወር ሳይሞላው ልጁን እያወጡ
እዩልን ይላሉ ዕንግዶች ሲመጡ፡፡
ጥቂት ውዳሴና ምስጋና ሽተው
ያን የመሰለ ልጅ በማፍራታቸው፡፡
አንዱ ከእንግዶቹ ልጁን ካዩት መሀል
“ የህ ልጅ ከበርቴ ነው የሚሆነው“ ይላል
በዚህም ቤተሰብ ያመሰግነዋል፡፡
አንዱ “ይህ ወንድ ልጅ ታለቅ ባለ ሥልጣን
ታላቅ ሹም ይሆናል“ ሲል ያሰማል ቃሉን
ባዩም ከመስጋና ያገኛል ድርሻውን፡፡
አንዱ “ይህ ልጅ “ይላል “ አይቀርም መሞቱ ።“
ዱላ ያጠግቡታል ይህን በማለቱ፡፡
ልጁ ሰው ነውና እርግጥ ነው ይሞታል፡፡
ትልቅ ሹም ይሆናል ከበርቴ ይሆናል
ማለት ግና ሐሰት ለመሆን ይችላል፡፡
ሆኖም ሲያስመሰግን ሲያስወድድ ሐሰት
የማይቀረውን ሞት አይቀርም ማለት
የበትር መዓት ነው ያተረፈው ምርት፡፡
አልፈልግም እኔ ውሸት መናገር
አያምረኝም ደግሞ ዱላና በትር፡፡
ጠባይህ ከሆነ እነደዘህ እንደልከው
“ሃሃሃ !አያችሁት ያንን ልጅ?“ ማለት ነው።
ማለት ነው_ “በዝጌሃር ! ሆ ሆ!ሂ ሂ!ሃ ሃ!
ሆ ሆ!ሆ ሆ ሆ!
ሄ ሄ ሄ ! ሃ ሃ ሃ ! “
     (ግጥሙን   ” አብዬ “መንግስቱ  ለማ ከቻይናው ደራሲ ከሉሕሡን ሃሰቡን ወስዶ  የጻፈው ነው።)……
……
         በሆሆ ! በሃሃሃ! በሄሄሄ! እንደዋዛ የሚያልፍ ዓለም ነው ፤ይህ ዓለም፡፡
ይህ መጠሪያ ሥሙ መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ የተባለ ሰው ሃሳብ ነው።……………
የህ ዓለም በከንቱ ውዳሴ የተሞላ ነው፡፡ከእውነታ ይበልጥ ተረት ተረት የሰውን  ማህበራዊ ኑሮ ጠፍንጎ ይዞታል፡፡ ሰው የኔ ነው የሚለውን ነገር ሁሉ እንድታጣጥልበት ከቶም አይፈልግም፡፡በተለይ  ከጥበብ የራቀ ሰው፣ባለው ቁሳዊ ሀብት ራሱን ከማህበረሰቡ የኑሮ ደረጃ አግዝፎ  የሚያይ ሰው ከሆነ ፣ሥለ እንከኑ አንዳች ብታወራ አይታገስህም፡፡(በዚህ ዓለም ሚዛናዊና ዲንጋይ ሌላ ሰው ላይ ከመወርወሩ በፊት፣እኔ ከሱ የባስኩ ሐጥያተኛ ነኝ። በማለት ከመወርወር የሚቆጠብ እምብዛም አይገኝም።)
በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ አብዛኛው ሰው ከራሱ ጋር ጭምር የተጣላ መሆኑን፣ትዕግስት አልባ አኗኗሩ ይመሰክራል፡፡በአሥተውሎት ሲጤን በአደባባይ የሚያወራውና በግሉ የሚኖረው ኑሮ ጫማና ኮፍያ  ሆኖ ይገኛል፡፡
ብዙው ሰው ህይወቱ ጫማና ኮፍያ መሆኑን ህሊናው ያውቃል፡፡ኑሮው፣በውሸት የወዛ እንደሆነ ይገነዘባል።እኩሌታው ደግሞ፣ያለማወቁን እንኳ ሥለማያውቅ ፣አለማወቁን በመገንዘብ፣ ከመናገር ይልቅ ማዳመጥን የመረጠውን ደጋግሞ ይተቻል።የሱ ቢጤዎችና፣ከዕውቀት የራቁም ሊቅ ያደርጉታል።እውነትን  በውሸት ና በተረታ ተረት  ተክቶ ዘመኑን ይጨርሳል።
ሰው ሁሌም እውነትን እነደሸሻት እና ተረት ተረት ውስጥ ተደብቆ እንደኖረ ነው፡፡ እውነትን ተከትሎ ሰው ልኑር ቢል ፣ዓለምን በአሁኑ ገፅታዋ  አናገኛትም ነበር።
ሰው ፣ፖለቲካን፣ኃይማኖትን፣ ባስ ሲል ዘሩን፣ጎሳውን ፣በማመካኘት፣ ለግሉ ብልፅግና ሲል  አምሳያውን ያለርህራሄ “እሱ እነደሚለው ” እያሶገደ የሚኖር ነው፡፡
ሰው እኩይ ድርጊቱን ፣በልቡ ሰውሮ ፣ሌላውን የሚያሞኝ  “የአንደበት ብቻ የሆነ ሃሳብ  ” በይፋ የሚነገር ፣በተግባር ሲፈተሽ ፖለቲካዊ፣ኃይማኖታዊ እና ዘራዊ ሰበብ በመፍጠር በሥሩ መሰሎቹን አሰባስቦ ፣ ፣እንደ ኔሮ. ሂትለር፣ሞሶሎኒ፣ስታሊን፣ፒኖቼ ፣(የአፍሪካ  አምባገነን መሪዎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡) በሚሊዮን የሚቀጠሩ ሰዎችን ፣እነደ እንስሳ በመቁጠር ፣በአብዮት፣ በፈጣሪ ፣ እና ተጨቋኝ በሚባለው ህዝብ ሥም ፣በግልፅ በአደባባይ ሰውን እየሳቀ ይገድላል፡፡
ይህን እኩይ ድርጊት ለራሱና ለመሰሎቹ ፣ምቾትና ድሎት እነደፈፀመ እንዳይታወቅበትም በራሱ ታሪክ ፀሐፊዎች አማከኝነት ሥለትክክለኛ  እና የፅድቅ ጦርነቱ ይፅፈል።ያፅፋል።በከያንያኑም ይዘመርለታል፡፡ ጦርነቱ ምክናያታዊ እንዳልሆነ፣ሰውን ያለህግ  ያውም ምንም ወንጅል ሳይሰራ ፣ሥልጣንን መከታ አድርጎ መግደል ራሱ ወንጀል ነው ፡፡ብሎ በድፍረት የሚናገር የራስ ሰው ካለም፣በገዛ አንገት ውስጥ ሸምቆቆውን ማስገባት እንደሆነ ፣የትሮትስኪና የአጥናፉ አባተ አሟሟት የመሰክርልናል፡፡ያለፍርድ ከገደሏቸው በኋላ “አብዮት ልጆቿን ትበላለች ።” አሉ፡፡
እውነቱ ይኸው ነው፡፡አምባገነናዊ መንግስታት፣ጥቂት ጥቂት እውነት የሚናገሩ ተፎካካሪዎቻቸውን አይወዷቸውም።ሥልጣን ላጎናፀፋቸው የመግደል፣የማሰር እና ያለከልካይ የመበዝበዝ  ገደብ አልባ መብታቸው ሲሉ ብቻ ፣ከአብላጫው ህዝብ  ጋር የሚያጋጭ ሐሰተኛ ታርጋ ይለጥፉባቸዋል፡፡………………አድሃሪ፣ቀልባሽ፣ቀኝመንገደኛ፣ፊውዳል፣አናርኪ፣ትሮትስኪ፣ነፍጠኛ፣ትህምከተኛ፣አሸባሪ፣አክራሪ፣ፀረ ሰላም፣ፀረ ዴሞከራሲ፣ፀረ ብሄር ብሄረሰብ፣ፀረ ልማት ወዘተ፡፡
 መቼም ይህንን በእዝን ልቡናችሁ ዛሬ ላይ የምታስታውሱ፣ሆ ሆ!ሃ ሃ ሃ !ሄ ሄ ሄ !…ማለታችሁ አይቀርም፡፡በህሊናችሁ ያላችሁ ሰዎች፡ልብ እንድትሉ እምፈልገው ፣ይህ አውነት በትንሹም ቢሆን ዛሬም እንዳለ ነው፡፡ነገ ደግሞ ሊበዛ የማይችልበት ምንም መንገድ  እንዳሌለም አትሳቱ፡፡  …
ሥለዚህም በመሥራቤታችሁ፣በህዝብ ትራንሥፖርት መሥጫ፣በህዝብ መዝናኛ ሥፍራ፣በየዕድሩ እና አውጋሩ …እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ሲያጋጥማችሁ፣ እውነት በመናገራችሁ ዱላ እንዳያቀምሷችሁ
በዝጌሃር ! ሆ ሆ!ሂ ሂ!ሃ ሃ!
ሆ ሆ!ሆ ሆ ሆ!
ሄ ሄ ሄ  ! ሃ ሃ ሃ !
በማለት  ለጊዜው ተገላገሏቸው። ” ሙያ በልብነው። ” እንዲሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.