‹‹ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሰጠውን ድጋፍ አልቀበልም፡፡›› የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው

‹‹ድጋፉ የሕዝቡን ችግር ያላገናዘበ፣ በዘላቂ ለማቋቋም ለምናደርገው እንቅስቃሴ የማይመጥን ሁኖ በማግኘታችን ድጋፉን እንደማንቀበል እናሳውቃለን፡፡›› በአማራ ክልል የተፈናቃዮች ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ

በአማራ ክልልና ከክልሉ ውጭ በተፈጠሩ ጊዜያዊ ግጭቶ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት እና ሕዝቡ በየወቅቱ የሚያደርጓቸው ድጋፎችም በቂ አለመሆናቸውን እና ዘላቂነት እንደሌላቸው ተፈናቃዮች እያሳሰቡ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል እንዲሁም የአማራ ክልል ወዳጆች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፍግም ታምኗል፡፡ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር (ቴሌቶን) ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል፡፡ ቃል የገቡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላደረጉት አስተዋፅኦ የአማራ ክልል የተፈናቃዮች ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ላቅ ያለ ምሥጋና እንደሚያቀርብ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር ዛሬ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ተፈናቃዮቹ ካሉበት ሁኔታ አንፃር በአስቸኳይ ወደመደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ ቃል የገቡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ቃል የተገባውን እንዲያሰባስቡም አሳስበዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው ሀገሪቱ ለተፈናቀሉት ወገኖች 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን ማስታወቁን የገለጹት አቶ አገኘሁ ‹‹ከዚህ ውስጥ ለአማራ ክልል 4 ነጥብ 798 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አውቀናል፤ ስላደረገው ድጋፍ እናመሠግናለን፡፡ ይህን ድጋፍ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአማራ ተፈናቃዮች ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ አንቀበልም፡፡ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱንና ካላው ካፒታል አንፃር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ አዝነናል›› ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ሀገሪቱ በለውጥ ንቅናቄ ውስጥ በነበረችባቸው አስቸጋሪ ወቅቶች ሳይቀር ባንኩ ላይ በአመኔታ በመቆጠብ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አገኘሁ ‹‹በባንኩ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ተገቢውን ጥበቃ እያደረገ የነበረ ታማኝ ሕዝብ በመሆኑ ባንኩ ከሚያገኘው ትርፍ አንፃር ለሕዝቡ የከፋ ችግር አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ግንባር ቀደም መሆን ነበረበት›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም አሉ›› አቶ አገኘሁ ‹‹በመሆኑም ድጋፉ የሕዝቡን ችግር ያላገናዘበ፣ በዘላቂ ለማቋቋም ለምናደርገው እንቅስቃሴ የማይመጥን ሁኖ በማግኘታችን ድጋፉን እንደማንቀበል እናሳውቃለን›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች በግላቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ በአማራ ክልል ሕዝብ ሥም እናመሰግናለን›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ግርማ ተጫነ / አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.