የጎሳ ፌደራሊዝምበቃሉ አጥናፉ ታዬ(ዶ/ር) ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

በቃሉ አጥናፉ ታዬ(ዶ/ር)
ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

ብዝሃነትን ለማስተናገድ እና ስልጣንን ወደ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ለማከፋፈል የፌደራል ስርዓት ተመራጭ እንደሆነ እንዳንድ ፀሃፍት ቢያተቱም፤ በተቃራኒው ደግሞ የፌደራል ስርዓት በተፈጥሮዎ ግጭትን እንደሚጋብዝ እና ተመራጭ እንዳልሆነ የሚያትቱም ተመራማሪዎች አሉ(አለማንተ, 2003).

ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንፃር እንዳንድ የአፍሪካ አገራት (ኮንጎ, ከ1960-1965፣ ማሊ, 1959፣ ኬንያ, 1963-1965፣ ዩጋንዳ, 1962-1966፣ ካሜሮን, 1961-1972) ከነጻነት በኃላ የፌደራል ስርዓት መርጠው መተግበር ቢጀምሩም አስከፊነቱን ተረድተው የፌደራል መዋቅርን ትተውታል(ኢርከ, 2014)፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሶስት የአፍሪካ አገራት(ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ እና ኢትዬጲያ) በፌደራል ስርዓት የሚተዳደሩ አገራት ቢሆኑም የጎሳ የፌደራል ስርዓት የምትተገብረው  አገር በዓለም ላይ ኢትዬጲያ ብቻ ናት፡፡

ምንም እንኳን  የፌደራል ስርዓት በዘርፉ ተመራማሪዎች ዘንድ አወዛጋቢ ቢሆንም የጎሳ የፌደራል ስርዓት ግን ግጭትን እንደሚፈጥር እና አገርን እንደሚበትን ከአወዛጋቢነት ባለፈ የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡ የጎሳ ፌደራሊዝም እንደ ዩጎዝላቪያ፣ የድሮዋን ሩሲያ(USSR)፣ ችኮዝላቫኪያን በመበታተን የሚታወቅ ስርዓት ሲሆን በእኛ አገርም እንዲተገበር የተፈለገበት ዋናው ምክንያት አገሪቱን ለመበታተን ታስቦ ነው፡፡ እኛ እና እነሱ፣ ነባርና መጤ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ በሚል የጎሳ ፖለቲካ ትርክት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን በቋንቋ ከፋፍሎ ወጣቱ ለአገሩ ሳይሆን ለብሄሩ ብቻ ታማኝ እንዲሆን ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ጥርጣሬን፣ አለመተማመንን፣ ለጎሪጥ መተያየትን ያመጣው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን (ባልና ሚስትን፣ አባትን ከልጁ፣ ልጆችን ከወላጆች) እንዲለያዩ ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡

የኢትዬጲያ የጎሳ ፌደራሊዝም መስራቾች እና አቀንቃኞች አገሪቱን ለመበታትን የተጠቀሙበት ስልት እንደሆነ እየታወቀ፤ ይህን የጎሳ ፌደራሊዝም ማፍረስ ሲገባን በዶ/ር አብይ አስተዳደርም የብሄር ፖለቲካው፣ አድሎዓዊነት፣ ጎጠኝነቱ፣ መታየቱ እጅጉን ልብን ይሰብራል፡፡ ህወሃት የተጠቀመበትን የከፋፍለህ ግዛው የጎሳ ፖለቲካ እንዴት እንደነፃነት ምልክት አድርገን እንጠቀምበታልን? ሰብዓዊነትን ተላብስን፣ ኢትዬጲያዊነት ተጫምትን መቆም ሲገባን እንዴት ለጎሳ አባላቶቻችን ያደረግንላቸውን ነገር እንደ ታላቅ ጀብድ በሚዲያ እንተርካልን? ኢትዬጲያዊነት ሱስ ነው ብሎ የተረከ መሪ እንዴት ብሄርተኝነትን ያራምዳል? ልብ ይስጠን!!!

1 COMMENT

  1. በመሰረቱ የሃገራችንን ፓለቲካ ረጋ ብሎ ከወደኋላ በመጀመር ለሚፈትሽ ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ የተሻለ ነገር ታይቶበት አያውቅም፡፡ እንዲያውም ባጭሩ ለውጥ ማለት በሃገራችን የጠገበን አውርዶ የተራበን በስፍራው መተካት ነው፡፡ ለሃገራቸውና ለወገናቸው ዘርና ቋንቋን ተገን ሳያረጉ የተዋደቁ በመጦርያ ጊዜአቸው አንገታቸው የተቀላበት፤ ለስደትና ለመከራ የተገፉበት የብሄር ፓለቲካ አራማጆች በበከተማና በጭካ ውስጥ የሚራወጡባት ሆናለች፡፡ የክልል ፓለቲካው ጉዳት ጣሊያኖች በጀግኖቹ የሃበሻ ተጋዳዮች ላይ ከረጩት መርዝ ይከፋል፡፡ በዚህ በወያኔ በተቀመረ የዘር ፓለቲካ ሁሉ ሃገርና ባንዲራ አውለብላቢ በመሆኑ ተበደልኩ ብሎ እንባ የሚያፈሰው ቁጥር ብዙ ነው፡፡ የሚበላው ምንም ነገር የሌለው በህልም ዓለም ሆኖ ደረሰብን የሚለውን በደል ለማጣጣት ሲሞክር በራሱ ህይወት ላይ ገበጣ እየተጫወተ እንደሆነ አይረዳም፡፡ በተለይም ተምረናል አውቀናል እናውቃለን የምንለው የፊደላት እውቀት ይዘን በዘር ፓለቲካ ተጠፍረን ሌላው እንዲጠፈርና የእኛን እንዲመስል የምናረገው የተወላገድ ጥሪ አፍራሽ ነው፡፡
    አፍራሽን አፍራሽ እየተካው ሃገሪቱ ያለቅጥ ወደ እማትመለስበት ጎዳና ለመግባት የቀራት ጥቂት ነው፡፡ ከትግራይ፤ ከኦሮሞ፤ ከአማራ ከሃረሬ ከሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች መሆን በምርጫ የተቀበልነው አይደለም፡፡ የትውልድ ሃረጋችን እንጂ፡፡ አንድ አንድን እየገፋና እያሰረ እየገደለ የሚኖርባት ያቺ ሃገር ተሻጋሪ ሃሳብ አልባ የምትሆን ሃገር ናት፡፡ በቅርቡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ብቻ ናት በሚልና አይደለም በሚሉ ወጣቶች መካከል የነበረውን ፍልሚይ ያየሁት በለቅሶ ነው፡፡ ድላና ገጀራ ይዞ የሚዘፍን ትውልድ እብድ እንጂ ለራሱም ለሌላውም የሚበጅ ትውልድ አይደለም፡፡ የሚገርመው ፓሊሱም የተዋቀረው በየወገኑና በየቋንቋው በመሆኑ አድሎአዊ ነው፡፡ እድሜ ለዘረኛው ወያኔ ሃገር የሚለው እምነት በቋንቋና በዘር ከተሰለፉ ጠባቦች ተፍቆአል፡፡ በዚህ መካከል የውጭ ሃገር የስለላ መረብ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሃገሪቱ ጭራሹን እንድትፈራርስ በሃይማኖት በኩል ሳውዲዎች/ የምንገዳድልበትን ጥይትና ጠበንጃ በማቀበል ቱርክ ያለፈ ሃይላቸውን ለማቋቋም የምትታገለው ራሺያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እሳቱ ላይ ነዳጅ በመጨመር የማይቆም እልቂት እንዲፈጠር በመስራት ላይ እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ ለ 30 አመት የአሰብን ወደብ ለ United Arab Emirates ያከራየችው ኤርትራ ወታደሮቿን በየመን ማሰለፏንና ለዚህም ከሳውዲና ከሌሎችም የአረብ ሃገራት ድጎማ እንደምታገኝ የታመኑ ምንጮች አትተዋል። የሚገርመው ግን ጥቁር ህዝብ ጨካኝነቱ በራሱ ወገኖች ላይ ነው። የወያኔና የሻቢያም ጀግንነት ባህር አቋርጦ የመጣ ጠላትን በመፋለም ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ወንድምና እህቱን ገድሎ የሚፎክር የሞኝ ገድል ነው። ይህን እንዴት ነጻ ጭንቅላት ያለው ማየት ይከብደዋል? እኛነታችን ተቀብለን ተማምነን መኖር ባለመቻላችን የአረብና የነጭ የፓለቲካ የእግር ኳስ የምንሆነው መቼ ነው? የነጻነትስ መለኪያው ምንድን ነው? ስንቦጫጨቅ፤ ስንጋደል፤ በዘርና በጎሳ በቋንቋ ስንፋለም መሽቶ እየነጋ ሌላው ዓለም ጥሎን ሄድ። ለዘረኞችና ለከፋፋዮች ሞት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.