የአሳዛኙ ብላቴና የመሀመድ እና የወላድ እንግልት ! – ነቢዩ ሲራክ

* ኢትዮጵያዊው ታዳጊ በህክምና ስህተት ለ9 ዓመታት ለከፋ አደጋ መዳረጉ ተረጋግጧል !
* የሳውዲ ጤና ጥበቃ ልዩ አጣሪ ኮሚቴ የሰጠው ውሳኔ ግን አሳዝኖናል
* የብላቴናው ቀሪ ህይዎቱም ውስብስብ ሆኗል
* አሰልችውን የዘጠኝ አመታት ፍትህ ፍለጋ ግን አልሰመረም
* ” ከሬሳ የማይተናነስ በድን አድርገው አኮላሽተው ውስጅ ይሉኛል ፣ እንዴት ይህን ውሳኔ ልቀበል ? ፍትህ እሻለሁ! እርዱኝ! ” እናት…
* የጅዳ ቆንስል ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን መከታተል ቢጀምርም ወደ ውጭ ጉዳይ የላከው ደብዳቤ ምላሽ አላገኘም

ህጻን መሃመድ አብድልአዚዝ የአራት ዓመት ንቁ ልጅ ነበር። አልፎ አልፎ ግን በአፍንጫው ላይ የበቀለ ስጋ ሲተኛ ስለሚያጨናንቀው ወላጆቹ ለህክምና ከመካ ወደ ጅዳ ውስጥ ታዋቂ ወደ ሆነው ዶር ሱሌማን ፈቂ በተባለ ሆስፒታል ይዘውት መጡ ። ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት መሆኑ ነው…እናም ብላቴናው መሀመድ ከወላጆቹ ጋር በመሆን ድክ ድክ እያለ ለቀላል ቀዶ ህክምናው ገባ …. ብዙም ሳይቆይ በግማሽ ሰዓት ይከወናል የተባለው ህክም ዘገየ … ቆየና ከቀዶ ጥገናው ወደ ልዩ ጥበቃ ክፍል( ICU – intensive car unit) ተዛወረ ፣ ይህ የተጠበቀ አልነበረምና ቤተሰብ ተጨነቀ … ልጅ መሀመድ “ይነቃል !” ተብሎ ቢጠበቅም መሀመድ ግን አልነቃ አለ … “ይነቃል !” ጥበቃው ከሰዓታት ፣ ቀናት ፣ ከቀናት ሳምንታት ወርና አመታትን ቢገፋም የተኛው ብላቴና አልነቃም !

ይህ በሆነ በዘጠኝ ዓመቱ መሃመድ አብድል አዚዝ በዚያች በተረገመች ቀኑ በተፈጠረ የህክምና ስህተት ላለፉት ለዘጠኝ ዓመታት የአለጋ ቁራኛ ሆኖ የልጅነት እድሜውን እየገፋ ያለበት ዋና ምክንያት በህክምና ስህተት መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አጣሪ ኮሚቴ ትናንት ምሽት አስታውቋል ። ምንም እንኳን የተሰጠው ውሳኔ ሆስፒታሉን ተጠያቂ በማድረግ ካሳ እንዲከፍል ቢወሰንም በሀኪሞች ስህተት አልጋ ላይ በድኑ ያደገው ብላቴናው መሀመድ ህክምና የማግኘት ተስፋውን ያጨለመ ሆኗል። ከምንም በላይ የሚያመው ወደ ሆስፒታሉ ሮጦ ከገባ በኋላ ላለፉት ዘጠኝ አመታት ሳይነቃ እድሜውን ከገፋበት ሆስፒታል እንዲለቅ በጤና ጥበቃ አጣሪ ኮሚቴ መወሰኑ ሲሆን ይህ ውሳኔ እንዳስከፋቸው የመሀመድ ቤተሰቦች አጫውተውኛል ። ” በሚሊዮን የሚቆጠረው ካሳ ምን ያደርግልኛል ” ያሉኝ እናት እንባቸውን እያዘሩ ፣ ገና ሆስፒታል ሳይገባ የሚያውቃቸውን መልከ መልካም ልጃቸውን ራስ እያሻሹ ፣ ላይሰማ ላያይ ላያውቃቸው ልብን በሀዘን በሚነካ ሁኔታ የሚገለባበጥ አይን አይኑን እያዩ እንዲህ አሉኝ …” በጤና ጥበቃ የተላለፈው ውሳኔ በግፍ ልጃችን የተሰናከለብንን ወላጆች የፍትህ ጥያቄ ያላገናዘበ ነው ፣ ከአፍንጫ ላይ ትርፍ ስጋን ለማንሳት ለቀላል ወዶ ህክምና በአራት አመቱ ሮጦ በእግሩ የገባ ልጀን አሰናክለው ወረወሩብኝ ፣ ያበላሹት ልጀን ውጭም ቢሆን ሔዶ ህክምና እንዲያገኝ ነው የምጠይቀው እንጅ እኔ ለልጀ ጉዳት ካሳ ይስጡኝ አላልኩም ፣ ደጋፊ የላቸውም ብለው ለ9 አመታት ማንገላታታቸው ሳያንስ አሁን ካሳ ትወስጃለሽ ፣ ልጅሽን አውጭ ይሉኛል ! ጥያቄየ ልጀ የተሻለ ህክምና ያግኝ ነው! … ልጀን አኮላሽተው ፣ ከሬሳ የማይተናነስ በድን አድርገው ውስጅ ይሉኛል ፣ እንዴት ይህን ውሳኔ ልቀበል ? ፍትህ እሻለሁ! ግፍ እየተፈጸመብን ነውና የፍትህ ያለህ ! የሰው ያለህ እላለሁ ! ” በማለት በእንባ እየታጠቡ ጉዳታቸውን ሲናገሩት ሆድ ያባባል! …የአመታት እንግልት ህመማቸውን ጉዳታቸውን ሲናገሩት ያማል ….

የመሀመድ ቤተሰቦች ለበርካታ አመታት የጅዳ ቆንልንም ሆነ የሪያድ ኢንባሲን ትብብር ጥያቄ አቅርበው ያገኙት ምላሽ አለማግኘታቸውን በተጎዳ ስሜት አጫውተውኛል ። ከዚህ ቀደም ባለፉት አመታት በልጃቸው ላይ ሆስፒታሉ የሰራውን ግፍ በፍትህ አካላት ለማቅረብ የጅዳ ቆንስልንና የሪያድ ኢንባሲን ጨምሮ ወደ ሳውዲ ከፍተኛ ሀላፊዎች ድረስ በመሄድ አሰልች ሙከራዎች አድርገው ባይሳካላቸውም ካለፉት ስድስት አመታት ወዲህ ግን ሙከራቸው ተሳክቶ ጉዳዩ በጤና ጥበቃ አንድ አጣሪ ኮሚቴ መድረሱን በዝርዝት አጫውታወኛል ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በአንባሳደር ውብሸት የሚመሩት የጅዳ ቆንስል ባለድረቦች ጉዳዩን ተቀብለው እየተከለታተሉት እንደሆነም ነግረውኛል ። ምንም እንኳን ቆንስሉ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፈው ክስ ምላሽ ባያገኝና መፍትሄ ባያመጣም የትናንትም ውሳኔው ሲተላለፍ ቆንስል ሙንትሃ ከስራ ሰአታቸው ውጭ በጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመገኘት ከአጣሪ ኮሚቴው ቀርበው ሂደቱን መታዘቸውንና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ቀነ ቀጠሮ መያዙን ለመረዳት ችያለሁ ።

እንደ ግፉዑ መሀመድ ቤተሰቦቹ እምነት ኮሚቴው በአጭር የሚቀጨውንና ተጨባጭ መረጃ ያለውን ጉዳይ ያዝ ለቀቅ እያደረገ ለስድስት አመታት ካጓተተ በኋላ ትናንት ምሽት ላይ በሰጠው ውሳኔ ታዳጊውን ያሰናከለውና የአልጋ ቁራኛ ያደረገው ሆስፒታል ላጠፋው ጥፋት ካሳ እንደሚከፍል አወስኗል ። ያም ሆኖ ያለ ህክምና መሳሪያ ድጋፍና መድሃኒት ለአንድ ቀን መቆየት የማይችለው ልጃቸው መሀመድ ሆስፒታሉን ለቆ እንዲዎጣ ውሳኔ ማሳለፉ በየትኛውም ሚዛን አግባብነት የሌለው በመሆኑ እናት ይናገራሉ ። ከዚህ አንጻር ውሳኔውን መቃወማቸውንና ጉዳዩን ወደ ሳውዲ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማድረስ ፍላጎት እንዳላቸውና መንግስትም ሆነ ማናቸውም ይህን ግፍ የተመለከተ ዜጋ የተነፈጉትን ፍትህ እንዲያገኙ ትብብር ያደርግላቸው ዘንድ ወላጅ እናቱ የፍትህ ፍለጋ ተማጽኗቸውን እንዳቀርብላቸው ከአደራ ጋር ጠይቀውኛል ።

ለዘጠኝ ዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆነው መሃመድ ጉዳይ ገና አዲሰ እያለ ለጅዳ ቆንስል ከፍተኛ ለአንባሳደር ተክለአብና እሳቸው ቀርቦላቸው እልባት ሳይሰጡት አልፏል። ቀጥለው ከመጡት የቆንስሉ ኃላፊዎችን ጨምሮ እስከ ሪያድ ኢንባሲና የሳውዲ ከፍተኛ ሹማምንት መፍትሄ ጠይቀው እንዳልተሳካላቸው የተጎጅው ብላቴና እናት እንባዋን እያዘራች አቤት ብለዋል ።

ከዜጎች መብት ጉዳይ ባለስልጣናት በቀዳሚነት መከታተልና ማስፈጸም ካለባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ከዚህ ቀደም ሌላው ቀርቶ ተጎጅን ወደ ፍትህ አካላት እንዲደርስ ሙከራ ባለማድረጋቸው እኔም ሆነ በርካቶች ጉዳዩ ያገባናል የምንል ዜጎች የሰላ ወቀሳ ማቅረባችን አይዘነጋም ። ከሳውዲ ባለስልጣናት በኩል ግን ጉዳዩ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተመርቶ ጉዳዩን በአጭሩ መወሰን ያልቻሉበት ጉዳይ ግራ ሲያጋባ እስካሁን ቢቆይም በቀጠሮና መመላለስ የደከሙት ወላጆችን ” ልጃችሁን ከሆስፒታል አውጡ !” በሚል የተወሰነው ውሳኔ ልብን በሀዘን የሚሰብር ነው ።

ፍትህ ሲዘገይ የተነፈጉትን ያህል ነው ! እንዲሉ ፣ አሁንም የዘገየው ዘግይቶም ውሉን አልያዘም ። በግፉአኑ ቤተሰቦች ፍትህ ተዛብቷል ። ከዚህ ቀደም በሳውዲ ለሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስትን ተወካዮች ድጋፍ አጥተው ለዘጠኝ አመታት የልጃቸውን መከራ የሚያማቸው ወላጆች በተለይም እናቱ በትናንቱ ውሳኔ አምርረው እያለቀሱ እንዲህ በማለት አስተያየት ሰጥተውኛልሲሉ እንባቸውን እያዘሩ የተገፊው ብላቴና እናት አጫውተውኛል …

ይህ ውሳኔ ከመሰጠቱ አስቀድሞ የካቲተ 30 ቀን 2007 በሆስፒታሉ ስህተት ከሆስፒታል አልጋ ላይ ሳይንቀሳቀስ እድሜውን በፈጀው መሃመድ ላይ ሆስፒታሉ የሆስፒታሉ አስተዳደር ወደ እናቱ ስልክ በመደወል መሃመድ ከሆስፒታሉ ለቆ እንዲወጣ ውሳኔ ማሳለፉንና የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች መረጃው እንደደረሳቸው ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ የሆስፒታሉን ውሳኔውን ተቃውመው ከሆስፒታሉ ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር ቢያንስ በሆስፒታሉ ስህተት የተጎዳውን የማይሰማ የማያይ ብላቴና መሃመድ እንዲወጣ የተላለፈውን ውሳኔ አስቁመውት እንደነበር አይዘነጋም ።

የማይሰማው የማይናገረው ብላቴናው መሃመድና ቤተሰቦቹ የዘገየባቸው ፍትህ ፣ የተነፈገን ያህል ራቀ ብንልም በጤና ጥበቃው ኮሚቴ የተሰጠው ውሳኔ ጤነኛ ነው አልልም ! እናም ፍትህ ያጡ ቤተሰቦች ወደ ከፍተኛ የፍትህ አካላትም ሆነ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳይደርስ የሰራውን ጉዳት አድራሽ የህክምና ተቋም አንድ የቤተሰብ አባላት መጋፋት አልተቻላቸውም ፣ እናም የሚመለከታቸው የመንግስት ተወካዮች ፣ ጉዳዩ ያገባናል የምንል ዜጎች ከተገፊና መንገዱ ሁሉ ጨለማ ከሆነባቸው ተገፊ ቤተሰቦች ጎን መሆን ግፉአኑ ፍትህ እስኪያገኙ አቤት ልንል ግድ ይለናል !

በዚህ ዙሪያ ያቀናበርኩትን መረጃዎችን ያካተተ ልዩ ዘገባ ይዠ እስክቀርብ ሰላም ሁኑ !

ፍትህ እንሻለን !

ነቢዩ ሲራክ
ሚያዝያ 19 ቀን 2007

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.