በዘረኝነት፣ በጥላቻና በመንጋ እየተናጠች ያለች ሀገር

በዘረኝነትና ጥላቻ ምክንያት የዜጎችን ሞትና መፈናቀል መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ ዘረኝነትና ጥላቻን በተለያየ አግባብ የሚያራምዱ አካላትን ለህግ እንዲያቀርብና ኢትዮጵያውያን በመረጡት የሃገሪቱ ቦታ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲጠበቅ የፖለቲካ ድርጅቶች ጠየቁ፡፡

መኢአድና ኢህአፓን ጨምሮ ሰባት ድርጅቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉልና በሌሎች አካባቢዎች በብሄር ፅንፈኛነት የደረሱ ግጭቶችንና ሰብአዊ ጉስቁልና በመዘርዘር መንግስት የዜጎችን መብትና ህይወት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በዘረኝነትና ጥላቻ ምክንያት ዜጎች ቤት ንብረታቸው እየተቃጠለና፣ እየተዘረፈ፣ በገዛ ሃገራቸው ስደተኛ መሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የተፈናቀሉትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመንግስት ድጋፍንና ዋስትና ወደቀዬአቸው እንዲመለሱና መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን ያለማቅማማት በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል – የፖለቲካ ድርጅቶቹ፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶች አክለውም፤ ጊዜ ያለፈበትን ዘረኝነትና ጥላቻ ከሚያራምዱ ኃይሎች ጋርም የሃሳብ ሙግት በማድረግ አላማቸውን የማክሸፍ ተግባር ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ውስጥ በመረጡት ቦታ የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብታቸው ከምንጊዜውም በበለጠ እንዲከበር ጠንካራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰናቸውን ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
በለውጥ አራማጅ ኃይሎች የተጀመረው አመርቂ የለውጥ እንቅስቃሴ ከፅንፈኞችና ለውጡን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ለመውሰድ ከሚፈልጉ ኃይሎች ለመታደግ እንዲሁም ለውጡ ፈሩን እንዳይለቅ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ህዝብም የተደራጀ ትግል በማድረግ አላማውን ለማሳካት ከሚበጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ስር በመሰባሰብ የመታገል ባህልን እንዲያጎለብትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተከታትሎና በጥንቃቄ መርምሮ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአለማቀፍ ህብረተሰብ እንዲያሳውቅም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ባወጡት በዚሁ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ መገናኛ ብዙኃን በፍቅርና መተሳሰብ አብሮ የመኖር ሃገራዊ ጠቀሜታን እንጂ ዘረኝነት፣ ፅንፈኝነትና ጥላቻን እንዲያራምዱም ተጠይቋል፡፡

መግለጫውን በጋራ የሰጡት እስከ ውህደት የሚያደርስ ስምምነት በቅርቡ የተፈራረሙት የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዲዩ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አንአፓ)፣ የአፋር ህዝቦች ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ህዝቦች ነፃነት ፓርቲና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ናቸው፡፡

አለማየሁ አንበሴ/ አዲስ አድማስ

1 COMMENT

  1. በዘረኝነት እየተናጣችሁ ላላችሁ ኤዲተሮች፣
    እንደተለመደው ኦሮሞን ሁሉ “ዘረኛ” ለማለት ነው የኦሮሞ አክቲቪስቶችንና ፖለትከኞችን ፎቶ እንደአርዕስት የለጣጠፋችሁት? ባህር ዳር እና ደሴ ላይ እየተደረጉ ያሉትስ ኋል ቀርና ዘረኛ ድርጊቶች ግን የኦሮሞ ስላልሆኑ ነው የተደበቁት??

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.